Saturday, 02 June 2012 10:31

የዩጂን ሚኒማ ትንቅንቅ ዛሬም ይቀጥላል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በአሜሪካዋ ግዛት ኤራጎን ውስጥ ትናንት የተጀመረው የኢትዮጵያ አትሌቶች የለንደን ኦሎምፒክ መሳተፊያ ሚኒማ የማግኘት ትንቅንቅ ዛሬም የሚቀጥል ነው፡፡ ከ2012 የዳይመንድ ሊግ 14 ውድድሮች አንዱን በሚያስተናግደው የዩጂን ፕሮፈንታይኔ ክላሲክ ውድድር ላይ በለንደን ኦሎምፒክ በ10ሺሜ፤ በ3ሺ መሰናክልና በ1500ሜትር ኢትዮጵያን የሚወክሉ ኦሎምፒያኖች ይለዩበታል፡፡ ትናንት ምሽት በ10ሺ ሜትር ሴቶች የኦሎምፒክ ድርብ ሻምፒዮኗ ጥሩነሽ ዲባባ ጨምሮ በአጠቃላይ 15 የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የተሳተፉበት ውድድር ተደርጓል፡፡ በትናንቱ ውድድር ጥሩነሽ ዲባባ ከ30ደቂቃ በታች ለመግባት የሚያስችል የአሯሯጮች እንዲመደብ ጠይቃም ነበር፡፡ በ10ሺ ሜትር ውድድሩ የተሳተፉት ሌሎች የኢትዮጵያ አትሌቶች፤ ሱሌ ኡትራ፤ ውዴ አያሌው፤ በላይነሽ ኦልጅራ፤ ትእግስት ኪሮስ ፤አበበች አፈወርቅ፤ ወርቅነሽ ኪዳኔ ፤ አሃዛ ኪሮስና አበሩ ከበደ ነበሩ፡፡ ከሳምንት በኋላ በኒውዮርክ በሚቀጥለው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ትናንት 27ኛ ዓመቷን የደፈነችው ጥሩነሽ ዲባባ በ5ሺ ሜትር እንደምትሳተፍም ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም በ800 ሜትር አስቀድመው ሚኒማ ያመጡት ፋንቱ ሚጌሶና መሃመድ አማን  ትናንት በዩጂን ተወዳድረዋል፡፡

ዛሬ ደግሞ በ5ሺ እና 1500 የሚደረጉ ውድድሮች ይኖራሉ፡፡ትኩረት የሳበው በ5ሺ ሜትር ቀነኒሳ በቀለና ሞፋራህ ዛሬ የሚገናኙበት ውድድር ሲሆን  በ1500  የሚሳተፉት ኢትዮጵያውያን ደግሞ በወንዶች መኮንን ገብረመድህን፤ ዳዊት ወልዴና ተስፋዬ ቸሩ ሲሆኑ በሴቶች ሚኒማቸውን ለማግኘት የገቡት ትዝታ ቦጋለ እና ብርቱካን ፈይሳ፤ ናቸው፡፡ በዩጂን ፕሮፎንታይኔ ክላሲክስ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ከ43 በላይ የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮና ሜዳልያዎችን የሰበሰቡ 17 አትሌቶች መሳተፋቸው ደማቅ ፉክክር የፈጠረ ሆኗል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሆላንድ ሄንግሎ ከሳምንት በፊት በተደረገው የ10ሺ ሜትር ውድድር ላይ 1ኛና ሁለተኛ ደረጃ የወስዱት ታሪኩ በቀለ እና ሌሊሳ ዴሲሳ በቀጥታ ለኦሎምፒክ ቡድን አልፈዋል፡፡ 16 የኢትዮጵያ አትሌቶች በተካፈሉበት ውድድር ኃይሌ በ10ሺ ሜትር የትራክ ውድድር  “ሚር ሄንግሎ” ተብሎ በተወደሰባት የሆላንዷ ሄንግሎ ከተማ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተወዳድሮ ለለንደን ኦሎምፒክ ተሳትፎ ያደረገው የመጨረሻ ሙከራ 7ኛ በመውጣቱ አልተሳካለትም፡፡

 

 

Read 1788 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 10:34