Monday, 03 June 2019 15:52

“የይቅርታ ጫፍ!” በለቅሶ ድንኳን ውስጥ!

Written by  ደ.በ
Rate this item
(8 votes)

   ድሬደዋ በዓመት የተወሰኑ ቀናት ቢዘንብ እንኳ፣ እንደዚህ የከበደና ከተማውን ያጨለመ ዝናብ ታይቶም አይታወቅ፡፡ ሰው ሁሉ ግራ ተጋባ፣ ሀዘንተኛው የሚለው ጠፋው፡፡ አንዳች እርም ነገር ያለበት፣ ጠማማ ሰው ቢሆን - ምናልባት ፈጣሪም ቁጣውን ሊያሳይ ነው ይባል ነበር፡፡ ደግሞስ ድሬዳዋ ገብቶ እኛሁን ሳይነቅል፣ አውሬነቱን ሳይጥል የሚወጣ የታለና፡- ድሬዳዋ እንደ አሜሪካ ናት፡፡ ሰው ሁሉ ከያገሩ ይዞት የመጣውን መሰሪነትና ጠማማነት፣ በዚያች ከተማ እህል ውሃ ታጥቦ፣ በሽንቱም በላቡም ይወጣለትና እንዳገሬው ሰው ገራምና ደግ ይሆናል፡፡
የሰላማዊት እናትም ያው የድሬደዋ ሰው ናቸው:: ገደቆሬ ተወልደው ከዚራ ያደጉ፡፡ ታዲያ የእኒህ ደግ ሴት ቀብር እንዲያምር፣ ዝናቡ ለምን አልቆም አለ? ሰላማዊት ዝናብ እየዘነበ፣ የርሷም ጉንጮች ላይ እንባዋ እንዳይዘንብ አልከለከለችውም፤ “እማ ገመናዬ!!... እማዬ ጓዳዬ!” ትላለች፡፡
ከፊሉ ሰው እርሷን እያየ አብሯት ያለቅሳል:: ሌላው ደግሞ እንዳታለቅስ የቆ የባጡን ያወራል:: “ተዪ-- የእግዜርን ዐይን አትውጊ! ስንት ወጣት ባጭር በሚቀጭበት ሀገር! … ስንቱ ሞቶ አስከሬን በሚቃጠልበት ዘመን … በቃ አስታምመሻል … በቃ!”
እርሷ ግን ትንሽ እንደማቆም ትልና፤ “እማ አጋለጥሺኝ … እማዬ ገመናዬን … ገለጥሺው!” እያለች ትቀጥላለች፡፡
ቤቱ ሰው በሰው ሆኗል፣ ድንኳኑም በሰው ታጭቋል፡፡ የእናቷ ልከኛ ቪላ ቤት፣ ሰርክም ሰው አያጣም፡፡ ጎረቤት እንደ ቤቱ ገብቶ በልቶ የሚጠጣበት ቤት ነው፡፡ ይህ ቀድሞ የነበረ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በሙስሊም ፆም፣ ጎረቤቶቻቸውን ሾርባ ሰርተው፣ ሳንቡሳ ቴምር ገዝተው፣ ቤታቸው ይጋብዙ ነበር፡፡ ደግ ሴት ነበሩ፡፡ ጨዋታስ ሲያውቁበት!
“ጉድ አደረግሺኝ! ጉድ አደረግሺኝ!”
ለቅሶው መሀል የስምንት ዓመት ልጇ ስልኳን ይዛ እየሮጠች መጣ፤ “እማዬ ስልክ?”
ቁጥሩን አየት አድርጋ፤ “ሄሎ! … ሄሎ! እንዴት ነህ!” ድምፅዋ ተለውጧል
“እንደዚህ ራስሽን አትጉጂ! … የናንተ ሀገር ሰው ልቅሶ ያበዛል!” አላት
“እናቴ ኮ ናት! …” አለች፤ ለስለስ ብላ፡፡
ብዙ ዐይኖች ወደርሷ አፍጥጠዋል፡፡ አንዳች ነገር ቀይ ፊቷ ላይ ማንበብ ከጅለዋል፡፡ ቀጥ ብሎ ቁልቁል የወረደው አፍንጫዋን፣ አስሬ ስታልበው ሳያቋርጡ ያያሉ፡፡ ለጊዜው እነርሱም ለቅሶውን አቁመዋል፡፡
“የናንተ ሀገር ሰው ልቅሶ የሚያበዛው በቁም ስለማይረዳ ነው፤ ፀፀት ነው!” ይላታል፡፡
