Saturday, 25 May 2019 09:35

ቃለ ምልልስ “የምጠላው ግፈኝነትን፤ የማስቀድመው ሰብአዊነትን ነው”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 · የዶ/ር ዐቢይ ቀናነት መሬት ላይ እንዳይወርድ በርካታ እንቅፋቶች አሉ
              · አቶ ማሙሸት የተመሰረቱባቸውን አስገራሚ ክሶች ይዘረዝራሉ
              · ለ8 ወር ፍርድ ቤት ሳልቀርብ፣ በግፍ ታስሬ ቆይቻለሁ ይላሉ
              · ለአገራዊ ቀውሱ መፍትሄው የሽግግር መንግስት ማቋቋም ነው


           አቶ ማሙሸት አማረ በመኢአድ ጉዳይ በምርጫ ቦርድ መታገዳቸውን ተከትሎ በተደጋጋሚ ለእስር እንደተዳረጉና አስገራሚ ክሶች እንደተመሰረቱባቸው ይናገራሉ፡፡ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለበርካታ ወራት በግፍ መታሰራቸውንም ያስረዳሉ:: ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ድራማ የሚመስለውን የእስራቸውንና ክሳቸውን ሂደት በዝርዝር ተርከውታል፡፡ ከዚህም ባሻገር እንዴት ወደ መኢአድ ተመልሰው፣ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ሆነው እንደተሾሙም ነግረውናል:: ፓርቲያቸው ለምን ራሱን ከውህደት አገለለ? ለውጡንና የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል? አገሪቱ ለገጠማት ቀውስ መፍትሄው ምንድን ነው? በሚሉና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የመኢአድ አዲሱ ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ፣ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር አውግተዋል፡፡


             በምን ዓይነት ሁኔታ ነው ወደ መኢአድ የተመለሱት?
ከእስር ቤት ከወጣሁ በኋላ በአመዛኙ ህዝባዊ አገልግሎቶች ላይ ነበር ስሳተፍ የቆየሁት፡፡ አስራት እና ሌሎች ሚዲያዎችን በማቋቋም፣ የተፈናቀሉ ወገኖችን በማበረታታትና ድጋፍ እንዲደረግላቸው በመቀስቀስ ስራ ላይ ቆይቻለሁ፡፡ እስር ቤት እያለሁ እጄን ሰብረውኝ ነበር፤ እሱንም ስታከም ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን ከፓርቲው ሰዎች ጋር መነጋገር ጀመርን፡፡ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስንነጋገር ቆይተን፣ እርቅ ፈጽመን ነው ወደ ፓርቲው የተመለስነው፡፡ ያው ከተመለስንም በኋላ ፓርቲው ጉባኤ አድርጐ እኔን በድጋሚ በፕሬዚዳንትነት መርጦኛል ማለት ነው፡፡
ከመኢአድ አመራርነት በምርጫ ቦርድ ውሣኔ ከተባረራችሁ በኋላ እርስዎ በተደጋጋሚ ታስረዋል:: የእስር ምክንያቶቹ  ምን ነበሩ?
የሚገርመው በፓርቲው ጉዳይ በምርጫ ቦርድ የተወሰነውን ውሣኔ ተቃውመን፣ ለፍ/ቤት አቤቱታ አቅርበን፣ የመጨረሻውን ውሣኔ ለመስማት ቀጠሮ እየጠበቅን በነበረበት ወቅት ነው አይኤስ ነህ ተብዬ የታሠርኩት፡፡ ፍ/ቤት በመኢአድ ጉዳይ የመጨረሻ ውሣኔ ለመስጠት ለግንቦት 13 ቀን 2007 ነበር የቀጠረው፡፡ እኔ በመሃል ግንቦት 5 ቀን በአይኤስ በታረዱት ሰዎች እጁ አለበት ተብዬ ታሰርኩ፡፡ የተያዝኩበት አጋጣሚም ጠዋት ወደ ዩኒቨርስቲ ለፈተና ስገባ ነበር፡፡ በደህንነቶች ታፍኜ ተወስጄ ለ5 ወራት ታስሬአለሁ፡፡ የተመሰረተብኝ ክስም በሊቢያ በታረዱት ወገኖቻችን ሞት እጁ አለበት የሚል ነበር::
እጁ አለበት ሲባል የአይኤስ አባል ነው ለማለት ነው ወይስ ምንድን ነው?
