Saturday, 08 June 2019 00:00

ጅቡን የወጋኸው ምኑን ነው ቢሉት፤ አፉን አለ አፉን ከወጋኸውማ አሰፋኸው

Written by 
Rate this item
(5 votes)


               ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ቤት ውስጥ አንድ አህያና አንድ የቤት ውሻ ይኖሩ ነበረ፡፡
አህያው እግርግም ውስጥ ይታሰራል፡፡ ብዙ መኖ በዙሪያው ይቀመጥለታል፡፡ በጣም ጠግቦ ይበላል። ጌታው ደግ በመሆኑ እንደ ልቡ እንዲያናፋም ይፈቀድለታል፡፡
የቤት ውሻው ደግሞ ጌታው ከውጪ ሲመጣ በር ድረስ ሄዶ ይቀበለዋል፡፡ ጌታውም ያመጣለትን ቅንጣቢ ሥጋ ይሰጠዋል፡፡
ወደ  ቤት አስገብቶም እጭኑ ላይ አስቀምጦ፣ እያሻሸ፣ እራት ሲበላ እንደገና ጉርሻ ይሰጠዋል፡፡ አህያ ከደጅ ሆኖ ለውሻው የሚደረግለትን እንክብካቤ በማየት በጣም ይቀናል፡፡
አንድ ቀን አህያ፤
“ውሻ ሆይ?” ይላል፡፡
“አቤት” አለ ውሻ፡፡
“እኔ ባንተ ህይወት በጣም እቀናለሁ”
“ለምን?”
“ጌታችን ከበራፉ ጀምሮ እየመገበህ፣ እያሻሸህ፣ አብሮ ገበታ እያቀረበህ፣ አብረህ ቴሌቪዥን እንድታይ እየፈቀደልህ፣ ሳሎን እያሳደረህ እንደ ሰው ያኖርሃል፡፡ እኔ ግን ብርድ እየፈደፈደኝ አድራለሁ፡፡ ጠዋት ተነስቼ እህል ተጭኜ  ወፍጮ ቤት እሄዳለሁ፡፡ ስመለስ ቀርበታ ተጭኜ ወንዝ እላካለሁ፡፡ ከዛ ሸቀጣ ሸቀጥ ተጭኜ ገበያ እሄዳለሁ፡፡ እንዲሁ ስሸከም ውዬ ስሸከም ይመሻል፡፡ የኔን ኑሮ ካንተ ሳወዳድረው ንድድ ይለኛል” አለው በምሬት፡፡
ውሻም፤
“ምን ታደርገዋለህ፡፡ ይሄ የተፈጥሮ ጉዳይ ነው፡፡
ምንም ብናደርግ ልናሻሽለው የምንችለው ጉዳይ አይደለም፡፡”
አህያም፤
“የለም ይሄንን የምንለውጥበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም፡፡ እኔ የማደርገውን ታያለህ” አለ፡፡
ውሻም፤
“ተው አይሆንም፡፡ ይህንኑ ኑሮህን ታበላሸዋለህ፡፡ አርፈህ ብትቀመጥ ይሻላል” አለውና ተለያዩ፡፡
አንድ ቀን አህያ የታሰረበትን ገመድ በጠሰና እየፈነጨ ሳሎን ገባ፡፡ እንደ ውሻው ጭራውን እየቆላ ፣ጌታው ጭን ላይ ሊቀመጥ ሲሞክር፣ አገሩን አተራመሰው፡፡
ሳህኑ መሬት ላይ ወደቀ፡፡ ጌታው ተፈነገለና ከነወንበሩ ወለሉ ላይ ተንጋለለ!
ይሄኔ የቤቱ አሽከሮች ትላልቅ ቆመጥ ይዘው መጡ፡፡ አህያውን እንዳይሞት እንዳይድን አድርገው እየቀጠቀጡ ፣ከቤቱም፤ ከግቢውም አስወጥተው በሩን ዘጉበት፡፡ አህያ ደም በደም ሆኖ፣ባቡር መንገድ ላይ ተኝቶ ቀረ፡፡
* * *
ቦታን አለማወቅ እርግማን የመሆኑን ያህል፣ አቅምን አለማወቅ ደግሞ ከመርገምት የከፋ መርገምት ነው፡፡ መንገድ ስላለና እግር ስላለን ብቻ አንሄድበትም፡፡ አቅጣጫውን ማወቅ አለብን፡፡ ወቅትንም መጠበቅ ይጠበቅብናል!
