Print this page
Saturday, 08 June 2019 00:00

የሰኔ 1/97 ሰማዕታት ዛሬ ይዘከራሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 የምርጫ 97” ቀውስን ተከትሎ፣ ሰኔ 1 ቀን 1997 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣ በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ የመብት ጠያቂ ሰማዕታትን የሚዘክር መርሃ ግብር፣ ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች በተገኙበት ዛሬ ጠዋት በመኢአድ ቢሮ ይካሄዳል፡፡
ይህን “ዝክረ ሰማዕታት” ያዘጋጁት የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የሰማዕታቱ ቤተሰቦች ኮሚቴ በማቀናጀት እንደሆነ የገለፁት የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ፤ በዘንድሮ መርሃ ግብር የ97 ምርጫ ቀውስን ተከትሎ ከሃገር የተሰደዱ ፖለቲከኞችና ምሁራንን ጨምሮ፣ ከ10 በላይ ሃገር አቀፍ ፓርቲዎች ይሳተፉበታል ተብሏል፡፡
“ሰማዕታቱ ለኢትዮጵያውያን ነፃነት የከፈሉት ዋጋ በመሆኑ ዕለቱን ከፍ አድርገን እንዘክረዋለን” ያሉት አቶ ሙሉጌታ፤ በመርሃ ግብሩ ላይ አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ የቀድሞ የቅንጅት አመራሮችና አባላት እንዲሁም ሌሎች እንግዶች ይገኛሉ ተብሏል፡፡
በዚህ መርሃ ግብር ላይ ሰማዕታቱን የሚዘክሩ ስነ ፅሁፎችና “የኪነ ጥበብ ስራዎች የሚቀርቡ ሲሆን፤ ወቅታዊ የሃገሪቱን ሁኔታ የሚዳስስ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦም በተሳታፊዎች ውይይት እንደሚደረግበት ተነግሯል፡፡  
መኢአድ ሰኔ 1 ቀን 1997 በአዲስ አበባ ብቻ 50 ዜጎች መገደላቸውን የሚያስረዳ የተጠናቀረ የሰነድ ማስረጃ እንዳለው የጠቆሙት አቶ ሙሉጌታ፤ የእነዚህ ሰማዕታት ቤተሰቦች የጋራ ማህበር መመስረታቸውን አስታውቀዋል፡፡
መርሃ ግብሩ ፒያሳ ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የመኢአድ ቢሮ፣ ነገ ከጠዋቱ 4 ሰዓት ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዲታደሙ ጥሪ ቀርቧል፡፡

Read 5771 times