ከአይኤስ ጋር ግንኙነት እየፈጠረ ሲያሸብር ነበር፤ በግድያውም እጁ አለበት በሚል ነው ፍ/ቤት ያቀረቡኝ፡፡ ይሄ ሁሌም ሳስበው ለእኔ ይገርመኛል:: ፍ/ቤቱ በወቅቱ “ይህ ሰው እርግጠኛ ናችሁ አይኤስ ነው?” ብሎ ደጋግሞ ጠይቆ ነበር፡፡ እኔም ተቃውሞዬን አቅርቤያለሁ፡፡ በኋላ ደግሞ በሌላ ቀጠሮ የክሱ ይዘት ተቀየረና ሚያዚያ 14 በተደረገው አይኤስን የማውገዝ የመስቀል አደባባይ ሠልፍ ላይ 1 ሚሊዮን ለሚሆን ህዝብ “ወያኔ አይኤስ ነው፤ ወያኔ ካልወረደ ኢትዮጵያ ሰላም የላትም” የሚል ተቃውሞ በማንሳት፣ ህዝብና ሀገር ላይ ጉዳት በሚያደርስ መልኩ ተንቀሳቅሷል ወደሚል ተቀየረ፡፡
የሚገርመው ሚያዚያ 14 እኔ ልደታ ፍ/ቤት በፓርቲው ጉዳይ ቀጠሮ ነበረኝና እዚያ ነበርኩ:: እነሱ ደህንነቶች አምጥተው “በሰልፉ ላይ አይተነዋል” ብለው በሃሰት አስመሰከሩብኝ፡፡ እኔ ደግሞ በዕለቱ ሰልፉ ሲካሄድ ፍ/ቤት እንደነበርኩ የሚያሳይ ማረጋገጫ የዋልኩበት ፍ/ቤት ፃፈልኝ፡፡ በዚህ የእነሱ ሃሰት ተጋለጠ፡፡ ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው ፍ/ቤትም፤ አቃቤ ህግ ክሱን እንዲያነሳ አድርጐ በነፃ አሰናበተኝ::  የሚያሳዝነው ግን ከዚያ ከፍ/ቤት ግቢ ሳልወጣ በድጋሚ በደህንነቶች ታፍኜ፣ በዚያው ማዕከላዊ ለብቻዬ ጨለማ ውስጥ አሠሩኝ፡፡ ሌላ ውንጀላም ይዘው መጡ፡፡ “የግንቦት 7 አባል ነህ፣ ከኤርትራ መንግስት ጋር ግንኙነት አለህ፣ ሰዎች እየመለመልክ ወደ ኤርትራ ትወስዳለህ” አሉኝ፡፡ እኔም ጉዳዩ እኔን ሆን ብሎ ለማንገላታት እየተሠራ ያለ ድራማ መሆኑ ስለገባኝ፣ ምንም መናገር አልፈለግሁም:: በሦስተኛው ቀን አራዳ ምድብ ችሎት ቀረብኩ:: በአይኤስ ጉዳይ አዲስ ክስ ይዘው ነበር ፍ/ቤት ያቀረቡኝ፡፡ ሚያዚያ 14 መስቀል አደባባይ አሳመፀ የሚለው ቀርቶ፣ ሚያዚያ 12 እና 13 በቦሌ አካባቢ ያሉ ወጣቶችን ወደ ሃዘንተኞች ቤት እየመራ፣ “ወያኔ አይኤስ ነው የሚል መፈክር ቂርቆስ በሚገኝ የሟቾች ቤት ተገኝቶ ሲያሰማ ውሏል” የሚል አዲስ ክስ አመጡብኝ፡፡ በዚህ ክስ ላይ “ከቂርቆስ የሟቾች ቤት ተነስቶም ወጣቶችን እየመራ፣ ወደ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ በማሰብ ተንቀሳቅሷል” የሚል ክስ አቀረቡብኝ፡፡
ለዚህ ክስ ያቀረቧቸው ምስክሮች “አቶ ማሙሸት ለእያንዳንዳችን 300 ብር እየሰጠ፣ ወያኔ አይኤስ ነው በሉ ብሎናል” ነበር ያሉት፡፡ “በመስቀል አደባባይ ለተገኘው 1 ሚሊዮን ሰው፣ ለእያንዳንዱ 300 ብር ሰጥቷል” በማለትም በአስገራሚ ሁኔታ መስክረዋል:: በዚህ የምስክርነት ሁኔታ ተደንቄ፤ “ብር የያዝኩት በመኪና ነው? በምንድን ነው?” ብዬ በመስቀለኛ ጥያቄ ስጠይቅ፣ በግልጽ መደናገር ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ በኋላ አንደኛው ምስክር በጥያቄው መጨነቁን ተናግሮ፣ “300 ብር ሰጥቶናል ብላችሁ መስክሩ ያሉን አቃቤ ህጉና ፖሊስ ናቸው” ብሎ እዚያው ፍ/ቤት እውነቱን ተናገረ፡፡ ወዲያው ዳኛዋ ዋስትናዬን አስጠበቁልኝና፣ 5ሺህ ብር ዋስ ከፍዬ እንድወጣ ፈቀዱልኝ፡፡ ነገር ግን ፖሊስ ከእስር ሊለቀኝ አልቻለም፡፡ ይግባኝ ብሎ ዋስትናውን በሌላ ፍ/ቤት አስከለከለኝ፡፡ ክርክሩ በሌላ ፍ/ቤት ቀጠለና፣ መጨረሻ ላይ ዳኛው ለከሳሾቹ “በጣም አዝናለሁ” ብለው 10 ገጽ ትችት ጽፈው በነፃ አሰናበቱኝ፡፡ በነፃ ከተሰናበትኩ በኋላ ደግሞ ለ10 ቀናት ደህንነቶች በራሳቸው ውሳኔ በእስር ቤት አቆይተው ነው የለቀቁኝ፡፡  
ከዚያ በኋላም ታስረው ነበር አይደል?
አዎ! በተደጋጋሚ አርፌ እንድቀመጥ፤ በፖለቲካ ጉዳይ ምንም እንቅስቃሴ እንዳላደርግ ከደህንነት ቢሮ ማስጠንቀቂያ ይሰጠኝ ነበር፡፡ ሦስት ሰው መድበውልኝ፣ ውሎና አዳሬን ይከታተሉ ነበር፡፡ ከእኔ ጋር የተገናኙትን ሰዎች ሁሉ እየጠለፉ ወደ እስር ቤት መውሰድ ጀመሩ፡፡ በ2008 ዓ.ም አመጽ በመላ ሀገሪቱ ሲቀሰቀስ የበለጠ ትኩረት አድርገውብኝ ነበር፡፡ እኔም በወቅቱ አሞኝም ስለነበር ትንሽ ፀበል ልጠመቅ ብዬ ወደ ሰሜን ሸዋ ምንጃር ዮሐንስ ፀበል ሄድኩ፡፡ እነሱ ግን “ጐንደር አመጽ ሊቀሰቅስ ሄዷል፤ ከየትም አምጡት” እያሉ ቤተሰቤን ያስጨንቁ ነበር፤ በኋላ ፀበል ቦታ እያለሁ ወንድሜ ስንቅ ሊያቀብለኝ በመጣበት አጋጣሚ ተከታትለውት፣ ከዚያው ከፀበል ቦታ ያዙኝና በድጋሚ ታሰርኩ ማለት ነው፡፡ የሚያሳዝነው ለ8 ወር ፍ/ቤት ሳልቀርብ፣ ቤተሰቤም ከመታሰሬ ውጪ የት እንዳለሁ ሳያውቅ ነበር የቆየሁት፡፡ በኋላ ሚዲያዎች ስለ ጉዳዩ ሲጯጯሁ፣ ከ8 ወር የግፍ እስር በኋላ ፍ/ቤት ቀረብኩ፡፡ የቀረበብኝ ክስም፤ “በጐንደር የተነሳውን አመጽ ማለትም የጋይንትን፣ የዳባትን፣ የጃንአሞራን፣ የወልቃይትን፣ የባህር ዳርንና አንዳንድ ኦሮሚያ አካባቢ ያሉ አመፆችን በማደራጀትና በመምራት፣ መንግስትን በሃይል ለመጣል በመንቀሳቀስ” የሚል ነው፡፡ በተጨማሪም፤ “በሰሜን ሸዋ ሁለት የጦር ማሰልጠኛዎችን በማቋቋም፣ ሰዎችን ከአዲስ አበባ እየመለመለ ብር ከውጪ ተቀብሎ፣ ጠመንጃ ገዝቶ እያሰለጠነ ነው” ይላል፤ ክሱ፡፡ በዚህ ክስ የተጠቀሰብኝ አንቀጽ ሞት የሚያስፈርድ ነበር፡፡ እኔም ለፍ/ቤቱ ምንም ላለማለት፣ ላለመከራከር ወስኜ በየችሎቱ ዝም ብዬ የሚባለውን እየሰማሁ ብቻ ነበር የምመለሰው፡፡ እነሱም ፍ/ቤቱን የሚያሳምን ማስረጃ ማቅረብ አልቻሉም፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ፣ በመሃል  የካቲት 7 ቀን 2010 ዓ.ም እቃችሁን ይዛችሁ ውጡ ተባልንና ወጣን፡፡
የእናንተን ከእስር መፈታትና አሁን ያለውን የለውጥ ሂደት  እንዴት ይመለከቱታል?
