Wednesday, 05 June 2019 00:00

2.1 ሚሊዮን ዶላር የሚሸጠው የአለማችን ውዱ መድሃኒት ለገበያ ቀረበ

Written by 
Rate this item
(2 votes)


             በህጻናትና ታዳጊዎች ላይ ለሚከሰት የጀርባ አጥንት መሳሳት በሽታ ሁነኛ መፍትሄ ነው የተባለውና ዞልጄንስማ የሚል ስያሜ የተሰጠው የአለማችን እጅግ ውዱ መድሃኒት በ2.125 ሚሊዮን ዶላር ሰሞኑን ለገበያ መቅረቡን የኤስኤ ቱዴይ ዘገበ::
ከአሜሪካ የምግብና የመድሃኒት አስተዳደር ባለፈው ሳምንት እውቅና የተሰጠው ይህ መድሃኒት አንድ ጊዜ የሚወሰድ ቢሆንም ክፍያው ግን በተራዘመ የክፍያ ፕሮግራም በአራት አመት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ነው መባሉን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በአለማችን ከ11 ሺህ ህጻናት አንዱ የዚህ በሽታ ተጠቂ ሆኖ እንደሚወለድ የጠቆመው ዘገባው፣ የዚህ ችግር ሰለባ የሆኑ ህጻናት ጭንቅላታቸውን ለመሸከም፣ ምግብና መጠጥ ለመዋጥ እንዲሁም ለመተንፈስ እንደሚቸገሩና ብዙዎችም በከፋ ህመም ሲሰቃዩ ኖረው ሁለት አመት ሳይሞላቸው እንደሚሞቱ ገልጧል፡፡
መድሃኒቱ በ2.125 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሸጥ ይፋ መደረጉን ተከትሎ የመብት ተሟጋቾችና የችግሩ ሰለባ የሆኑ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን የገለጸው ዘገባው፣ መድሃኒቱን አምርቶ ለገበያ ያቀረበው ኖቫርቲስ የተባለ ኩባንያ ግን 4 ሚሊዮን ዶላር ሊሸጠው አስቦ እንደነበርና የገዢውን አቅም እንደሚፈትን በመገመት ካሰበው ዋጋ በግማሽ ቀንሶ እንዳቀረበው በመግለጽ አቤቱታውን አስተባብሏል፡፡


Read 3467 times