Print this page
Monday, 10 June 2019 10:23

ለማስተማር ሳይንሳዊ ዘዴዎችን ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 በሕክምናው ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሙያዎች ስለሚሰሩት ስራ ይዋል ይደር ሳይባል በጊዜው ጠንቅቀው ማወቅ የሚገባቸውን ነገር ሊያውቁ ይገባል፡፡ ምክንያቱም በተማሩት ሙያ የሚያ ገለግሉት በቀጥታ ሕይወትን የማዳን ስራ ስለሆነ ነው፡፡ ይህ ሙያ እንደሌላው ሙያ ቆይ ይደርሳል፤ቀስ ተብሎ ሊሰራ ይችላል፤ዛሬ ይኼኛው ሐኪም ካልቻለው ነገ ያኛው ሐኪም ይሞክረው ….እከሌ እስኪመጣ ድረስ …የማያይባልበት ቅጽበታዊ ውሳኔን የሚያስፈልገው ስለሆነ ነው፡፡ ማንኛውም ሐኪም ቢያንስ ቢያንስ የቀረበለት ሕመምተኛ ጉዳይ ከአቅሙ በላይ መሆኑን ለማወቅ እንኩዋን ቢሆን እውቀቱ ያስፈልገዋል፡፡ ካልሆነ ግን በቀላሉ ሊድን በሚችል ሕመም ምክንያት ለሕክምና የቀረበ ሰው ሕይወት ባልተገባ ሁኔታ በቀላሉ ሊያልፍ ይችላል፡፡ አንድ የህክምና ባለሙያ ከትምህርት አለም ወጥቶ በስራ ለመሰማራት በእርግጠኝነት ብቃቱ ሊረጋገጥ የሚችልበት እውቀት መቅሰምና ምዘናውን ማለፍ እንዲሁም የሚያገኘው ማረጋገጫ እምነት እና ኃላፊነት ከተጣለበት አካል ሊሆን ይገባል፡፡ Blue Print   የሚለውን የትምህርት መመዘኛ መመሪያ በሚመለከት ባለፈው እትም ከአሰልጣኙ ዶ/ር ሰለሞን ወርቁ እና ከሰልጣኝ ዶ/ር ወንድሙ ጉዱ አንዳንድ ሀሳቦችን እንስተን ቀሪውን በዚህ እትም ልናስነብባችሁ እነሆ ብለናል፡፡
ዶ/ር ሰለሞን ወርቁ በኢፌድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሰው ኃይል ልማት የትምህርት ስልጠና ከፍተኛ አማካሪ ናቸው:: በአለም አቀፉ ፕሮግራም በሚቺጋን ዩኒቨርስቲ የትምህርትና ስልጠና ዳሬክተር በመሆን ከኢትዮጵያም ውጪ በማስተማር ስራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ መንግስታዊ ድርጅቶች ማለትም እንደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፤ትምህርት ሚኒስቴር ከመሳሰሉት ድጋፍ እየተደረገላቸው ስለሆነ አስተማሪዎችን በማብቃቱ ረገድ አስፈላጊውን ስራ በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ አሁን እንደባህል እየታየም የህክምና ትምህርት የሚለውን ዘርፍ እየተቀበሉት መጥተዋል፡፡
ዶ/ር ሰለሞን እንዳሉት፡-
‹‹….ለእኔ የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ አኩዋያ የማምንበት ማንኛውም አይነት በማስ ተማር ስራ ላይ የተሰማራ የህክምና ባለሙያ አስተምራለሁ ካለ ሳይንሳዊ የማስተማር ዘዴ ዎችን በደንብ ጠንቅቆ ማወቅ አለበት፡፡ መተግበርም አለበት፡፡ በዚህ መልክ ከተሰራ ብቃት ያለው ተማሪን ወይንም ባለሙያን ያወጣል፡፡ ብቃት ያለው ባለሙያ ምሩቅ ወጣ ማለት የተሻለ አገልግሎት ለታካሚው ማድረስ ይቻላል ማለት ነው፡፡  በዚያው ልክ የሚወጣውን ከማረጋገጥ አኩዋያ ብቃት ያለው ጥሩ የምዘና ዘዴ ካላስቀመጥን የምናወጣቸው ባለሙያዎች በቂ ችሎታ አላቸው ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡ አሁን በዚህ ዘርፍ በሙያ ማህበራትም ብዙ እንቅስቃ ሴዎች ስላሉ ጥሩ ጊዜ መጥቶአል ማለት ይቻላል፡፡›› ብለዋል፡፡