ለውጥ ማለት የአሠራር፣ የተቋም፣ የስርዓት ለውጥ ሲኖር ነው፡፡ በዚህ ሃገር አሁን የተቋምም ሆነ የሥርአት ለውጥ የለም፤ የአሠራር ለውጥም የለም:: ያው አሠራር፣ ያው ተቋማት፣ ያው ስርአት ነው የቀጠለው፡፡ ነገር ግን የለውጥ ብልጭታው አለ:: ከእስር ቤት መፈታታችን እንደ ለውጥ መወሰዱ ተገቢ አይደለም፡፡ መጀመሪያውኑ መብታችንን ስለጠየቅን መታሰር የማይገባን ሰዎች ነን፡፡ መቃወም ነው ያሳሰረን እንጂ የተለየ የሠራነው ወንጀል የለም:: እንደውም ህግ ቢኖር፣ እነሱ እኛን ስላሰሩ ይቅርታ መጠየቅ ነበረባቸው፡፡ ከአቶ ሃይለማርያም ወደ ዶ/ር ዐቢይ የተደረገ ለውጥ አለ፡፡ ዶ/ር ዐቢይ በግላቸው ቅን አሳቢ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በአነጋገራቸው በአስተሳሰባቸው ቀና ናቸው፡፡ እንደ ድሮዎቹ ፍረጃ አያበዙም፡፡ የእሳቸው ቀናነት ብቻውን ግን ለውጥ መጥቷል አያስብልም፡፡ ምክንያቱም ቀና ስርአት፣ ቀና ተቋም፣ ቀና አሠራር አልመጣም፡፡ ኢህአዴግ እንዳለ ነው ያለው፡፡ የእሣቸው ቀናነት እንኳ በወረዳ፣ በዞን፣ በክልል ደረጃ መሬት ላይ የለም፡፡ የእሣቸው ቀናነት ያለው እሳቸው ጋ ብቻ ነው፡፡ እሳቸው ቀናነታቸውን መሬት ላይ ማውረድ አለመቻላቸውን እየተመለከትን ነው፡፡ ለዚህ ነው ሰው የሚፈናቀለው፣ የሚገደለው፣ ስርአት አልበኝነት የተስፋፋው፡፡ የዶ/ር ዐቢይ አስተሳሰብና አሠራር መሬት ላይ እንዳይወርድ በርካታ እንቅፋቶች አሉ፡፡  የጐበዝ አለቃ፣ ሁሉ ነገር የኔ ነው ባይ፣ ባለተራ ነኝ ባይ የእሣቸው አስተሳሰብ መሬት ላይ እንዳይወርድ እንቅፋት እየሆኑ ነው:: ኢህአዴግ አሁንም ፖሊሲው፣ ተቋማቱ፣ አሠራሩ ሁሉ እንዳለ ነው፡፡ ለዚህም  ነው ዛሬም የህዝብ መከራ የበዛው፡፡
እርስዎ ምን አይነት ለውጥ ነበር የሚጠብቁት ወይም የሚፈልጉት?
