Saturday, 25 May 2019 10:06

መሣሪያና ገንዘብ አዘዋዋሪዎቹ እነማን ናቸው?

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(3 votes)

 አሁንስ “Fake News” እየመሰለን ነው!
                 
           በዚች መጣጥፍ በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አደርጋለሁ፡፡ አንደኛው፤ በህገ ወጥ የጦር መሣሪያና የገንዘብ ዝውውር ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን ሁለተኛው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾሟቸውን ባለስልጣናትና ለሀገራዊ ቦርድና ኮሚቴዎች የሚመርጧቸውን አባላት ይመለከታል:: ሁለቱንም ጉዳዮች በየተራ ለማየት እሞክራለሁ፡፡
ህገ-ወጥ መሣሪያና ገንዘብ አዘዋዋሪዎቹ እነማን ናቸው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ስልጣን ከያዙ ወዲህ ባሉት ጊዜያት በመንግስት መገናኛ ብዙሃን አማካይነት ከሚተላለፉ ዜናዎች ውስጥ “በአዋሽ የጉምሩክ ፍተሻ ጣቢያ ይህን ያህል የጦር መሳሪያ ከመሰል ጥይቶች ጋር ተያዘ፡፡ በባህር ዳር ኬላ ይህን ያህል ሽጉጥ ከጎንደር ወደ መሀል አገር ሲጓጓዝ ተያዘ:: በአዲስ አበባ መግቢያ ይህን ያህል ሚሊዮን ዶላር ተያዘ…” የሚሉት ተደጋግመው ይደመጣሉ፡፡
እነዚህን ዜናዎች በተመለከተ በህብረተሰቡ ዘንድ ተደጋግመው የሚነሱት ጥያቄዎች፤ “እነዚህን የጦር መሳሪያዎች ሲያንቀሳቅሷቸው የነበሩት እነማን ናቸው? ያን ያህል መጠን ያለው የውጭ ሀገርና የኢትዮጵያ ገንዘብ ያጓጉዝ የነበረው ግለሰብ ወይም ቡድን ማን እንደሆነ ፍንጭ የለም? ገንዘቡና መሳሪያው በራሱ አቅምና ጉልበት መኪና ላይ ተጭኖ ነበር የሚጓጓዘው?...” የሚሉ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች በቂ መልስ ያላገኘው ህብረተሰብ፤ ዛሬ ዛሬ እነዚህን ዜናዎች ሲሰማ “ይሄ ነገር ‘Fake News’ (የውሸት ዜና) ይሆን እንዴ?” ማለት ጀምሯል፡፡
ወንጀልን መከላከል የፖሊስ ሥራ ብቻ አለመሆኑ ተደጋግሞ ሲነገር እንሰማለን፡፡ “በህዝብ ድጋፍ ያልታገዘ የወንጀል መከላከል ሥራ አጥጋቢ ውጤት አያስገኝም፡፡ ህዝብን ያላሳተፈ የወንጀል መከላከል እንቅስቃሴ በአንድ እጅ ማጨብጨብ ነው” ይላል ፖሊስ ራሱ፡፡ በዚህ አባባል የዚህ ጽሑፍ አቅራቢም ይስማማል፡፡ ምክንያቱም (አንድ መቶ ሚሊዮን ህዝብ በሚኖርበት ሀገር) የፖሊስ ኃይል ውሱን ስለሆነ በአንድ ጊዜ ሁሉም ስፍራ ሊገኝ አይችልም:: ህዝብ ግን በሁሉም ስፍራ ይኖራል፡፡ ህዝብ በየአካባቢው በይፋም በስውርም የሚደረገውን እንቅስቃሴ ያያል:: የሚነገረውንና የሚንሾካሾከውን ጭምር ይሰማል:: “ከህዝብ የሚሰወር ነገር የለም” የሚባለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው መንግስታዊ አሰራር፣ ህገ መንግስታዊ እውቅና የተሰጠው፣ የመንግስት ተቋማት ሊከተሉት የሚገባ የአሰራር መርህ ይመስለኛል፡፡ ይሁን እንጂ ፖሊስ ይህንን የአሰራር መርህ ወደ ጎን በመተው፣ የተጠርጣሪዎችን ማንነት በመደበቅ፣ የወንጀለኞች ጫካ መሆኑ እየተስተዋለ ነው፡፡ ፖሊስ የተጠርጣሪዎችን ማንነት ይፋ ባለማድረግ፣ የወንጀለኞች ሽፋንና ከለላ እየሆነ ነው፡፡ ለምን? በበኩሌ፤ ፖሊስ የተጠርጣሪዎችን ማንነት ይፋ የማያደርገው በሁለት ምክንያቶች ይመስለኛል:: አንደኛው ምክንያት፤ ከወንጀሉ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች እንዳይበረግጉና እንዳይሰወሩ ለማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የተጠርጣሪዎችን ሰብአዊ መብትና ክብር ለመጠበቅ በማሰብ ይመስለኛል፡፡