ሙያን ከማዳበር አኩዋያ ስልጠና አስፈላጊ ነው የሚለውን ሀሳብ ቀደም ብሎ ስራው ሲጀመር የነበረው ምላሽ አሳዛኝ ነበር:: ዲግሪውን ለመስራት ከወሰድኩት ትምህርት ሌላ ስልጠና ምን ያደርጋል የሚል አይነት ምላሽ የነበረው ሲሆን አሁን ግን ከተማሪው እና ከሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ ቁጥር መጨመር ጭምር ተመርቀው ስራ ላይ የሚውሉ ባለሙያዎች ችሎታ አነጋጋሪ እየሆነ የመጣበት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህም የተነሳ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ሆነ ሌሎች ተቋማት መገናኛ ብዙሀንን ጨምሮ የትምህርት ጥራት መጉዋደልን እንደመነጋገሪያ  አድርገው የወሰዱት ሲሆን የትምህርት ጥራት መጉዋደል ከደረሰባቸው ተቋማት አንዱ ደግሞ የጤና ትምህርት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡
በሕምናው ዘርፍ የሐኪሙንና የታካሚውን አለመመጣጠን በሚመለከት በርካታ የህክምና ተማሪዎች ተምረውና ተመርቀው ሲወጡ ብዙዎቹ ታካሚውን ከማገልገል አኩዋያ በተገቢው ቁመና ላይ አይገኙም፡፡ ብዙ ሐኪም ለማምረት ጥረት በሚደረግበት ጊዜ ጥራቱም ላይ ችግር እንዳያስከትል ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት የህክምና ተማሪዎች በቁጥር አነስተኛ የነበሩ ሲሆን አሁን ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ወደትምህርት ይሰማራሉ፡፡ መም ህራን ተማሪዎቻቸውን አያውቋቸውም፡፡ የህክምና ትምህርት ደግሞ እንደሌሎች ትምህርቶች በንባብ ብቻ የሚወጡት ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ ችሎታን በተግባር ማሳየት የሚጠበቅበት ነው፡፡
የኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር በማህጸንና ጽንስ ሕክምናው ዘርፍ ለመሰማራት በትምህርት ላያ ያሉ ሐኪሞችን ጥራት እና ብቃት ለማረጋገጥ የሚቻልበትን ይህንን የስልጠና ሂደት ማካሄድን መርጦአል፡፡ የዚህ ውጤትም በሙያው ክህሎትን አዳብረው የሚወጡ ባለሙያ ዎች የሚመዘኑበትን መርህ ማዘጋጀት ትልቁ ተግባር በመሆኑም በመምህርነት የተሰማሩ ባለ ሙያዎችን ማሰልጠን ተጀምሮአል፡፡
በመሰልጠን ላይ ከነበሩት ባለሙያዎች ዶ/ር ወንድሙ ጉዱ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲ ካል ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር አንዱ ናቸው፡፡ ባለፈው እትም ለንባብ በቀረበው ጽሁፍ እንዳ ስረዱት ይህ ፈተናን ለማዘጋጀት ብሉ ፕሪንት ያስፈልጋል የተባለው ስልጠና በአማርኛው የፈተና ንድፈ ሀሳብ ሊባል ይችላል፡፡ ባለሙያዎቹ የሚቀርብላቸው ፈተና ከየትኛው የትምህርት አይነት ምን ያህል በሚል የሚወሰንበት እና በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በተመሳሳይነት ፈተናው የሚቀርብበት ነው፡፡ ለምሳሌ በዚህ አመት በማስተማር ላይ ባሉት 12 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተመሳሳይ ጥያቄ ወጥቶላቸው ከመካከላቸው በተወሰኑት ዝቅተኛ ነጥብ ከተገኘ ለዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪዎቹ በቂ እውቀት እንዳላገኙ ወይንም እንዳልተማሩ ምላሽ ይሰጣል፡፡ ይህ ምክንያቱ ምን እንደሆነ በጥልቅ እንዲፈተሸ እና በተመሳሳይ ደረጃ ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች እኩል የማስተማር ሂደቱ ተስተካክሎ እንዲቀጥል ጥረት ይደረጋል፡፡ ከትምህርት አሰጣጡ ነው ? ወይንስ ከማስተ ማር ዘዴው ? አለዚያም ከተማሪው ለትምህርት ዝግጁ ካለመሆን ነው? …ወዘተ የመሳሰሉት ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡
