Saturday, 08 June 2019 00:00

መንግስት በግብረሰዶም ጉዳይ የሀገሪቱን ህግ እንዲያስከብር ጥሪ ቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ግብረሠዶማውያን ኢትዮጵያን እንጐበኛለን ማለታቸው ማህበረሰቡን ያስቆጣ ሲሆን የሀገሪቱ የሃይማኖት ተቋማት ግብረ ሰዶማውያን ኢትዮጵያን መርገጥ አይችሉም መንግስት ህግ ያስከብር አቋሙን ከወዲሁ ያሳውቅ ብለዋል፡፡  
ጐብኚዎቹ ትኩረት ያደረጉበት የላሊበላ ቤተክርስቲያን አስተዳደር በበኩሉ በፈጣሪ ጽዩፍ የሆነውን ድርጊት ፈፃሚ ግብረሰዶማውያንን ተቀብሎ አላስተናግድም፤ ስለአካባቢው ለሚደርስባቸው ጉዳትም ከወዲሁ ራሣቸው ኃላፊነት ይውሰዱ ሲል በአጽንኦት አስጠንቅቋል፡፡
በአሜሪካ ቺካጐ ዋና ቢሮውን ያደረገውና ከ30 አመታት በላይ ግብረሰዶማውያንን በተለያዩ ሀገራት የሚያስጐበኘው ቶቶ አስጐብኚ በመጪው ጥቅምት ነበር የኢትዮጵያ አባሎቹን ይዞ ጉብኝት ለማድረግ የወጠነው፡፡
“የኢትዮጵየ ታሪካዊ እሴቶች” በሚል መርህ የጉብኝት መርሃ ግብሩን አዘጋጅቻለሁ ያለው አስጐብኚ ድርጅቱ በመላው ዓለም ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ውግዘት እና ተቃውሞ ማስተናገዱን ተከትሎ የጉብኝት እቅዴን በድጋሜ አጤናለሁ ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ጉብኝቱን መሠረዝ አለመሠረዙን ማረጋገጫ ከመስጠት ተቆጥቧል አስጐብኚ ድርጅቱ፡፡
አስቀድሞ የጉብኝት እቅዱን የተቃወመው የ120 ማህበራት ስብስብ የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ሠልስቱ ምዕት መንፈሳዊ ማህበራት ህብረት ግብረ ሰዶማዊነት ለኛ ለኢትዮጵያውያን ከሃይማኖታችን ከትውፊታተንን ከኢትዮጵያዊ ባህላችን ያፈነገጠ በመሆኑ እንዲሁም በሀገሪቱ ህግም ወንጀል በመሆኑ በእምነት ቦታዎች እና በሀገራችን የታቀደውን ጉብኝት አጥብቀን እንቃወማለን ብሏል፡፡  ይህን ሰይጣናዊ ድርጊት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለይም የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በአጽንኦት እንዲያወግዙት ጥሪ አቅርበዋል ማህበራቱ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በጉዳዩ ላይ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ማህበራቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስም በተመሳሳይ ድርጊቱን በጽኑ አውግዞ የግብረሰዶማውያኑ ኢትዮጵያን የመጐብኘት እቅድ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ብሏል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው የግብረ ሰዶማውያኑን ድፍረት መንግስት እንዲያወግዝ እንዲሁም የወንጀል ህጉን በማጥበቅ ቁርጠኝነቱን እንዲያሳይ ጠይቋል፡፡ እንዲሁም ግብረሰዶማውያኑ በምንም ተአምር ቅዱሳት መካናትን እንዳይረግጡ ለመንግስት ማሳሰቢያ እንዲፃፍም ቅዱስ ሲኖዶሱ ወስኗል፡፡
“ድርጊቱ በሃይማኖት ሃጢያት፣ በባህል ነውርና አፀያፊ በኢትዮጵያ ህግ ወንጀል ነው” ብሏል ቅዱስ ሲኖዶስ፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በበኩሉ ሃጢያት ነውርና ወንጀል የሆነውን ግብረ ሰዶማዊነት በሀገራችን እንዲስፋፋ እየሠሩ ያሉ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸው በእጅጉ እንዳሳሰበው አስታውቆ የድርጊቱ ፈፃሚዎች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ እንዲሁም መንግስት ህግን በማስከበር ጠበቅ ያለ ቁጥጥር እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡
“የግብረ ሰዶም ድርጊት ፈጣሪን የሚያስቆጣ የአመጽ ተግባር ነው” ያለው ጉባኤው ተግባሩም የሰውነት ዝቅጠት መገለጫ እንጂ በምንም መልኩ ከሰብአዊ መብት ጋር ሊጐራኝ የሚገባው አይደለም ብሏል፡፡
የሀገር ቅርስና ታሪካዊ ቦታዎችን ኢላማ ያደረገ የእንገናኝ መልዕክቶችና ቀጠሮዎችን መንግስት በአስቸኺይ እንዲያስቆም፣ ለዚህ የረከሰ እኩይ ተግባር ተባባሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እጃቸውን እንዲሰበስቡ አሳስቧል ጉባኤው፡፡ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን ይወጣ ሲልም ጉባኤው አሳስቧል፡፡
የግብረ ሰዶማውያኑ አስጐብኚ ድርጅት ኢትዮጵያን ኢላማ አድርጐ ለመምጣት መሞከሩን የአክሱም ከተማ አስተዳደር፣ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳደር ተቀባይነት የለውም ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ታዋቂ ተጽእኖ ፈጣሪ የሃይማኖት ልሂቃን እና የፖለቲካ አክቲቪስቶችም ድርጉቱን አውግዘው መንግስት የሀገሪቱን ህግ እንዲያስከብር አሳስበዋል፡፡
መአዛ ጥበባት ዳንኤል አስራት በማህበራዊ ገፃቸው ባሠፈሩት መልዕክት “ኢትዮጵያ ግብረሰዶማዊነትን በባህሏም፣ በእምነቷም በህጓም አትፈቅድም፡፡ ካልመጣን ሞተን እንገኛለን ካሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት አይነት የእንግዳ አቀባበል አለ በሏቸው” ብለዋል፡፡

Read 6119 times