ስለዚህ እንግዲህ፣ ቦታ፣ አቅም፣ መንገድና አቅጣጫን ማወቅ የመጪው ዘመን ትምህርታችን ይሁን።
“በደጉ ጊዜ ሆያ ሆዬ ሲጨፈር፤
ብትሰጠኝ ስጠኝ ባትሰጥ እንዳሻህ
ከጐረቤትህ ከነሱ ጋሻህ” ይባል ነበር፡፡
ዛሬ ጋሻ ቀርቶ ሁዳይም የለምና ዘፈኑ ተቀይሯል፡፡
“እዚያ ማዶ አንድ ሻማ እዚህ ማዶ አንድ ሻማ፤
የኛ መብራት ኃይል ባለመቶ አርማ” በሚል ምፀት ተለወጠ፡፡
“ክፈት በለው በሩን የጌታዬን” ብለናል በቡሄ፡፡
የ”ሀሁ በስድስት ወሩዋ”
ሙሾ አውራጅ፣ እቴሜት ጌኔ አምበርብር ደግሞ
“ዋይ ዋይ
ህመም ለህመም ሳንወያይ
አንተ ከመሬት እኛ ከላይ” ያለችውን ገልብጠን “እኛ ከመሬት አንተ ከላይ” ተባብለናል፡፡
 ለውጥ በአንድ ጀንበር ይምጣ አይባልም፡፡ “ዓይንህነገ ይበራልሃል”
ሲባል፤ ዛሬን እንዴት አድሬ” አለ እንደሚባለው አንሆንም፡፡
ምኞታችንና ጥያቄያችን ብዙ፤ መልሳችን ግን ጥቂት ነው፡፡ ሚዛን ይሸቀባል ወይ? የኑሮ ውድነት የት ደረሰ? ዲሞክራሲያችን ፋፋ ወይ? ፍትሕ አበበ ወይ? ኢኮኖሚው አደገ ወይ? ትምህርት ተስፋፋ ወይ? እስፖርት በለፀገ ወይ? ቤት ኪራይ ረከሰ ወይ? ሙስና ቀነሰ ወይ? ወንጀል መነመነ ወይ? ሹም - ሽር ቀነሰ ወይ? መንገድ በዛልን ወይ? ህንፃዎች በዙ ወይ? መኖሪያ ቤት ሞላን ወይ? ሻጭና ሸማች ተስማምተው ከረሙ ወይ? መልካም አስተዳደር ሰፈነ ወይ? መብራት ይጠፋል ወይ? ውሃ ይደርቃል ወይ? ኔትዎርክ ይበጣጠሳል ወይ? በመጨረሻም ገቢ ጨመረ ወይ? ወጪ ቀነሰ ወይ? ወይስ የተገላቢጦሽ ሆነ?
ጥያቄያችን እጅግ ረዥም፣ መልሳችን በጣም አጭር ነው፡፡
በአጠቃላይ ግን ኑሮ ተመቸን ወይ? ሰፊው ህዝብ “የባሰ አታምጣ” አለ? ወይስ “ነገ በተስፋ የተሞላ ሆነልኝ” አለ፡፡ መቼም፤ ወቅቱ የትራንስፎርሜሽን ነው ብለን ለማጽናናት አንችልም፡፡ አዝመራ እሚደርሰው በሰኔ፣ እኔን የራበኝ አሁን” ይለናላ! በክፉ ዘመን የሰው ሁሉ ስሙ “አበስኩ ገበርኩ ነው” እንዳለው ይሆን?
የዱሮ ዘመን ሊቀመንበር፤ ኤክስፐርቶች ግራፍና ስታቲስቲክስ ደርድረው፤ “ሀገራችን ለመለመች፣ አደገች፣ ዘንድሮ እህል በሽበሽ እንደሚሆን ነው ስታቲስቲክሱ የሚያሳየው” ሲሉ፤ የሀገሪቱ መሪ “የግድግዳውን ስታቲክስ አይተናል፡፡ የመሬቱን ንገሩኝ፡፡
ገበያው ጋ ሄደን እህሉ መኖሩን አሳዩኝ!” አሉ ይባላል፡፡
በልተን ለማደር ችለናል ወይ? እንደ ማለት ነው፡፡
የኑሮ ውድነትን መባባስ ለማየት አውዳመቶቹን መመርመር ነው፡፡ የጉራጌው ተረት ሁሉንም ይቋጨዋል:-
“ጅቡን የወጋኸው ምኑን ነው? ቢሉት፤ አፉን አለ፡፡ አፉን ከወጋኸውማ አሰፋኸው!”

Read 8400 times