ዶ/ር ወንድሙ አክለውም አንድ የማህጸንና ጽንስ ሐኪም አንዲትን እናት ለማከም ብቃት አለው የለውም የሚለውን ለማወቅ መመዘኛውን በትክክል አገር አቀፍ አድርጎ መቅረጽ ይገባል፡፡ እንደገናም certification board exam በሚለው ደረጃ ተፈትኖ ማለፍ ካልቻለ ትምህርቱን ወይንም ልምምዱን እንደገና እንዲቀጥል ደደረጋል እንጂ በቀጥታ ከታካሚዎች ጋር አይገ ናኝም፡፡ ስለዚህም በሙያው ብቁ ካልሆነ ደካማው ጎን የት እንዳለ አስቀድሞ ለማወቅ ስለሚረዳ ተጠቃሚዎችን የሚጎዳ አሰራር አይከሰትም፡፡ ይህንን ስልጠና ለመውሰድ ከ12 ዩኒቨርሲቲዎች በማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስትነትና  መምህርነት የሚሰሩ ባለሙያዎች የተገኙ ስለሆነ በአጭር ጊዜ ተግባራዊ ወደማድረጉ እንደሚገባ እምነቴ ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር ሰለሞን ወርቁ እንደሚሉት ይህ ብሉ ፕሪንት ወይንም የፈተና ንድፈ ሀሳብ ምን ይይዛል ወይንም ምን መምሰል አለበት ከሚለው በፊት ፈተና ለምን ? የሚለውን ጥያቄ መመለስ መቻል አለብን ፡፡ አንድ የህክምና ሙያ ተማሪ ትንንሽ መረጃን ሰብስቦ ከትምህርት ቤቱ በመውጣት ብቃት ያለኝ ባለሙያ ነኝ ሊል እንደማይችል ሁሉም የሚያምንበት ነው፡፡ አንድ ተማሪ የመማር ቆይታውን ጨርሶ ከትምህርት ቤቱ ከወጣ በሁዋላ ወደ ስራው አለም ሲቀላቀል ሊሰራበት የሚችለው ውጤት ሲያስመዘግብ ፈተናው ውጤታማ ነው ተማሪውም ብቃት አለው ሊባል ይችላል፡፡ ስለዚህ ምዘናው ይሄ ባለሙያ በስራው አለም ወደፊት ሊያጋጥም የሚችለውን ችግር የሚመስል ጥያቄ ተሰጥቶት ያንን ማለፍ ሲችል ብቻ ብቃት ያለው አስተማማኝ ባለሙያ ሊባል ይችላል፡፡
ይህ የምዘና ብሉ ፕሪንት ተማሪዎቹ በትምህርት ላይ በቆዩበቸው ጊዜያት የተሸፈኑትን የትም ህርት አይነቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት የትኞቹ ርእሶች ጥያቄ ሊወጣላቸው ይገባል ?ስንት ጥያቄ ከየትኛው አርእስት ሊወጣ ይገባል ? የመሰሰሉትን በመመሪያ በአንድ አይነት ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ማዘጋጀት ይገባል፡፡ የፈተናው አይነት በቁጥር ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡
የህክምና ሙያ በመጀመሪያ የበሽተኛው ችግር ምንድነው ብሎ ማወቅ ይገባዋል፤
ይሄ በሽተኛ ምን አይነት መድሀኒት ያስፈልገዋል የሚለውን መለየት አለበት፤
በሽታው የትኛውን አካል በምን መልክ ነው ያጠቃው የሚለውን ለመለየት የሚያስችል ሳይንሳዊ እውቀት ሊኖረው ይገባል፤
አንድ ሐኪም ከበሽተኛው ጋር ቁጭ ብሎ በሽተኛው ምን ማድረግ እንዳለበት መምከር መወያየት እንዳለበት አስቀድሞ ሊያውቅ ይገባል፡፡
እነዚህ ዋና ዋና ነገሮች በምዘናው ውስጥ ተካተው ብቃት ያለው የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ባለሙያ ለማፍራት እንዲቻል ሙያተኞች በሚማሩባቸው 12 ዩኒቨርሲቲዎች ተግባራዊ ለማድረግ ተግባሩ ተጀምሮአል፡፡  

Read 8105 times