Monday, 03 June 2019 15:32

የእንስቶቹ የስኬት ታሪክ - (በራሳቸው አንደበት)

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 “በተሰማራሁበት ዘርፍ ትልቅ ደረጃ ላይ እደርሳለሁ”
                        ማርታ ከበደ


            ማርታ ከበደ እባላለሁ፡፡ የአዳማ ነዋሪና የአምስት ልጆች እናት ነኝ፡፡ በራሴ ተነሳሽነት ከትንሽ ንግድ ተነስቼ ስፍጨረጨር ነበር፡፡ የሴቶች ኢንተርፕሪነርሽፕ ፕሮጀክትን አግኝቼ ሥልጠና ከወሰድኩ በኋላ በብድር ታግዤ፣ ንግዴን በማስፋፋት፣ በአሁኑ ሰዓት፣ የጋርመንት ማምረቻና መሸጫ እንዲሁም “ማርይዛ” የተሰኘ የፋሽን ዲዛይን ማሰልጠኛ ባለቤት ነኝ፡፡ ከዘጠኝ ዓመት እድሜዬ ጀምሮ በእጅ ስራ ጥበብ ሙያ ውስጥ የቆየሁ ሲሆን ሙያው በውስጤ እንዲሰርጽ ያደረገችው የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት መምህሬ ናት፡፡
ከምንም ተነስቼ፣ እችላለሁ ብዬ ታትሬ በመስራት፣ በአሁኑ ሰዓት በ “ማርይዛ” ፋሽን ዲዛይን ማሰልጠኛ ተቋሜ ውስጥ በደረጃ 1 እና በደረጃ 2፣ በሁለት ፈረቃዎች፣ በአንድ መምህር እገዛ አስተምራለሁ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ያሰለጠናቸውን 55 ያህል ተማሪዎች ለፈተና ለማቅረብ እየተሰናዳን ሲሆን እነዚህን ተማሪዎች በማህበር በማደራጀትና በማጠናከር፣ ከሴቶች ኢንተርፕሪነርሽፕ ልማት ፕሮጀክት ጋር ለማገናኘት አቅደናል፡፡ ከመቀጠር ይልቅ ልክ እንደኔው የራሳቸውን ንግድ እንዲመሰርቱና ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ ፍላጐት አለኝ፡፡ ለዚህም የሞራል፣ የስነ ልቦናና የትምህርት ዝግጅት ላይ ሁለንተናዊ ድጋፍ እያደረግሁላቸው እገኛለሁ፡፡
ከሴቶች ኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ፕሮጀክት፣ መጀመሪያ የተበደርኩትን ገንዘብ ከመለስኩ በኋላ በድጋሚ ተበድሬ፣ ንግዴን እያስፋፋሁና እያሳደግሁ ነው የምገኘው፡፡ በተለይ የፕሮጀክቱን ሥልጠና ካገኘሁ በኋላ የንግድ ሥራዬን በእቅድ በመምራት፣ ወጪና ገቢዬን በማስላት፣ የሰለጠነ የንግድ አሠራር ማንቀሳቀስ ጀምሬያለሁ፡፡ ፕሮጀክቱን በእጅጉ አመሰግናለሁ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ጋርመንት አመርታለሁ:: የሙሽራና የሚዜ ልብሶችን በባህላዊ ልብስ ዲዛይን አድርጌ ከመሸጥ በተጨማሪም አከራያለሁ፡፡
በቀጣይ ተጨማሪ ተማሪዎችን ለስልጠና ተቀብዬ፣ የኔን ተሞክሮ በማጋራት፣ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ እጥራለሁ፡፡ በተሰማራሁበት የጋርመንትና የፋሽን ዲዛይን ስራ፣ ትልቅ ደረጃ ላይ እንደምደርስ አምናለሁ፡፡ ለዚህም በትጋት እየሰራሁ ነው፡፡


_______________


                                    “ከ400 ብር ካፒታል ተነስቼ 7 ሚ.ብር ደርሻለሁ”
                                         አባይ ተክሉ

