Sunday, 02 June 2019 00:00

ሳይላጥ ‘የሚያስለቅስ’ ሽንኩርት… ‘ኦንሊ ኢን ኢትዮጵያ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 “እናላችሁ… እንደ ወዳጃችን ሁሉ ያልተረጋገጡ የወሬ ምንጮች እንደሚሉት፤ አዲስ በመቋቋም ላይ ላሉ ‘ፖለቲካ ፓርቲዎች’ ምልመላው የዋዛ አይደለም ይባላል፡፡ ያሉት
አልበቁን ይመስል! (እነ እንትና... ‘ዘ ፖለቲካል ፓርቲ ቱ ኤንድ ኦል ፖለቲካል ፓርቲስ’ የሚል ነገር ትዝ ካላችሁ፣ ‘ጊቭ ሚ ኤ ኮል’ ቂ…ቂ…ቂ…»
  

           እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ባል ከሥራ ወይ ከሆነ ስፍራ ይመለሳል፡፡ እናም…ሚስት ምግብ ታቀርባለች፡፡ አንድ ጊዜ ይጎርስና ፊቱን ያጨማድዳል፡፡
“ይሄ ምንድነው?” ይቆጣል፡፡
“ይሄ ምንድነው ማለት…”
“ይሄንን…ይሄንን… ወጥ ብለሽ ነው ያቀረብሽልኝ!”
“ደግሞ ምን ሆነ ልትል ነው? ስማ… እኔ ልጅት ሆኜ ነው…ሰዉ ይሄም እየናፈቀው ነው፡፡”
“አንድ ራስ ሽንኩርት የሌለው ነገር ወጥ ብለሽ ታቀርቢልኛለሽ! አንደኛውን በሹሮ የተሠራ ሙቅ ነው አትዪኝም!” (ኸረ ተው ግፍ ይቆጥርብሀል!)
“ስንት ራስ ሽንኩርት ነበር የፈለግኸው ጌታው! አስር ራስ?”
“ምን አለ ትንሽ ለዓይን እንኳን የሚሆን…”
“አይ በቃ! ስማ ሽንኩርቱ አልታይ ካለህ በአጉሊ መነጽር ፈልገው፡፡ ይሄ ምን ይላል! አንድ ኪሎ ሽንኩርት ሀያ አምስት ብር ገብቶ፣ አጅሬው ጭራሽ የሽንኩርት ንፍሮ አማረህ!”
እናማ...አለ አይደል…ከአሁኑ በሆነ ዘዴ “ሹሮ ‘ማይነስ’ ሽንኩርት” አይነት ምግብ ሼፎቻችን ይፍጠሩልንማ፡፡ ምን ያሳዝናል አትሉኝም…ይሄ ሁሉ ጩኸት፣ ይሄ ሁሉ መማረር ማሰወገድ አንኳን ባይቻል ለመቀነስ ሙከራ የሚመሰል ነገር እንኳን ለማየት አለመቻላችን፡፡ የገደል ማሚቶአችንን ራሳችን ‘እየሰማነው’ ነው፡፡ እኛው ተናግረን እኛው ብቻ አድማጭ ከሆንን ችግር አለ ማለት ነው፡፡ ችግርማ በሽበሽ ነው፡፡
እኔ ምለው…ይህ ሁሉ ፖለቲካኛ፣ ይህ ሁሉ ተንታኝ/ኤክስፐርት ምናምን የሚባለው ምነዋ በኑሮ ውድነት አበሳውን እያየ ያለውን ህዝብ የሚታደግ አማራጭ ይዞ መምጣት ተሳነው! አሀ… ይሄ ሁሉ ፖለቲከኛና ‘አክቲቪስት’ በቀን አምስቴም ሰባቴም ተመግቦ መጨረሻ (በ‘ክላማይክሱ’ እንዲሉ ጸሀፊዎች…) በዮሀንስ አራምዴ… (ያውም በ‘ብላኩ!’ ቂ…ቂ…ቂ… እሱኛው ነው ወደድ የሚለው…አይደል! አጄንዳ ፈጠርኩ ማለት ነው…ዘንድሮ ‘አጄንዳ’ የማይሆን ‘ነገር’ የለም ብዬ ነው፡…) በዮሀንስ አራምዴ… ካወራረደ በቃ አለቀ ማለት ነው! ምን መሰላችሁ… የዘንድሮ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች በየሆቴሉ ‘እግራቸውን ሰቅለው’ (የአነጋገር ዘይቤ ነገር ነው…) ይቀለባሉ የሚል ሀሜት ቢጤ ስለምንሰማ ነው፡፡ እውነት ነው አንዴ!? ኮሚክ እኮ ነው… በባለአራትና በባለአምስት ኮከብ ሆቴል ‘ፏ’ እያሉ ‘ሪቮሊሲዮን’ ምናምን ማካሄድ ከአፍሪካና ከዓለም ብቻ ሳይሆን ከዩኒቨርሱም አንደኛ ሳያደርገን አይቀርም፡፡)