እንደኔ እንደኔ ሁለቱም ምክንያቶች አሳማኝ ሆነው አይታዩኝም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ፖሊስ ህዝብ የሚሳተፍበት የወንጀል መከላከል ሥራ እሰራለሁ እስካለ ድረስ “ተጠርጣሪዎች ይሰወራሉ” ብሎ መስጋት የለበትም ባይ ነኝ፡፡ ቢሰወሩም ህዝብ መንጥሮ አውጥቶ ይሰጠዋልና! በሁለተኛ ደረጃ “የተጠርጣሪዎችን ሰብአዊ መብት ለመጠበቅ” የሚለውን በተመለከተ አንድ ሰው “በወንጀል ተጠርጣሪ ነው” ማለት ቢያንስ ቢያንስ ለመጠርጠር የሚያበቃ በቂ ሁኔታ ተሟልቷል ማለት ነው፡፡ አንድን ሰው “ለመጠርጠር የሚያበቃ በቂ ሁኔታ” ከተሟላ ደግሞ፤ በበኩሌ የተጠርጣሪውን ማንነት ይፋ ማድረግ ሰብአዊ መብቱንም ሆነ ክብሩን የሚነካ ሊሆን አይችልም የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ በየትም ሀገር ተግባራዊ የሚደረግ አሰራር መሆኑንም የህግ ባለሙያዎች ጭምር የሚያውቁት ነው፡፡
ከእነዚህ እውነታዎች በተጨማሪ በበኩሌ ሁለት ተደማሪ ሀቆች ይታዩኛል፡፡ በተለይም አሁን ሀገሪቱ ካለቺበት የሰላምና የፀጥታ ስጋት አኳያ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎችንና የህገ ወጥ ገንዘብና የኮንትሮ ባንድ እቃ አሸጋጋሪ ተጠርጣሪዎችን ማንነት ይፋ በማድረግና ባለ ማድረግ መካከል ለህዝብና ለሀገር የሚያስገኘውን ጥቅምና ጉዳት መመዘን አስፈላጊ ነው፡፡ ሁለተኛ የፍትህ አካላት በፍርድ ሂደት ውሳኔ እስከሚሰጡ ድረስ (በሁሉም ጉዳዮች ሳይሆን) ወቅታዊ የህዝብ ሰላምና ደህንነት ስጋት በሆነ ወንጀል በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ ህብረተሰቡ “ኅሊናዊ የሞራል ፍርድ” የመስጠት መብት የለውም ወይ? የሚለው ጥያቄ መታየት አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡
በበኩሌ፤ የወንጀል ሰለባ የሆነ ማህበረሰብ፣ በፍርድ ቤት በሚሰጥ ፍትህ ብቻ እርካታ ያገኛል፣ ጉዳቴን ህግ ተበቀለልኝ ብሎ የእርቅ ስሜት ያድርበታል የሚል እምነት የለኝም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ማህበረሰባዊ ቁስል በፍርድ ቤት ውሳኔ ብቻ አይሽርም፡፡ እንዲያውም የፍርድ ቤት ውሳኔ የባሰ ብስጭት ሊፈጥርበት የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል ብዬ አስባለሁ፡፡ እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች ላይ ማህበረሰቡ በውስጡ ያለውን ስሜትና የኅሊና ፍርድ እንዲናገር ማድረግ ጠቃሚ ነው ይላሉ፤ የማህበራዊ ሳይንስ ሊቃውንት፡፡
የሹመት ሀትሪክ
