Saturday, 25 May 2019 09:57

ፖለቲካ ያላችሁ፣ እስቲ እንያችሁ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

  “እናላችሁ…ሌላ ደግሞ… አለ አይደል... ‘የአፋልጉኝ ውጤቶች’ የሚባል ፓርቲ ይቋቋምልንማ! ልክ ነዋ…የበላቸው ጅብ ሳይጮህ ይከርምና እኛ አፋልጉን ማስታወቂያ ባናወጣም ራሳቸው፣ ራሳቸውን ፈልገው በየአራትም፣ በየምናምን ዓመቱም ብቅ የሚሉት ‘በልዩነት’ ቢሰባሰቡ ይሻላላ!--”
                       እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… ልዩ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይፈጠሩልን፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ብዙ እየተሳካልን አይመስልም፡፡ ስለዚህ ሀገር በቀል በሆኑ ሀሳቦች ለእኛ የሚስማሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይቋቋሙልን፡፡ ቢያንስ፣ ቢያንስ ኔኦ ሊበራል ምናምን እየተባባልን፣ ከስሙ በስተቀር ምኑንም በማናውቀው ነገር አንካሰስም:: ብንካሰስ አንኳን ‘ፖለቲካዊ ክሱ’ ሀገር በቀል ይሆናል፤ ቂ…ቂ…ቂ…(የአዲስ አበባ እድሮች በመሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሆኑ ወይ ያልከው ወዳጃችን፤ ቦተሊካ ‘እጣ ፈንታህ’ ሳይሆን አይቀርም!) 
እናማ… ሀሳብ አለን፡፡ ‘ፌዝ የፖለቲካ ፓርቲ’ ይቋቋምልን፡፡ ልክ ነዋ… ‘ቦተሊከኛ’ ነን የሚሉ፣ የስታንድአፕ ኮሜዲያንን ሰፈር እያጣበቡ ያሉ ፌዘኞች ስለበዙብን… አለ አይደል… የእኛ የሚሉት የተለየ ፓርቲ ይቋቋምላቸው! የፓርቲያቸው ስም ግልጽ ከሆነ፣ እኛም የእነሱን ስም የድራፍት ማወራረጃ አናደርገውም፡፡
“ስማ… ሰውየው ከተመረጥን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የጤፍ ዋጋን በኩንታል መቶ ሀምሳ ብር እናስገባዋለን አለ እኮ!”
“ማነው እሱ?”
“ያ አንኳን የፌዝ ፓርቲ ጸሃፊ ነው ምናምን…”
“እና…የፌዝ ፓርቲ ምን እንዲልልህ ነበር የፈለግኸው!”
አለቀ ማለት ነው፡፡ የምር ግን ምን ይመስልሀል በሉኝ… ‘የፌዝ ፓርቲ’ ከፍተኛ ድምጽ የሚያገኝ ይመስለኛል፡፡ ህዝባችን ቀደም ሲል በነበሩትም፣ አሁን አሉ በሚባሉትም የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን ያህል ተስፋ ስለሌለው፤ ወደፊት የተሻሉ ይመጡ ይሆናል አይነት ሀሳብን እንደ “ላም  አለኝ በሰማይ” አይነት ስለሚያየውም፣ ‘ፌዝ ፓርቲን’… አለ አይደል… በ‘ፕሮቴስት ቮት’ ለወንበር የሚያበቃ ነው የሚመስለኝ፡፡ (እነሱ ወንበር ሲይዙ ደግሞ ስታንድ አፕ ኮሜዲያን ከተማው ውስጥ ራሳችን የምናስተዳድረው የ‘ኮሜዲያን ክፍለ ከተማ’ ይከልልን ሊሉ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ አለ፡፡)
ስሙኝማ… ሀንጋሪ ውስጥ ‘ሀንጌሪያን ቱ ቴይልድ ዶግ ፓርቲ’ የሚሉት አለ፡፡ የተቋቋመው በሀገሪቱ ፖለቲከኞች ላይ ለማሾፍ ተብሎ ነው፡፡ ዓላማ ብለው ከዘረዘሯቸው መሀል…በሳምንት አንድ የሥራ ቀን ብቻ፣ በቀን ሁለቴ የጸሀይ መጥለቅ፣ ነጻ ቢራ፣ ዝቅተኛ ታክስ፣ ዘላለማዊ ህይወትና የዓለም ሰላም ናቸው፡፡ በተጨማሪም … “ነገ ትናንት መሆን ነበረበት፣” “ማኛውንም ነገር ቃል እንገባለን፣” በሚሉ አይነት አስቂኝ መፈክሮቻቸው ይታወቃሉ:: የዜማዎቻቸው ስንኞች ለየት ያሉ ናቸው…“ምን እንፈልጋለን? ምንም! መቼ እንፈልገዋለን? መቼም!” የሚሉ ዓይነት፡፡
የምር ግን አንዳንዴ ድርቅ፣ ምንችክ ካለው ፖለቲካችን ትንሽ ዘና የሚያደርገን የዚህ አይነት ፓርቲ ወይ ቡድን ነገር ቢኖርስ አያሰኝም! አሀ… በፖለቲካችን ከማማረር  ይልቅ ዘና ብለን እንስቃለና!