“አንቺ ግን እናትሽን የምትችይውን ሁሉ አድርገሽላታል፤ በቃ ያለ ነው፡፡ በርግጥ ጌጡ ልዩ ሰው ነበረች፤ ግን በቃ ፈጣሪ ደግ ሰው አይሞትም! ወይም ዕድሜ ይጠግባል” አላለም፡፡ ብዙ ደግ ሰዎች ያለ ዕድሜያቸው እንደተቀጩ ቅዱስ መጽሐፍም ይናገራል፡፡ የማቱሳላን እድሜ አልመኝላቸውም!” ሲላት የወትሮ ንግግሩ ትዝ አላትና ወደ ሳቅ ልትገባ ነበር፡፡ ደስ ሲለው የሀገሩ ደራስያን መጽሀፍት ውስጥ ያሉትን ገፀ ባህርያት ህይወት ሊጠቅስላት ይችላል ወይም ከሼክስፒር ቴአትር፣ አሊያም ከጆን ሚልተን ስንኞች፣ ከጆን ኪትስ ሶኔቶች … ፀባዩን ስለምታውቅ ገርሟት ዘጋችው፡፡ ይልቅስ ቀን ስለሆነ፣ እናቷንም አንድ ሁለቴ መጥቶ ስላገኛቸው በሀዘን የሚሰበር መስሏት በነበር፡፡ … የፈረንጅ ነገር! ብላ ዝም አለችው፡፡ ሰባት ዓመት ሙሉ አብረው ኑው፣ ፀባዩ ለምን እንደገረማት ራስዋን ገረማት፡፡
ከአሁን በኋላ ምን ዓይነት ህይወት፣ ምን ዓይነት ትዳር ይኖራቸው እንደሆነ እያለመች ወደ ልቅሶው ገባች፡፡ እናትዋን የሚያውቁ በዝምድና የሚገናኙ፣ ጎረቤት ሆነው ብዙ ዓመታት ያሳለፉ ሁሉ እያለቀሱ ይገባሉ፡፡ አንዳንዶቹ ለእርሷ ብሰው ስለሚያለቅሱ እንዲተዉ ይለመናሉ፡፡ በዚያ ዝናብ፣ በዞያ ዶፍ ውስጥ እንኳ የልቅስተኛው ቁጥር እየጨመረ መሄዱን አላቋረጠም ነበር፡፡ ወንዱም ሴቱም እያለቀሰ፣ ወይም አንገቱን ዝቅ እንዳደረገ ይገባል፡፡
በውጭ ስንዴ ለቀማው፣ ድስት መጣዱ፣ የተለያየ ነገር ማዘጋጀቱ ለእድር ብቻ አልተተወም፡፡ ወንዱ እንጨት ፈለጣ፣ ሴቱ ማዕድ ቤትና እልፍኝ ውስጥ ስራውን ቀጥሏል፡፡ በሞቃቱ ወራት ቢሆን ብዙ ነገሩ ከባድ ይሆን ነበር፡-
ዝናቡ ቀስ እያለ ሲያባራ የቀብሩ ጉዳይ የማይቀር ሆነ፡፡ እዚያም በተመሳሳይ የሚያለቅሰው አልቅሶ፣ ዝም ብሎ ሀዘኑን በሆዱ የያዘውም ይዞ፣ ቀሳውስቱ የቀብሩን ስነ ስርዐት አስፈፅመው ተመለሱ፡፡ አሁን ፈተናው የሰላማዊት የብቻዋ ነበር፡፡ ከባለቤትዋ ጋር ስላላት የትዳር ጉዞ ማሰብ፣ ማውጣት፣ ማውረድና መወሰን አለባት፡፡ እናትዋ ጋ የሚኖሩትን ሁለት ልጆቿን ጉዳይ ምን እንደምታደርግ ግራ ገብቷታል:: ባለቤትዋ የማያውቀው የሁለት ልጇቿ ጉዳይ፣ አደባባይ የሚሰጣበት፣ገመናዋ የሚወጣበት ቀን እየደረሰ ነው፡፡
ባልዋ የምድር ባቡር ሰራተኛ ሆኖ ድሬደዋ ሲሰራ፣ ራስዋን እንደ ልጆች እናት አድርጋ ስላልነገረችው ግር ብሏታል፡፡ ሁለት ጓደኞቿ ለባሎቻቸው ሳይነግሩ አግብተው፣ በመጨረሻ ነገሩ ሲገለጥ የደረሰባቸውን አበሳ ታስታውሳለች፡፡ ሁለቱም በባሎቻቸው ተደብድበው፣ ንብረታቸውን ተነጥቀው ተሰኝተዋል:: “አታለልሺኝ” የሚል ሙሾ ተሟሽቶባቸዋል፡፡ ለዚያውም የእነርሱ አንድ ልጅ ነው፡፡
“እማዬ ገመናዬን ዘረገፍሺው!” አለች፤ አመለጣትና፡፡
ብዙ ሰዎች ኑሮዋ ለንደን መሆኑንና ፈረንጅ ባል እንዳላት እንጂ ሌላ ብዙ ነገር አያውቁም፡፡ ሁሉንም  የሚያውቁት እርሷና እናቷ  ናቸው፡፡ ፈረንጁ ሁለት ጊዜ ከእርሷ ጋር ሲመጣ፣ ልጆቿን ጅጅጋ ያሉት አክስቷ ጋ አስቀምጣቸው ነበር፡፡ ደግነቱ ትምህርት ቤት ተዘግቶ ስለነበረ ብዙም አላስጨነቃት፡፡ ጊዜውን በክረምት ያደረገችውም አውቃ ነበር፡፡ አሁን ግን ልጆቿን ለማን ጥላ፣ በምን አንጀቷ ትኖራለች! … ያበጠው ይፈንዳ! … ፈረንጁ ከእነ ልጆቿ ከተቀበላት ተቀባለት፡፡ አለዚያም አንደ ሁኔታው ትኖራለች፡፡ ግን ያዝንባታል፣ ያሸማቅቃታል፡፡