ሃሳቤን በአንዲት እድሜ ጠገብ አባባል ልጀምር:: “ከእንጨት … ከሰው መርጦ ለሹመት” ይላሉ አበው:: ይህቺ አባባል ብዙ ነገር ትናገራለች፡፡ በሀገራችን ዘመናዊ የመንግስት አስተዳደር ስርዓት እውን መሆን የጀመረው በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ንጉስ ምኒልክ የመጀመሪያውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ12 ሚኒስትሮች ያዋቀሩት በ1900 ዓ.ል ነበር:: እነዚያ ተሿሚ ሚኒስትሮች ምን ዓይነት ስብጥር እንደነበራቸው በበኩሌ አልመረመርኩም፡፡ ይሁን እንጂ ተሿሚዎቹ የተመረጡት “… ከሰው መርጦ ለሹመት” በሚለው መስፈርት ሊሆን እንደሚችል አስባለሁ፡፡
በርግጥ ከበግ ወይም ከግመል አሊያም ከፈረስ መርጦ ሹመት ሊሰጥ ስለማይችል ይቺ አባባል አስቂኝ ገጽታ አላት፡፡ አስቂኝ ገጽታዋን ተትን ውስጧን ስንመረምር ግን ሌላ ምስጢር ብልጭ ብሎ ይታየናል፡፡ ይህ እውነታ ብልጭ እንዲልልን “ከሰው መርጦ” የሚለውን ሐረግ ወስደን ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡ በዚያ ዘመን “ሰው የሚባለው ‘ሰው’” ማን ነው? የሚለውን ጥያቄ ስናነሳ፤ ሰው ማለትማ የተማረ፣ የተመራመረ ለማለት ሳይሆን “መደባዊ ማንነት ያለው ሰው” ለማለት መሆኑን እንረዳለን፡፡ ስለዚህ በዚያ ዘመን ስልጣን ይገኝ የነበረው “የእከሌ ልጅ/ቤተሰብ” ተብሎ ደምና አጥንቱ ተቆጥሮ፣ ለስርዓቱና ለአልጋው ያለው ታማኝነትና ቅርበት ታይቶ የሚመረጥበት ሁኔታ እንደነበር እንገነዘባለን፡፡
ይሄ የምኒልክ ዘመን የተሿሚ መምረጫ መስፈርት ወደ አፄ ኃ/ስላሴም ዘመን ተሸጋግሯል ብዬ አስባለሁ:: በአፄ ኃ/ስላሴ ዘመን “የእከሌ ልጅ/ቤተሰብ” ተብሎ ደምና አጥንቱ ተቆጥሮ፣ ለስርዓቱና ለአልጋው ካለው ታማኝነት በተጨማሪ የትምህርት ዝግጅትና ብቃት በመስፈርትነት የሚካተትበት ሁኔታ እንደነበርም ማስተዋል ይቻላል፡፡ በዘመነ ደርግ ዘርና አጥንት ቆጠራው ችላ ቢባልም፣ መደባዊ ማንነትና ታማኝነት ዋነኛ መስፈርቶች ሆነው መቀጠላቸው ታይቷል፡፡
ወደ ኢህአዴግ ስንሸጋገር መስፈርቶቹ በርካታ እንደነበሩ ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ሌሎቹን መስፈርቶች ለጊዜው እንለፋቸውና በኢህአዴግ ዘመን ከእውቀትም፣ ከልምድም በላይ የሹመት ዋነኛው መስፈርት የድርጅት አባል መሆን ነበር:: አንድ ሰው የፈለገውን ያህል ሊቅ ቢሆን የኢህአዴግ አባል ካልሆነ አይሾምም፡፡ የድርጅት አባል ከሆነ ዘበኛም ቢሆን ሚኒስትር ተደርጎ ሊሾም እንደሚችል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በአደባባይ ነግረውናል፡፡ የኢህአዴግ ሲቪል ሰርቪስ ምስቅልቅሉ የወጣው በዚህ መስፈርት ምክንያት እንደነበር መገንዘብ ሊቅነትን የሚጠይቅ አይመስለኝም፡፡  
በዚህ ከንቱ መስፈርት ምክንያት በርካታ ሀገራቸውን መጥቀም የሚችሉ እውቀትም፣ ልምድም፣ ግንዛቤም ያላቸው ዜጎች እድሉን ተነፍገዋል:: በዚህ ከንቱ መስፈርት ምክንያት እውቀትም፣  ልምድም፣ ግንዛቤም የሌላቸው የድርጅት አባላት ስልጣን ጨብጠው ነገር ግን ወንበር ከማሞቅ የዘለለ ፋይዳ ያለው ስራ ሳይሰሩ ከወንበራቸው ላይ ተሽቀንጥረው ወርደዋል፡፡ የሚያሳዝነው አንዳንዶቹ በተመደቡበት የሚኒስትርነት ሹመት ፋይዳ ያለው ስራ አለመስራታቸው በግምገማ ጭምር ቢረጋገጥም ተጨማሪ ገንዘብን እንዲያገኙ የሦስትና የአራት ድርጅቶች የቦርድ ሰብሳቢ ወይም አባል የሚደረጉበት አጋጣሚም ነበር፡፡