እናላችሁ… ኑሮ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በአንድ በኩል ፈራንካው የለ፣ በሌላው በኩል እምነት የለ፣ በሌላው በኩል ባህሪው የለ፣ በሌላው በኩል “አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ” ብሎ ነገር የለ! አንድ እንጀራ ገዝቼ ቁርስና ምሳ አደርጋታለሁ ብሎ ነገር አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በአንድ በኩል የምግብ ‘ጎሪላ ፋይተርስ’ ምናምን የመሰሉት እነ ጄሶ ምናምን አሉ፤ በሌላ በኩል ዘንድሮ አንድ እንጀራ የቀድሞውን እንጎቻ ሊሆን ምንም አልቀረው፡፡ (“ዳቦ ላይ ያለው የግዴታ የግራም ሚዛን ለእንጀራውም ይደረግለን!” የሚለውን መፈክር መጠቀም የሚፈልግ፣ የኮፒራይት ጭቅጭቅ አይኖርም፡፡)
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ ይቺን ስሙኛማ…አንድ ትንሽዬ ልጅ መቶ ዶላር ፈለገና ሁለት ሳምንታት ሙሉ በየቀኑ ቢጸልይ ምንም ማግኘት አልቻለም፡፡ ከዛም…“ፈጣሪ ሆይ መቶ ዶላር ላክልኝ…” የሚል ደብዳቤ በቀጥታ ለፈጣሪ ላከ፡፡ የፖስታ ቤቱ ሠራተኞች፤ ለፈጣሪ የተላከውን ደብዳቤ ሲመለከቱ ተገርመው ለፕሬዚደንት ክሊንተን ሊልኩት ወሰኑ፡፡ ፕሬዚደንቱ ደብዳቤውን ሲያነቡ ስሜታቸው ተነካ፡፡ ጸሀፊያቸውንም አምስት ዶላር እንድትልክለት ነገሯት፡፡ አምስት ዶላር ለልጁ ብዙ ይሆናል ብለው አስበው ነው፡፡ ልጁም አምስት ዶላር በማግኘቱ ተደሰተ፤ ተቀመጠናም የምስጋና ደብዳቤ ጻፈ፡፡ “ፈጣሪ ሆይ ገንዘቡን ስለላክልኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ግን በሆነ ምክንያት ገንዘቡን የላክልኝ በዋሺንግተን ዲሲ በኩል ነው፡፡ እነኛ ሌቦች ዘጠና አምስት ብሩን ቀንሰው ነው የላኩልኝ” አለ አሉ፡፡
ገንዘባችን በምንና በምን እየተቀናነሰ እንደሚሄድ ግራ የሚገባን ጊዜ አለ ለማለት ያህል ነው፡፡
ቀባጥሮም ቀምቶ በሀሰት ነግዶ
ከክብሩ አብልጦ ገንዘብ በጣም ወዶ
ብዙ ሰው ይኖራል ራሱን አዋርዶ
ብለዋል ከበደ ሚካኤል…ያንና ጊዜ፡፡ አሁን ያለንበትን ቢያዩ ኖሮ ምን ይሉ ነበር!
ታዲያላችሁ …መቼም ማናችንም ገንዘብ እንፈልጋለን፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ኑሮ በየቀኑ ከድጡ ወደ ማጡ በሆነበት… እያንዳንዷ ሳንቲም ብትናፍቀን አይገርምም፡፡ ግን ደግሞ ሌላው አንዴ ሲጎርስ እኛ ሦስቴ ከመጉረስ አይነት ‘ተራ ግለኝነት’ በእጅጉ ተሻግሮ ቀይ መስመር ወደ ሌለው ‘ስግብግብነት’ ሲገባ ደግሞ አስቸጋሪ ነው፡፡ ፈረንካው እስከተገኘ ድረስ ምንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ የማንል መበርከታችን የብዙ ችግሮቻችን ሰበብ እየሆነ ነው…‘ቦተሊካውን’ ጨምሮ ማለት ነው፡፡
የምር ግን… ምን መሰላችሁ፣ በሚገባ በተዋቀረና በተደራጀ ስርአት መመራት እየቀረ ብዙ ነገሮች በግለሰቦች ወይም በቡድኖች ፍላጎት ላይ እየተዘወሩ ባሉበት ጊዜ ጩኸታችንን የሚሰማ ቢጠፋ ምንም አይገርምም፡፡ እናማ…በትንሽ ትልቁ ጡንቻ ማሳየት የምንፈለግ አየሩን እየተቆጣጠርን ባለበት፣ መደማማጥ አስቸጋሪ ነው፡፡ አሀ…ተኩላውን ከበግ መለየት አስቸጋሪ ሆኗላ! ይሄ ደግሞ…አለ አይደል…ምን መብላት እንደምንችል፣ ምን ‘ሊበላን’ እንደሚችል ሁሉ ግራ ይገባል፡፡
ስሙኝማ …በቀደም አንድ ወዳጃችን ስለ ከተማችን አንዳንድ ነገር ‘አፕዴት’ ሲያደርገን ነበር:: እናማ…የ“ቡና እንጠጣ” ግብዣ ሁሉ ዋናው ጉዳይ ቡናው አይደለም እያለን ነበር፡፡
“ስማ አትጥፋ…”
“ምነው ቸኮልክ…ሻይ ብንጠጣስ…”
ኸረ! ሻይ እንጠጣ! አጅሬ በሻይ ሰበብ ልትጠጣኝ!
