Sunday, 02 June 2019 00:00

ይፈርሳሉ የተባሉ “ህገ ወጥ” ቤቶች ጉዳይ ውዝግብ ፈጥሯል

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(4 votes)

  በህገ ወጥ ግንባታ የተጠረጠሩ የወረዳ ኃላፊዎችና ፖሊስ ታሰሩ
                                         
     ከ30ሺህ በላይ ህገወጥ ቤቶች በአምስት ክፍለ ከተሞች መሠራታቸውን የገለፀው የአዲስ አበባ አስተዳደር፤ በህገወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩ የፖሊስ አባላትና የወረዳ አመራሮች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ፡፡
ቤቶቹ በቦሌ፣ በየካ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶና በጉለሌ በህገወጥ መንገድ በተያዙ ቦታዎች ላይ የተገነቡ ናቸው ተብሏል፡፡ በዚህም አስተዳደሩ በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 9 ኮተቤ አካባቢ በህገወጥ መንገድ የመሬት ወረራ በማድረግ ህገወጥ ቤቶችን ገንብተዋል፤ አስገንብተዋል ብሎ የጠረጠራቸውን አራት የፖሊስ አባላትንና አንድ የወረዳውን ኃላፊ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል፡፡
በቀጣይም አስተዳደሩ በወረራው ላይ ተሳትፈው የተገኙ የመንግስት አካላት፣ ባለሀብቶችና ግለሰቦች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ተገልጿል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙሀን በሰጠው መግለጫ፤ ከ2010 ጀምሮ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ከ30ሺህ በላይ ህገወጥ የቤቶች ግንባታ በመዲናዋ መፈፀሙን ጠቁሞ በዚህ ድርጊት ውስጥ ደላላዎች፣ ባለሀብቶች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የመንግስት አስተዳደር አመራሮችና የፀጥታ ሃይሎች መሳተፋቸው መረጋገጡን አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ይፈርሳሉ የተባሉ ቤቶች ጉዳይ አሳስቦኛል ያለው በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የተቋቋመው የአዲስ አበባ ባለአደራ ም/ቤት በበኩሉ፤ መስተዳድሩ ህገወጥ ቤቶቹን ለማፍረስ የያዘው ዕቅድ ግልጽነት የጐደለው፣ ጥናት ላይ ያልተመረኮዘ የጅምላ እንቅስቃሴ ነው ብሏል፡፡ “የከተማዋ መስተዳድር የህዝብ ውክልና የሌለው በመሆኑ እስከ ቀጣዩ ምርጫ ድረስ ህግ እያስከበረ መቆየት ነው ያለበት” ይላል  - ም/ቤቱ፡፡
“አስተዳደሩ ውሣኔውን በድጋሚ ካላጤነ ተቃውሞ ሠልፍ እንጠራለን” የሚለው ባለአደራ ም/ቤቱ፤ “እኛ ባደረግነው ጥናት አብዛኞቹ ቤቶች በለፍቶ አዳሪዎች አቅም የተገነቡ እና ከአስር አመት በፊት የተሰሩ ናቸው፤ የባለሀብቶች አይደሉም” በማለት ለዚህም ማስረጃ እንዳለው ባለአደራው ይገልፃል፡፡
መስተዳደሩ ይፈርሳሉ የተባሉ ቤቶች የሚገኙባቸውን አካባቢዎች ሰሞኑን ለጋዜጤኖች አስጎብኝቷል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 9 ሠፈራ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ያገኘናት ወ/ሮ እቴነሽ ዋቅኦ፤ የሦስት ልጆች እናት ናት፡፡ ከወለጋ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ወደ አዲስ አበባ የመጣችው በ2010 ዓ.ም ነበር፡፡ በከተማው ኑሮ መወደድ፣ በደላሎች ያልተገባ ተስፋ ተገፋፍታ፣ ከገበሬ በገዛችው ሁለት መቶ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ አራት ክፍል ቤት ገንብታለች፡፡
ቤቷ ሁለት ጊዜም ህገወጥ ነው ተብሎ እንደፈረሰባት የምትናገረው እቴነሽ፤ “ህገወጥ እንደሆነ እያወቅሁ የተመቀጥኩት መሄጃ ስለሌለኝ ነው” ትላለች፡፡
ቤቱን የገዛችው በመንደር ውል በመሆኑ በወቅቱ የነበሩ ደላሎችና የቤቱ ሻጮች ጊዜውን ወደ ኋላ አድርገን እንዋዋል እንዳሏት ትናገራለች፡፡
ሰኢድ አደም የሁለት ልጆች አባት ሲሆን ስሙን የማያውቀው ግለሰብ በጓደኛው አማካኝነት ከአምስት ወር በፊት ኮተቤ አካባቢ ባለ መኖሪያ ቤቱ አስጠርቶት አሁን የሚኖርበትን ቤት እንዲጠብቅና ማንም ቢጠይቀው ቤቱ የእኔ ነው በል መባሉን ይናገራል፡፡
በርካቶቹ በአካባቢው ላይ የሰፈሩት እራሳቸው ሰርተው ሳይሆን የዕለት ችግራቸውን ለማቃለል ተጠልለው ነው የሚለው ሰኢድ እኔ ሚስቴ አራስ በመሆኗ ሳይፈርስብኝ ቀርቷል እንጂ ህገወጥ መሆኑ ተነግሮኛል ይላል፡፡
“መንግሥት ከረዳኝ እውነቱን እንናገራለን ያለው ሰኢድ ከወረዳው የሚገባልን ቃል ካለ እና ለደህንነታችን ዋስትና ከተሰጣቸው እውነቱን እንደሚናገሩ ገልጿል፡፡


Read 5412 times