በዚህ ዓይነት መሳቀቅ ከቆየች በኋላ አጅሬው ከተፍ አለ፡፡ ከአየር ማረፊያ፣ ወደ ቤታቸው ሲመጣ፣ ትንሽም አልተደናገረም፡፡
በሚገባ ተቀበለችው፡፡ እርሱም “መጽሀፍቱን፣ ቅዱሱን እርኩሱን እየጠቀሰ ሊያፅናናት ሞከረ:: አንዳንዴ የሚጠቅሳትን ሀሳብ ጠቀሰላት፤ በጥሩ ጊዜ ስለ paygmalion አወራት፡፡ ዕድለኛው የግሪክ ንጉስ አፈታሪክ፡፡ አንዲት ቆንጆ ልጅ ሀውልት አድርጎ ሰርቶ፣ ያችን ደረቅ ሀውልት ላይ ያያትን የራሱን ፍጡር ቢያደንቅ፣ የፍቅር አምላክ የምትባለው አፍሮዳይት ህይወት ዘራችባትና ሚስቱ አድርጓት፣ በተድላ ስለኖረው ዕድለኛም ቆጥሮ ነገራት፡፡ ራሱን እንደ ዕድለኛ ቆጥሮ፣ከራሱን ጋር ሊያወዳድረው ሞከረ፡፡
ዛሬ ይህንን ለምን እንዳነሳበት ባታውቅም ውስጧ እየተናጠ፣ ነፍሷ ባንዳች ሞገድ እየተናወጠ ነበረ:: አሁን ግን የቁርጡ ሰዓት እየመጣ ነው:: ከጎረቤት ያሉትን አንድ የዕድሜ ባለፀጋ መምህር አስቀምጣ፣ ከዚህ ቀደም ልጆች እንዳሏት ሳትነግረው ስለ ፈፀመችው ጋብቻ መፀፀቷን ልትገልጽለት አሰበች፣ ከዚያም ወደ መኝታ ክፍል አስገብታው ልትወጣ ስትል፣ አፈፍ አድርጎ ያዛት፡፡ ከጎረቤት ሰው ልትጠራ እንዳሰበች ነገረችው፡፡
“አያስፈልግም! … አያስፈልግም!”
ደነገጠች፡፡
“እኔ ፕያግማሊን ነኝ፤ ዕድለኛ ነኝ ብዬሻለሁ!”
ግራ ተጋባች፡፡
“አንቺን በመምረጤ ዕድለኛ ነኝ፡፡ አደራሽን! አንቺ ግን ራስሽን እንደ ፍራንካንስቴን አትቁጠሪ!”
ምን ማለቱ እንደሆነ ቀድሞም ታውቀዋለች፡፡ ሰው ራሱ በሰራው ስራ መከራ እንደሚያይ አትቁጠሪ እያላት ነው፡፡ ይህ ፍራንካንስቴን የሼሌ ገፀ ባህሪ ነው፡፡ የሜዲካል ኮሌጅ ተማሪ ፈጥሮት፣ ፈጣሪውን የገደለ፣ ህይወቱን የበላ ገፀ ባህሪ! ተገረመች፡፡ ራስሽን ዕድለ ቢስ አታድርጊ እያላት ነው፡፡
“Keep up our pious love!”
ድንቄም አለች፡፡
ስሚኝ “ሁለቱን ልጆችሽን አምጫቸው፣ ካገባሁሽ ቀን ይልቅ፣ የወደድኩሽ ዛሬ ነው፡፡ አንቺ ድንቅ ሴት መሆንሽ ዛሬ ከአየር ማረፊያ ስመጣ ነው የሰማሁት! ዛሬ የእናትሽ ልቅሶ ላይ ባትሆኚ፣ ሼሌ ገዝቼ ደግሜ እሞሽርሻለሁ!
ሰላማዊት ድንገት መሬት ምንጣፉ ላይ ወደቀች፡፡
“እኔን ስለምታፈቅሪኝ፣ እኔን ከማጣት ይልቅ የምትወጃቸውን ሁለት ልጆችሽን ህይወት፣ ለኔ ለጣዖትሽ ሰዋሽ!! ፍቅር ከዚህ በላይ የሚገለጥበት መስቀል የለም!” ብሏት አብሯት ዝብ አለ፡፡
ወገቧን ይዞ ሲያነሳት አዲስ የሚናኝ የፍቅር መዐዛ፣ የነፍሱን እልፍኝ እያላወሰው ነበር፡፡ እርሷ በጉንጯ ከሚወርደው እንባ በቀር ቃል አልነበራትም፡፡  

Read 3045 times