Sunday, 02 June 2019 00:00

የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ንረት አሳሳቢ ሆኗል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

  አንድ ኩንታል ጤፍ 3ሺ 300 ብር ደርሷል

            ጤፍን ጨምሮ የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ መጠን የናረ ሲሆን በስንዴ ዱቄት እጥረት ሳቢያም ዳቦ ቤቶች መቸገራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ላለፉት ሶስት አመታት እምብዛም ጭማሪ አሳይቶ የማያውቀው የጤፍ ዋጋ፤ ከአንድ ወር ወዲህ እየናረ መምጣቱን የሚናገሩት ሸማቾች፤ የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ በአንድ ሣምንት ውስጥ ከ2ሺህ 7 መቶ ብር ወደ 3300 ብር ማሻቀቡን ይገልፃሉ፡፡ በየአካባቢው 4 ብር እና 5 ብር ይሸጥ የነበረው የአንድ እንጀራ ዋጋ 6 ብር 7 ብር መግባቱን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
በአቃቂ ገበያ የጤፍና ስንዴ ነጋዴ የሆኑት አቶ በለጠ ባንትይገኝ ለአዲስ አድማስ እንዳስረዱት፤ “ቀደም ሲል በየጊዜው የዋጋ ጭማሪ የሚያሳዩት የአደአ ማኛ ጤፍና የምንጃር ማኛ ጤፍ ብቻ ነበሩ፤ ካለፈው ሣምንት ጀምሮ ግን በሁሉም የጤፍ አይነቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል” ብለዋል፡፡
የጤፍ ዋጋ የጨመረው ከዋና አከፋፋዮች ነው ያሉት ነጋዴው፤ ለወትሮ የጤፍ ዋጋ የሚጨምረው በክረምትና በመስከረም ወራት እንደነበር አስታውሰው፤ በዚህ ወቅት መጨመሩ ግን ያልተለመደ ነው ብለዋል፡፡
አርሶ አደሩ በታህሳስ፣ ጥርና የካቲት የተሰበሰበውን ምርት። ለማዳበሪያ መግዣ ገንዘብ ለማግኘት አውጥቶ የሚሸጥበት ወቅት በመሆኑ የእህል ዋጋ በአብዛኛው ይቀንስ ነበር ያሉት ሌላው የእህል ነጋዴ አቶ ይልማ፤  የስንዴም ሆነ የጤፍ እጥረት የተፈጠረው ከዋና አከፋፋዮች ነው ብለዋል፡፡
እስካሁን በስንዴ ዋጋ ላይ እምብዛም የዋጋ ጭማሪ አልታየም የሚሉት ነጋዴው፤ ኩንታሉ እስከ አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር እንደሚሸጥ ተናግረዋል::
በሌላ በኩል፤ ዳቦ ቤቶች፤ በስንዴ ዱቄት መጥፋት መቸገራቸውን ገልፀዋል፡፡ ገበያ ላይ የስንዴ ዱቄት በቀላሉ አይገኝም ያሉት የዳቦ ቤት ባለቤቶች፤ ችግሩ ምን እንደሆነ እነሱም እንደማያውቁት ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር በበኩሉ፤ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ የዳቦ ፋብሪካ በማቋቋም በዳቦ ገበያ ያለውን የፖለቲካ ጨዋታ እንደሚያከሽፍ አስታውቋል፡፡
በአጠቃላይ ጤፍ፣ ዳቦና ሽንኩርትን የመሳሰሉ መሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ መምጣቱን የሚገልፁት ነጋዴዎችና ሸማቾች፤ መንግስት ችግሩን እንዲፈታ ጠይቀዋል፡፡   

Read 4186 times