Saturday, 08 June 2019 00:00

በአክሱም ዩኒቨርስቲ በተገደለው ተማሪ የተጠረጠሩ 10 ተማሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


                  ሰሞኑን በአክሱም ዩኒቨርስቲ በተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት አንድ ተማሪ ህይወቱ ማለፉ የሚታወቅ ሲሆን፤ ከተማሪው ግድያ ጋር በተያያዘ 10 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው በፖሊስ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው::
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ በተከሰተ ግጭት አንድ ተማሪ መሞቱን ተከትሎ ከግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በአክሱም ዩኒቨርስቲ የብሔር መልክ ያለው ውጥረት ተከስቶ እንደነበር ያስረዱት የአክሱም ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት፤ ተማሪዎች ድንጋይ መወራወር ሲጀምሩ የፀጥታ ኃይሎች ወደ ግቢው ገብተው ለማረጋጋት መሞከራቸውን ተናግረዋል፡፡
ሆኖም የብሔር መልክ ያላቸው ትንኮሳዎች አይለው ማክሰኞ ግንቦት 27 ቀን 2011 ዓ.ም፣ የኢድ አልፈጥር በዓል ቀን ሁሉም ተማሪዎች ዕረፍት ላይ በነበሩበት አጋጣሚ፣ ከረፋዱ 4፡30 ላይ በተወሰኑ ተማሪዎች የድንጋይ ውርወራ ግጭት ማገርሸቱንና በግጭቱም ዮሐንስ ማስረሻ የተባለ የመካኒካል ኢንጅነሪንግ የ2ኛ ዓመት ተማሪ ህይወቱ ማለፉን ፕሬዚዳንቱ ያስረዳሉ፡፡
በዚህ ግጭት ሶስት ተማሪዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና ላይ እንደሚገኙም የተገለፀ ሲሆን በርካቶች ደግሞ ቀላል ጉዳት አጋጥሟቸው መታከማቸውን ለማወቅ ተችሏል::
ረቡዕ እለት አምስት ያህል ተማሪዎች በግጭቱ ተሣትፎና ወንጀል ፈፃሚነት ተጠርጥረው መታሰራቸውን ዩኒቨርስቲው ያስታወቀ ሲሆን ድርጊቱን በጽኑ ያወገዙት የትግራይ ም/ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረ ፂዮን ገ/ሚካኤል በበኩላቸው፤ በዩኒቨርስቲው ለተፈጠረው ብሔር ተኮር ግጭትና ለተማሪው ሞት ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለህግ ይቀርባሉ ብለዋል፡፡
“ድርጊቱ አስነዋሪ ነው” ያሉት ዶ/ር ደብረጽዮን፤ “ትግራይ የብሔሮችና ብሔረሰቦች መኖሪያ መሆኗን አምኖ ለመጣ ተማሪ፣ እንዲህ አይነት ተግባር መፈፀም፣ ሰላም ወዳዱን የክልሉን ህዝብ ባህልና ታሪክ የማይገልጽ ነው” ብለዋል፡፡
ግንቦት 16 ቀን 2011 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ በተመሳሳይ ሁኔታ በተማሪዎች በተቀሠቀሰ ግጭት፤ የሦስተኛ አመት የኢኮኖሚክስ ተማሪ የነበረው ወጣት ሰአረ አብርሃ ህይወቱ ማለፉ አይዘነጋም፡፡ በዚሁ ግጭት 3 ተማሪዎችም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ገብተው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ተማሪዎቹ የተገደሉት በድንጋይና በዱላ ተደብድበው እንደሆነም ተነግሯል፡፡
በሌላ በኩል፤ ባለፈው ሐሙስ በነቀምቴ ከተማ “ፋክት” በተባለ ሆቴል ላይ በተፈፀመ የቦንብ ጥቃት፣ የነቀምት ከተማ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋች የሆነው ወንድወሰን ዮሐንስ የተገደለ ሲሆን፤ ሶስት ሰዎች ላይም ከባድ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል፡፡ ጥቃት አድርሰዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑም ታውቋል፡፡

Read 6175 times