Sunday, 02 June 2019 00:00

የዶ/ር ካትሪን ሃምሊን ሃውልት ተመረቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)


              “እኒህ እናት ዕድለኛ እናት ናቸው፤ ለምን እንደተፈጠሩ የሚያውቁ፣ ሰው ሆነው ሰውን ያዳኑ፣ ከዘር በላይ ከቀለም በላይ፣ ከጾታ በላይ፣ ሰውነት ሰው ለማዳን መዋል እንደሚችል ያስተማሩን ጀግና ሰው ናቸው፡፡ ጀግንነት ሰው መሆን፣ ጀግንነት ሰው ማዳን እና ጀግንነት ለተረሱት መቆም መሆኑን እኒህ ሴት ባለቤታቸውና ቤተሰቦቻቸው በተግባር አሳይተውናል”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ በሃውልት ምረቃው ወቅት የተናገሩት፡፡
“የሴቶቹ ሕይወት ሲለወጥና ሲታደስ አያለሁ፡፡ ሁሌም ሃሳቤ ከነሱ ጋር ነው፤ ህመማቸው ህመሜ ነው፡፡ ይሄ ደሞ የምችለውን እንድሰራና እንዳደርግ ይገፋፋኛል፡፡ እስከዛሬ እዚህ የኖርኩትና አሁንም እዚህ የምኖረው በዚህ ምክንያት ነው”
ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን - “ተምሳሌት” ከተሰኘው መጽሃፍ የተወሰደ  


         የሃምሊን ፌስቱላ ሆስፒታል መስራች የሆኑት ዶክተር ካትሪን ሃምሊን ባለፉት 60 አመታት በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በአዲስ አበባ የተሰራላቸው ሃውልት ከትናንት በስቲያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ የተመረቀ ሲሆን፣ በፊስቱላ ህክምና ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የወርቅ ሜዳልያና የእውቅና የምስክር ወረቀት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተበርክቶላቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ዶክተር ሃምሊን ለምን እንደተፈጠሩ የሚያውቁ ሰው ሆነው ሰውን ያዳኑ፤ ከዘር በላይ ከቀለም በላይ ከጾታ በላይ ሰውነት ሰው ለማዳን መዋል እንደሚችል ያስተማሩን ጀግና ሰው ናቸው ሲሉ ለዶክተር ሃምሊን ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡
“ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን እርስዎ ጉራጌ ነዎት? እርስዎ ወላይታ ነዎት? እርስዎ አማራ ነዎት? እርስዎ ኦሮሞ ነዎት? ከእኔ ዘር ውጭ ሌላ ሰው የሚሰራ የለም በሚባልበት ዘመን ከየትኛው ዘር ቢወጡ ነው እነዚህን ምስኪን የሚመለከታቸው ያጡ ሴቶች ሰብስበው አድነው ሰው ያደረጉት ከየትኛው ብሔር ወጥተው ነው?” ሲሉ የጠየቁት ጠ/ሚ አቢይ፣ ዶክተር ካትሪን ሃምሊን ለምን እንደተፈጠሩ የሚያውቁ ዕድለኛ እናት ናቸው ብለዋል፡፡“ጀግንነት ሰው መሆን፣ ጀግንነት ሰው ማዳን እና ለተረሱት መቆም መሆኑን እኒህ ሴት ባለቤታቸውና ቤተሰቦቻቸው በተግባር አሳይተውናል” ሲሉ ለዶክተር ሃምሊን ያላቸውን አድናቆት የገለጹት ዶ/ር አቢይ ከባለቤታቸው ቀዳማዊት አመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ፌስቱላ ሆስፒታል የሚገኙ ታካሚዎችን ጎብኝተዋል፡፡

Read 3383 times