Sunday, 02 June 2019 00:00

ከ1 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

ባለፉት ሁለት አመታት በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች ከተፈናቀሉ 3 ሚሊዮን ዜጐች መካከል 1.9 ሚሊዮን ያህሉ ወደ ቀዬአቸው መመለሳቸውን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ተቋም ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
ተቋሙ ከየዞኑ ባሰባሰበው መረጃ መሰረት ከምዕራብ ወለጋ ከተፈናቀሉት መካከል 97 በመቶ ያህሉ (120ሺህ ተፈናቃዮች 116ሺህ) ወደ ቀዬአቸው የተመለሱ ሲሆን፤ ከምስራቅ ወለጋ ተፈናቃዮች 84 በመቶ ያህሉ (ከ83 ሺህ ውስጥ 70ሺህ) ወደ ቀዬአቸው ተመልሰዋል፡፡
ከሱማሌ ክልል ከተፈናቀሉት 962 ሺህ ዜጐች መካል 30 በመቶ ያህሉ (287 ሺህ ያህሉ ብቻ) መመለሳቸውን እንዲሁም ከአማራ ክልል ከተፈናቀሉት ውስጥ 35 በመቶ ያህሉ (107ሺህ ዜጐች) ወደቀዬአቸው መመለሳቸውን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ ከጌድኦ እና ምዕራብ ጉጂ 35 በመቶ ያህሉ የተፈናቀሉት 1 ሚሊዮን ገደማ ዜጐች ሙሉ ለሙሉ ወደ ቀዬአቸው የተመለሱ ሲሆን ተፈናቃዮችን ሲያስተናግዱ የነበሩ መጠለያ ጣቢያዎች መዘጋታቸውንም ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከጉጂና ከጌዲኦ የተፈናቀሉ ዜጎች ከመጠለያ ጣቢያዎች ቢወጡም ገና በየአካባቢያቸው በሚገኙ ቀበሌ ጽ/ቤቶች የማቋቋሚያ ፕሮግራም እየተከናወነላቸው መሆኑን ተቋሙ አመልክቷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ባለሙያዎች ወደቀዬአቸው የተመለሱ ተፈናቃዮችን ማነጋገራቸውን የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ የወደመ ንብረታቸውን መንግስት እንዲተካላቸው መጠየቃቸውን ጠቁሟል፡፡
1.9 ሚሊዮን የተፈናቀሉ ዜጐች ባለፉት ጥቂት ወራት ወደ ቀያቸው የተመለሱ ቢሆንም አሁንም 1.1 ሚሊዮን ያህሉ በየመጠለያ ጣቢያው እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡

Read 2462 times