ለውጡ ማህበረሰቡን በደንብ ያሳተፈ መሆን ነበረበት፡፡ እርግጥ ነው ባለፉት 27 አመታት በሀገሪቱ የተፈጠረው ችግር ከባድ ነው፡፡ ማንም በአንድ አመት ወይም በሁለት አመት በቀላሉ የሚፈታው አይደለም፡፡ መኢአድ አሁን አሸንፎ ስልጣን ቢይዝ፣ ይሄን አገር በአንድ ጊዜ ቀጥ አድርጐ ለመምራት እንደሚቸገር ጥርጥር የለውም፡፡ የተቀበሩ መአት የተንኮል ፈንጂዎች አሉ፡፡ እነዚያ ፈንጂዎች በጥንቃቄ መክሸፍ አለባቸው፡፡ ፈንጂዎቹ እንዲከሽፉ አሁን ኢትዮጵያን ያስፈልጋት የነበረው የሽግግር መንግስት ነው፡፡ ቢያንስ የ1 አመት ዕድሜ ያለው፣ ሁሉንም ያካተተ የሽግግር መንግስት ተቋቁሞ፣ ተቋማትን ሊያስተካክል ይገባ ነበር፡፡
እኔ የማስበው፣ የሽግግር መንግስት፣ በመጀመሪያ በሀገሪቱ እርቅና መግባባትን የሚፈጥር፤ ቀጥሎ ህገ መንግስቱን በሚያግባባን መልኩ እንደገና እንዲዘጋጅ የሚያደርግና የዲሞክራሲ ተቋማትን ገንብቶ፣ ምርጫን አስፈጽሞ፣ ለአሸናፊው ወገን ስልጣን የሚያስረክብ ይሆን ነበር፡፡ አሁን ዶ/ር ዐቢይ የሀገሪቱ ቀዳዳዎች በዝተው የተቸገሩት በዚህ የተነሳ ነው፡፡ አንዱ ማንነቱን ሲጠይቅ፣ ሌላው ክልል፣ ሌላው ከክልሌ ውጣልኝ፣ የብሔርና የዘር ጥያቄው---እነዚህ ሁሉ አስፈላጊው የሽግግር ሂደት ውስጥ ባለመግባታችን የሚከሰቱ ናቸው፡፡ አሁን በሀገሪቱ ያሉ መራራቆች፣ መጓተቶች ሁሉ የዚህ ውጤት ናቸው፡፡ ይህን መራራቅና መጓተት ወደ እርስ በእርስ መጋመድ ቀይሮ ኢትዮጵያን ማስቀጠል ካልተቻለ፣ ለወደፊትም ፈተናችን መቀጠሉ  አይቀርም፡፡
እኔ ዶ/ር ዐቢይን ብሆን ከምንም በፊት የማደርገው ሁሉንም ያሳተፈ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ነበር፤ ቀጥሎም ህዝቡ ወደ እርቅና ብሔራዊ መግባባት በሽግግር መንግስቱ በኩል የሚሄድበትን መንገድ እፈጥራለሁ፤እንደ ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ተቀምጬ “እኔ አሻግራችኋለሁ አልልም” ነበር፡፡ የፀብና የችግሮች ሁሉ መነሻ የሆነው ህገ መንግስት ሳይሻሻል፣ ይሄን ሃገር አሻሽላለሁ ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ጐጠኝነትን አስፍቶ ኢትዮጵያዊነትን ያቀጨጨ ነው፡፡ ይሄን ይዞ እንዴት ነው ኢትዮጵያን መገንባት የሚቻለው? የችግሮች ሁሉ መነሻ የሆነው ህገ መንግስት ሳይሻሻል፣ ሌላ ነገር ማሻሻል አርቴፊሻል ነው የሚሆነው፡፡
አሁን አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?
የየአካባቢው ህዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች፣ በየቦታው በሚደረጉ ሰልፎች የሚወጡ መፈክሮች፣ በየቦታው ያሉ ጩኸቶች ሲታዩ ሁኔታው አስፈሪ ነው፡፡ አሁን ሁሉም በየአካባቢው ንጉስ ሆኗል፤ የመሳፍንት ዘመን ላይ ያለን ነው የሚመስለው:: ይሄን ለመንግስት ብቻ በመተው የሚታለፍ አይደለም፡፡ የአገራችን ጉዳይ ያገባናል የምንል ሁሉ መንግስትን ምን እየሠራህ ነው? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፤ አቅጣጫዎችን መንገዶችን ማመላከት ያስፈልጋል፡፡ ወዴት እየሄድን ነው? ምን ሲፈጠር ነው የምንረካው? በሚሉ ጥያቄዎች ላይ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል:: ስለ ምርጫ ከማውራታችን በፊት ፖለቲከኞች፣ እነዚህን አገራዊ ጉዳዮች በማስተካከል ላይ መሳተፍ አለብን፡፡  