“ምን መሰለህ …አንዲት ቀጠሮ አለችኝ፣ ይረፍድብኛል፡፡”
“ትንሽ ብናወራ…ምን ችግር አለው፡፡ ደግሞ እንዳይረፍድብህ በኮንትራት ታክሲ ትሄዳለህ፡፡”
በኮንትራት ታክሲ! እኔ የምለው …አንዳንዱ እንዴት ነው እንዲህ የሚመቸው! እሱ አስራ ሰባት ቁጥርና መቶ ምናምን ቁጥር አንበሳ ላይ ለመግባት ትከሻው እስኪናጋ እየተጋፋ፣ ለአናንተ የኮንትራት ታክሲ ‘ሀሳብ’ ያቀርባል፡፡ ልክ እኮ… “ውድ ያልሆነ አሪፍ ፍርፍር የሚሸጥ ቤት ባገኝ…” ስትሉ… “የእንትና ክትፎ ቤት፣ ስፔሻል ክትፎ እንዴት እንደሚጥም አልነግርህም…” የማለት አይነት ነው፡፡
(ሰዓት እያያችሁ) “እንደውም ኦልሬዲ አስር ደቂቃ አሳልፌያለሁ፡፡”
“ትንሽ ቢጠብቁህ ምን ይሆናሉ! በስንት ጊዜ ብንገናኝ ምንድነው እንዲህ ጥድፊያው…” ከተገናችሁ ገና ሶሰት ቀናችሁ እኮ ነው!
ይሄኔ ነው ‘ጠርጥር’ ጂኖች ሥራቸውን የሚጀምሩት፡፡ “አጅሬ ሌላ ነገር አስቧል ማለት ነው!” ወዲያው ‘እንቆቅልሽ’ ይፈታል፡፡ “ለሆነ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመለምለኝ ፈልጎ ነው!” እናላችሁ… እንደ ወዳጃችን ሁሉ ያልተረጋገጡ የወሬ ምንጮች እንደሚሉት፤ አዲስ በመቋቋም ላይ ላሉ ‘ፖለቲካ ፓርቲዎች’ ምልመላው የዋዛ አይደለም ይባላል፡፡ ያሉት አልበቁን ይመስል!  (እነ እንትና... ‘ዘ ፖለቲካል ፓርቲ ቱ ኤንድ ኦል ፖለቲካል ፓርቲስ’ የሚል ነገር ትዝ ካላችሁ፣ ‘ጊቭ ሚ ኤ ኮል’ ቂ…ቂ…ቂ… አንዳንድ ‘ኦፊሺያል ፈረንጂኛ’ ስንሰማ፣ እኛም ያለችው ጠፍታን ‘ፕሮፋይል ፒክቸር’ ነገር እንዳንሆን ብለን ነው፡፡)
እናማ፣ በዘንድሮው ስሌት…አለ አይደል…ለስንትና ሰንት ዓመት ርቀቱን ጠብቆ ተንጠራርቶ ሲጨብጠን የነበረው ሰው፤ ድንገት አንድ ቀን ዘሎ ቢጠመጠምብን፣ ከሁለት አንድ ምክንያት ቢኖረው ነው እንላለን... ወይ “አጣዳፊ ጉዳይ ስለገጠመኝ ገንዘብ አበድረኝ” ምናምን ሊል ነው፤ ወይ ‘ሊመለምለን’ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
በዚህም፣ በዛም ኑሮ ጣራውን ቀዶ አልፎ፣ አላፈናፍን እያለን እንደሆነ ልብ ይባል፡፡ አሁን ከባድ ዝናብ ሊሆን ይችላል፣ ‘ተመልካች’ ከሌለ፣ ነገ ‘ሱናሚ’ የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡ ይሄ ደግሞ ለማንም የሚመች አይሆንም! ሽንኩርት እንኳን ‘ሳንልጠው’ እያስለቀሰን ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1693 times