           አባይ ተክሉ እባላለሁ፤ የአዳማ ከተማ ነዋሪ ነኝ፡፡ ከ6 ዓመት በፊት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሳለሁ ለሚገጥመኝ የገንዘብ እጥረት እጅ አልሰጥም ብዬ፤ በ400 ብር የባልትና ውጤት ሥራ ጀመርኩ:: ከዩኒቨርስቲ ከትምህርቴ ጐን ለጐን፣ የባልትና ውጤቶችን እያዘጋጀሁ በመሸጥ፣ በትንሹ የጀመርኩት ሥራ ነው ዛሬ እዚህ ውጤት ላይ ያደረሰኝ፡፡ ሥራ በጣም እወዳለሁ፤ ዋናው መለያዬ ሥራ ነው፡፡ ሥራ ጓደኛዬም ነው፤ በአጠቃላይ ሁሉ ነገሬ ነው ማለት እችላለሁ፡፡
በ400 ብር  አተር ክክ በማስከካት የጀመርኩት የባልትና ውጤት፤ አሁን አጠቃላይ ካፒታሉ ወደ 7 ሚ. ብር አድጓል፡፡ በእርግጥ ይህ ስኬት በእኔ ጥረት ብቻ የመጣ አይደም፤ የባለቤቴ የአቶ ካሳሁን ንጉሴም እንጂ፡፡ ባለቤቴ ከፍተኛ እገዛ ያደርግልኛል:: ሴቶች እንደኔ ውጤታማነቸው እንዲሰምርና መንፈሰ ጠንካራ እንዲሆኑ፣ ባሎቻቸው ራዕያቸውን በመደገፍ፣ ያልተቆጠበ እገዛ ሊያደርጉላቸው ይገባል::
ከፕሮጀክቱ ያገኘሁትን ሥልጠናና ብድር በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋሌ፣ ለስኬቴ አንዱና ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ በእኔ አስተሳሰብ ገንዘብ ብቻውን ውጤታማ አያደርግም፤ የስራ ትጋትና አርቆ አሳቢነትም ጭምር እንጂ፡፡ ከባሌ ጋር የሥራ እቅድ አዘጋጅቼ ነው ከፕሮጀክቱ ለመጀመሪያ ጊዜ 300ሺህ ብር የተበደርኩት፡፡  በዚህ ገንዘብ እቃ ገዛዝተን ስራችንን አስፋፋንበት፡፡ ብድራችንን በሶስት አመት ውስጥ መመለስ ሲገባን፣ እኛ በአንድ አመት ውስጥ መልሰን፣ በድጋሚ 1 ሚሊዮን ብር ተበደርን፡፡ ይህንንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰርተን እንደምንመልስ እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሴቶች እምቅ አቅም አለን፤ እንችላለን ብለን ከተነሳን የማናሳካው ነገር የለም፡፡ ዋናው ነገር ግን በራስ መተማመንን ማሳደግ ብቻ ነው፡፡ ከራሴ ተሞክሮ በመነሳት ሴቶችን የምመክረው፤ በራስ መተማመናቸውንና የመንፈስ ጥንካሬያቸውን እንዲያሳድጉ ነው፡፡ አንድ ሰው መንፈሰ ጠንካራ ከሆነ ማንኛውንም ስራ ማሳካት ይችላል፡፡ አንድን ሥራ ሲያስቡ ገንዘብ ብቻ ማሰብ የለባቸውም፤ ትኩረታቸው የሥራው ፍቅር ላይ መሆን አለበት:: ከዛ በኋላ ነው ብር የሚመጣው፤ ስለዚህ እህቶቼ በዚህ መንፈስ ራሳቸውን አዘጋጅተው፣ ከገንዘብ ችግር፣ ከጥገኝነትና ከጠባቂነት በመውጣት፣ ራሳቸውን ባለሀብት ስራ ፈጣሪ አድርገው፣ ለሌሎችም እንጀራ የሚያበሉ መሆን እንዲችሉ እመክራቸዋለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሁለንተናዊ ድጋፍ ላደረገልኝ ለሴቶች ኢንተርፕሪነርሽፕ ልማት ፕሮጀክት እንዲሁም የተቀጠረበትን ሥራ ትቶ ከጐኔ በመሆን፣ እኔን አምኖ አብሮኝ በመስራት፣ ለውጤት ያበቃኝን፣ ባለቤቴን አቶ ካሳሁን ንጉሴን በጣም አመሰግናለሁ፡፡


_______________________



                              “ወደ ወተት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ለማደግ እቅድ አለኝ”
                                     ብርቱካን ጥሩነህ