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ የሆነ ቦታ ያየኋትን ይቺን ስሙኝማ…
የአሜሪካ ዲሞክራት ስትሆን…
ሁለት ላሞች አሉህ፡፡
ጎረቤትህ ምንም የለውም፡፡
ስኬታማ ስለሆንከ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማሀል፡፡
የመረጥካቸው ሰዎች ላሞችህ ላይ ታክስ ይጥላሉ፡፡
ታክሱን ለመክፈልም አንዷን ለመሸጥ ትገደዳለህ፡፡
የመረጥካቸው ሰዎች ታክሱን ይወስዱና ለጎረቤትህ ላም ገዝተው ይሰጡታል፡፡
አንተም የኩራት ስሜት ያድርብሀል፡፡
የአሜሪካ ሪፐብሊካን ስትሆን ደግሞ…
ሁለት ላሞች አሉህ…
ጎረቤትህ ምንም የለውም፡፡
እና ምን ይጠበስ!
ታዲያላችሁ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እኛ ዘንድ አብዛኛው ‘ሶ ኮልድ ፖለቲከኛ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) “እና ምን ይጠበስ!” የሚል አይመስላችሁም!
ስሙኝማ… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ ግራ ግብት ያለን ነገር አለ፡፡ ከእነኚህ መቶ ምናምን የሆኑና ቅርብ ይሁን ሩቅ ያልለየለት መጪው ምርጫ ላይ ይሳተፉ ይሆናል ብለን  ከምናስባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ዘጠና ምናምን በመቶዎቹ የቆሙላቸው አላማዎች ገብተዋችኋል! ግራ ገባና… ስብሰባ ነው፤ የታሸገ ውሀ ነው፤ ሱፍ በከረባት ነው…ኸረ በስህተት እንኳን አንዳንድ አቋሞቻችሁን ወይም አቋም የሚመስሉ ነገሮቻችሁን ንገሩንማ፡፡
“እርስዎ የእንትን ፓርቲ ሰብሳቢ መሆንዎ ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ የትምህርት ፖሊሲያችሁ ምን ይመስላል?”
“ዋናው ፖሊሲያችን ትምህርትን በመላ ሀገሪቱ ማስፋፋት ነው፡፡”
“እሱን ለማለትማ ፖለቲከኛ መሆን አያስፈልግም፡፡ እኛ ማወቅ የምንፈልገው በምን መልኩ ነው ትምህርትን በመላ ሀገሪቱ የምታስፋፉት?”
“እሱን ስንመረጥ በዝርዝር የምንወያይበት ይሆናል፡፡”
የምር ‘የፌዝ ፓርቲ ይቋቋምልንማ!