ወደ ዘመነ ዶ/ር ዐቢይ እንለፍና ባለፈው አንድ ዓመት የሆነውን ለማየት እንሞክር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከቀደምት የኢህአዴግ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ለየት ያሉ የሚያስመሰግኗቸውን እርምጃዎች ወስደዋል፡፡ በዚህም እርምጃቸው አንዳንድ ዜጎች ባላቸው እውቀት፣ ልምድና ግንዛቤ ሀገራቸውን የማገልገል እድል አግኝተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ጠቃሚና ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት ጥረት ማድረግ ጀምረዋል፡፡
ይሁን እንጂ አሁንም ጉድለቶች ይስተዋላሉ:: በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዘመን፣ የኢህአዴግ አባል ያልሆኑ አንድ ሚኒስትር እንደነበሩ እናስታውሳለን፡፡ ይህ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል ሲገባው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ዘመን የድርጅት አባል ያልሆነ አንድም ሚኒስትር አለመኖሩ እጅግ የሚያሳዝን ነው:: አሳዛኙ ነገር ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስና በአቶ ኃ/ማሪያም ዘመን የተለያዩ ድርጅቶች የቦርድ አባል በመሆን “ሀትሪክ የሰሩ” (ከሦስት ድርጅት በላይ የቦርድ አባል የሆኑ) ባለስልጣናት ነበሩ፡፡ አሁን በዘመነ ዶ/ር ዐቢይ ደግሞ (ሀገሪቱ ሰው ያጣች ይመስል) ለተለያዩ ሀገራዊ ኮሚቴዎች አባል በመሆን “ሀትሪክ የሰሩ” ግለሰቦችን እያየንና እየሰማን ነው፡፡ የሚገርመው ነገር አንዳንዶቹ ግለሰቦች “ሀትሪክ” መስራታቸው ብቻ ሳይሆን ለተሰየሙበት ሀገራዊ ኮሚቴ አባል ለመሆን የሚያስችል በቂ የትምህርት ዝግጅትም ልምድም የሌላቸው መሆኑ ጭምር ነው፡፡
በመሰረቱ የተለያዩ ማንነቶችን ግምት ውስጥ ያስገባ ስብጥር ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ቀምመው ካስቀመጧት “ቅርጫት ውስጥ” ያሉ ሰዎችን ብቻ ሁልጊዜ እያወጡ መጠቀማቸው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ጠቃሚ ሥራ ሊሰሩ የሚችሉ ዜጎችን እድል የሚያሳጣ መሆኑን ልብ ሊሉት ይገባል፡፡
ከፍ ሲል እንደገለጽኩት ቀደም ባሉት ዓመታት ብዙዎቹ ሚኒስትሮች በሁለትና ሦስት ተቋማት የቦርድ አመራር አባል ሆነው በመስራታቸው፣ በጊዜ ማጣት እዚያም እዚህም ሲንደፋደፉ፣ የአንዱንም ተቋም ስራ በቂ ጊዜ ወስደው፣ ጥርት አድርገው መስራት አለመቻላቸው ይስተዋል ነበር፡፡ ከዚያ ድክመት ትምህርት ባለመወሰዱ ዛሬ በሁለትና በሦስት ሀገራዊ ኮሚቴዎች ውስጥ እንዲሰሩ በዶ/ር ዐቢይ የተመደቡ ግለሰቦችም ተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚገጥማቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- በጽሁፉ ውስጥ የተንጸባረቀው ሃሳብ ጸሐፊውን ብቻ የሚወክል ሲሆን ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 2971 times