            ብርቱካን ጥሩነህ እባላለሁ፡፡ የአዳማ ከተማ ነዋሪ ስሆን የተሰማራሁበት የስራ ዘርፍ፣ የከብቶች እርባታ ነው፡፡ ከብቶች የማረባበት ቦታ ጠባብ ቢሆንም በጥሩ ስራ ላይ እገኛለሁ፡፡ ስራውን ከስድስት አመት በፊት በአንዲት ላም ነው የጀመርኩት፡፡ በነገራችን ላይ ያቺ ላም የሀበሻ ነበረች፡፡ የገዛኋትም ልጄ ታሞ ወተት ያስፈልገዋል ሲባል ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ከሥራው መውጣት አልቻልኩም፡፡ መጀመሪያ ግን ሽሮ ቤት ከፍቼ ስሰራ ነበር፡፡ ያቺን  የወተት ላም በልጄ ሰበብ  ከገዛሁ በኋላ ሥራው እያጓጓኝ ስለመጣ ወደ ፈረንጅ ላም ቀየርኳት፡፡ ከዚያም የሴቶች ኢንተርፕሪነርሽፕ ልማት ፕሮጀክት ሲመጣ፣ ስልጠና ወስጄ፤ ካርታና ፕላን ሰው አስይዞልኝ፣ 100ሺህ ብር ተበደርኩ:: ብድሩን ስወስድ ያለኝ ሃብት፣ 20 ሺህ ብር የተገመተች አንዲት ላም ብቻ ነበር፡፡
የምሰራው በዘልማድ ስለነበር ብዙ ውጣ ውረድና ችግሮች ገጥመውኛል፡፡ ሁለት ላሞችም ሞተውብኛል፡፡ ብድሩን ለመመለስ ገበያ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር፡፡ አሁን ግን ምርጥ ዘሮችን በማግኘት በእንክብካቤና ከብቶቹን በአመጋገብም በኩል የተሻልኩ ስለሆንኩ ውጤታማ ሆኛለሁ:: ቶ ለመመለስ ገበያ ማግኘት ሪ ነበር፡፡ አሁን እያንዳንቸው 60ሺህ ብር የሚያወጡ 13 ላሞች፣ ሰባት ጥጆች፣ 11 በጐች አሉኝ፡፡ እንግዲህ ይሄ ወደ ገንዘብ ሲቀየር ወደ 800ሺህ ብር ይደርሳል፡፡ በ2007 ዓ.ም ፕሮጀክቱ አጫጭር ስልጠና ሰጥቶናል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን የሁለተኛ አመት የሌቭል ተማሪ ነኝ፡፡ በራሴ ሳይንሱን እየተማርኩት ነው፡፡ የእንስሳት እንክብካቤና ህክምናን እንዲሁም አጠቃላይ የእንስሳት ፋርሚንጉን ሁኔታ እየተማርኩት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ለእርባታውና ለስራው አሁን ያለኝ ግቢ እጥፉም የሚበቃኝ አይመስለኝም፡፡
የበለጠ እንድተጋና ሥራዬ እንዲደላደል አቅም የሆነኝ “ወሳሳ” የተባለ የፋይናንስ ተቋም ሲሆን ያለ ማስያዣ (ኮላተራል) የ250 ሺህ ብር ብድር ሰጥቶኛል፡፡ አሁን እሱን እየከፈልኩ ነው:: የከተማው ግብርና ቢሮ ክትትል እያደረገልኝ፣ ራሴም በደንበኝነት የምይዛቸው የእንስሳት ሀኪሞች እያገዙኝ ጥሩ እየሰራሁ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት 90 ሊትር ወተት በቀን እያለብኩ፣ ወደ 2ሺህ ብር የቀን ገቢ አለኝ፡፡ ሆኖም የመኖ  ዋጋ ማሻቀብና የገበያ ትስስር ማጣት  ፈተና ሆኖብኛል፡፡
አሁን የገጠመኝ ፈተና የገበያ ትስስር ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ በአብይ ፆም ወቅት ወተት የሚጠጣ ሰው በመቀነሱ ወተት ሲደፋ ነው የቆየው፡፡ ባንክ የሚከፈል እንኳን ጠፍቶ ለመጠባበቂያ ብዬ ያስቀመጥኩትን ነው አሟጥጬ ስከፍል የነበረው፡፡ ትልቁ ችግር የመኖ አቅርቦትና የገበያ ትስስር ነው:: እርግጥ በ “ወሳሳ” በኩል ከአንድም ሁለቴ ስልጠና ወስጄ ነው ብድር የወሰድኩት፡፡ ስልጠናው ጠቃሚ ነው፡፡
ወደፊት የወተት ማቀነባበሪያ ድርጅት የማቋቋም ህልም አለኝ፡፡ ከዚያ በፊት ግን የላሞቹን ቁጥር ማሳደግ እፈልጋለሁ፡፡ አሁን ያሉት እንኳን እንደምታዩት ተፋፍገው ነው፡፡ ወደፊት መሬት ተፈቅዶልኝ ሥራዬን አስፋፍቼ ለመስራት እፈልጋለሁ፡፡ እስካሁን ለተደረገልኝ ድጋፍ ስልጠናና የገንዘብ ብድር፤ ፕሮጀክቱን አመሰግናለሁ፡፡ ሌሎች ሴቶችም የዚህ እድል ተጠቃሚ ቢሆኑ ምኞቴ ነው፡፡



Read 1606 times