ደግሞላችሁ… ‘የምቁ ፓርቲ’ ይቋቋምልንማ:: ፖለቲከኞች ይመቀኛኛሉ ወይ ከተባለ፣ እንክት አድርጎ ነዋ! አንደኛው የቢሮ በር ቆልፎ ቁልፉን አልሰጥም ብሎ ‘ለሰለስ ያለ ‘መፈንቀለ ፓርቲ’ የሚያደርገው፣ ሌላው ደግሞ ማህተም ይዞ ሄዶ አልሰጥም ብሎ የራሱን ደብዳቤዎች አይነት ነገር መጻጻፍ የሚጀምረው እኮ በፖለቲካ መስመር ልዩነት አይደለም፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ፖላንድ ውስጥ አንድ ፓርቲ አላቸው፡፡ ስሙ ማን መሰላችሁ… ‘ዘ ፖሊሽ ቢር ላቨርስ ፓርቲ’ አሪፍ አይደል! በነገራችን ላይ በ1991 በተደረገና ከባድ ፉክክር ነበረበት በተባለ ምርጫ ተወዳድረው፣ አስራ ስድስት መቀመጫ አሸንፈው ነበር፡፡ በወቅቱ ኮሚኒዝም ፈርሶ ፖላንድ ተርመስመስ ያለ ሁኔታ ውስጥ ስለነበረች ብዙም የፖለቲካ ፓርቲዎች አልነበሩም፡፡ መፈክራቸው ምን የሚል ነበር መሰላችሁ… “የተሻለ አይሆንም፤ ግን በእርግጠኝነት ይበልጥ አስቂኝ ይሆናል” የሚል ነበር፡፡ ስሙኝማ… መስከረም ሲጠባ “ከፖላንድ ባገኘነው ተሞክሮ…” ምናምን በሚል ‘ዳግም አረቄ ለሀገር እድገት’ አይነት ስም ያለው ፓርቲ ቢቋቋም የሚከለክል ህግ ይኖራል? ለማወቅ ያህል ነው:: መፈክራቸውም…አለ አይደል… “የዳግም አረቄን ውለታ መርሳት ለታሪከ ደንታ ቢስ መሆን ነው፣’ የሚል ሊሆን ይችላል፡፡
እናላችሁ…ሌላ ደግሞ… አለ አይደል... ‘የአፋልጉኝ ውጤቶች’ የሚባል ፓርቲ ይቋቋምልንማ! ልክ ነዋ…የበላቸው ጅብ ሳይጮህ ይከርምና እኛ አፋልጉን ማስታወቂያ ባናወጣም ራሳቸው፣ ራሳቸውን ፈልገው በየአራትም፣ በየምናምን ዓመቱም ብቅ የሚሉት ‘በልዩነት’ ቢሰባሰቡ ይሻላላ!
እኔ የምለው… ዓለም ስለ እኛ ስንቱን ክፉ ነገር ሲያወራ፣ ጠፍተው ከርመው፣ በ“ፉርሽ ባትሉኝ” ስለሚመለሱ ፖለቲከኞቻችን የማይዘግቡትሳ! ለፖለቲካ ሳይንቲስቶች አሪፍ የጥናት ርእስ ሊሆን ይችላላ! የሆነ መጠይቅ መበተን ነው…
“ለሦስት ዓመት ከዘጠኝ ወር ከፖለቲካው መድረክ የጠፋኸው የት ሄደህ ነው?”
“በጠፋህባቸው ዓመታት ፖለቲካዊ አስተሳሰብህ ምን ያህል ዳብሯል ትላለህ?” *
“ከአሁኑ ምርጫ በኋላ የምትሰወረው ለአራት ዓመት ነው ለስምንት?”
አይነት ጥያቄዎች መስጠት ነው፡፡ ታዲያላችሁ… “የኮከብ ምልክት የተደረገበት አስፈላጊው እሱኛው ስለሆነ ነው” የሚል የግርጌ ማስታወሻ ይጻፋል፡፡ ከምርምር በኋላም አጥኚው፣ ስለ ሁለተኛው ጥያቄ ድምዳሜውን ያሰፍራል፡፡
ተጠያቂው ለሁለተኛው ጥያቄ ከሰጠው መልስ ማወቅ እንደተቻለው፣ ከጅምሩም ምንም አይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ ስላልነበረው የተገኘው የዳበረ አስተሳሰብ ሳይሆን የፖለቲካ ውድድርን ከአርሴና ማንቼ ግጥሚያ ለይቶ ያለማየት አስተሳሰብ ነው፡፡
‘ምርመራ’ በሚለው ክፍልም ምን ብሎ ቢጻፍ ጥሩ ነው… “የዚህ ሰው ፖለቲከኛ መሆን በዚች ሀገር አንድ ሰው ምንም ነገር መሆን ቢያቅተው፣ በመጨረሻ ፖለቲከኛ መሆን እንደሚችል ነው::” ቂ…ቂ…ቂ…
ፖለቲካ ያላችሁ፣ እስቲ እንያችሁ…
  አንዱ ምን አለ መሰላችሁ… “ፖለቲከኛ ማለት ልምድ ያለው ኪስ አውላቂ ማለት ነው፡፡ የሁለቱንም ባህሪይ ወደ በጎ መለወጥ አስቸጋሪ ነው::” (የ‘ጥናቱ’ ምንጭ አልተጠቀሰም፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…)
ደህና ሰንብቱልኛማ!

Read 1725 times