Monday, 03 June 2019 15:24

ኤርሚያስ ገሠሠ ጅምና ማርሻል አርት ለ700 ነዳያን የምሳ ግብዣ አደረገ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

 የስፖርት ትምህርትና የበጐ ሥራውን  በ1995 ዓም አንድ ላይ የጀመረው ኤርሚያስ ገሠሠ ጂምና ማርሻል አርት ማዕከል (ጅት ኩን ዱ ት/ቤት)፤ ዘንድሮ ለ16ኛ ጊዜ የፋሲካን ፆም ፍቺ ምክንያት በማድረግ ከ700 በላይ ለሆኑ ነዳያን የምሳ ግብዣ አደረገ፡፡
የማርሻል አርት (ጅት ኩን ዱ)ጥበብን በማስተማር አካልና አዕምሮን አጠንክሮ፣ በሥነ ምግባር ትምህርት ፀባይን ያንፃል የሚለው የትምህርት ቤቱ መሥራችና ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ገሠሠ፤ ማርሻል አርት (ጅት ኩን ዱ) ትምህርት ደግሞ ራሳችንን እንድንሆንና ራሳችንን እንድንገልጽ ያደርጋል በማለት አስረድቷል፡፡
ባለፈው ሳምንት እሁድ በወረዳ 14 ወጣት ማዕከል መዝናኛ ውስጥ ጐዳና ላይ ላሉ ከ700 በላይ ለሚሆኑ ነዳያን የምሳ ግብዣ ያደረገው፣ አብሮ የመብላትን የኢትዮጵያውን ባህል ለመግለጽ ነው ያሉት የት/ቤቱ ኃላፊ፤ ከወረዳው ጋር በመሆን 5 ሕፃናትን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እያሉ በማስተማር፣ የበዓል ወጪያቸውን በመቻል፣ አልባሳት በመግዛት፣…የዜግነት ድርሻችንን እየተወጣን ነው ብለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ለ5 የጐዳና ተዳዳሪዎች፤ የሊስትሮ ዕቃ፣ ፌስታል፣ ማስቲካ ገዝቶ በመስጠት የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው የጠቆሙት ኃላፊው፤ በማሽን ሻይ ማፍላት የሚችል አንድ ልጅ እንዲቀጠር አድርገናል ብለዋል፡፡ የማርሻል አርት ትምህርት እንዲማሩ በማስተማርም አካላቸው በስፖርት፣ አዕምሮአቸውን በሥነ - ምግባር እንዲታገጽ አድርገና በማለት አስረድተዋል፡፡
ለምሳ ግብዣው በአጠቃላይ 30ሺ ብር ያህል ወጪ እንደተደረገ የገለፁት አቶ ኤርሚያስ፣ ወጪውም የተሸፈነው ከተማሪው ገንዘብ በመሰብሰብና የተለያዩ ድርጅቶች ባደረጉት ድጋፍ  እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

Read 2423 times