የብሔራዊ መግባባትና እርቅ ኮሚሽን መቋቋም፣ ምርጫ ቦርድን፣ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን፣ የደህንነትና መከላከያ መ/ቤቶችን ሪፎርም የማድረግ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
የእርቅ ኮሚሽን የተባለው ከተቋቋመ ቢቆይም እስካሁን ሥራ አልጀመረም፡፡ ህዝብ አሁንም እየሞተ፣ እየተፈናቀለ ነው፡፡ የድንበር ኮሚሽኑም በተመሳሳይ ምንም እያደረገ ያለው ነገር የለም:: በዚያ ላይ ኮሚሽኑ ሁሉንም ያግባባ አይደለም:: ኢህአዴጎች እንኳ በድንበር ኮሚሽኑ ጉዳይ ላይ አልተግባቡም:: ኢህአዴግ እርስ በእርስ ተግባብቶ ባልሄደበት ሁኔታ፣ የድንበር ኮሚሽኑ የሚሠራው ስራ ተቀባይነት ያገኛል ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ አስቀድሜ እንዳልኩት፣ በመጀመሪያ መሠራት የነበረበት ሥራ አልተሠራም፡፡ ከሽግግር መንግስት የመነጨ ቢሆን፣ አጨቃጫቂ አይሆንም  ነበር፡፡ የእርቅ ኮሚሽን ውስጥ እኮ ብዙ ግፍ ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አሉበት፡፡ ይሄ እንዴት ይሆናል? የአቶ ኃይለማርያም መንግስት ሃገር አዘርፎ፣ የህዝብ ማንነትን አስነጥቆ፣ ሰብአዊ መብትን አስደፍጥጦ በህዝብ ማዕበል የወደቀ መንግስት ነው፡፡ ያ ሁሉ ግፍ ሲፈፀም፣ አቶ ኃይለማርያም ያውቃሉ፡፡ የእሣቸው በዚህ ኮሚሽን ውስጥ መካተት በራሱ የሚያግባባ አይደለም፡፡ አሁን ያለውን የዘር ፌደራሊዝም ያካለለ ህገ መንግስት አስቀምጦ የወሰንና ማንነት ኮሚሽን ማቋቋም በራሱ ተቃርኖው ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ ህገ መንግስት ላይ በሚቀዳ ማናቸውም የህግ ማሻሻል፣ የተቋም ለውጥ፣ የብሔራዊ መግባባትና እርቅ ማምጣት ፈጽሞ አይቻልም፡፡
ታዲያ ምንድን ነው መደረግ ያለበት?
አስቀድሜ እንዳልኩት፤ በመጀመሪያ በህዝብ የታመነ፣ ሁሉን ያካተተ የሽግግር መንግስት ማቋቋም፣ በሽግግር መንግስቱ አስፈፃሚነት የህወሓት የፖለቲካ ፕሮግራም የሆነውን ህገ መንግስት መቀየር፡፡ ይሄ ህገ መንግስት’ኮ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች አፈር የበሉበት ነው:: ማንም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ አይያዝም ይላል፤ ህጉ፡፡ እኛ’ኮ የተያዝነው ያለ ፍ/ቤት ትዕዛዝ ነው፡፡ ማንም ሰው ቃሉን ለመርማሪ ፖሊስ ለመስጠት አይገደድም ይላል፡፡ እኛ’ኮ ተገድደን ነው ቃል ስንሰጥ የነበረው፡፡ ስለዚህ ይሄ ህገ መንግስት በተግባር ተፈትሾ የወቀደ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ለኛ እሳት ነው፡፡ እሳት ደግሞ በጉያ አይያዝም፡፡ ስለዚህ ህገ መንግስቱ በቅድሚያ መሻሻል ሳይሆን መቀየር ነው ያለበት፡፡ በተቀየረው ህገ መንግስት ነው የሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ መወሰን ያለበት እንጂ በዚህ ህገ መንግስት አይደለም::
በሀገሪቱ የተንሰራፋውን ዘረኝነት ማርገብ፣ አዲስ ማስገዛት የሚቻለውም ይሄ ህገ መንግስት ሲቀየር ነው፡፡ አንዳንዶች ህወኃትን በጽኑ ያወግዛሉ፤ ህወኃትን ሲያወግዙ አስተሳሰቡን ሳይሆን ሰዎቹን ነው፡፡ መወገዝ ያለበት ግን ሰዎቹ ሳይሆኑ አስተሳሰቡ ነው፡፡ አስተሳሰቡ ዛሬም ሀገር እየመራ ነው፡፡ ሰዎች በቦታው ተመድበውለት ሃሳቡ ህገ መንግስቱን በጉያው አድርጐ እየሠራ ነው፡፡ ይሄን ሃሳብ ነው ማስወገድ ያለብን እንጂ ሰዎቹ ላይ ማነጣጠሩ ጥቅም የለውም፡፡ ዘረኝነትና ብሔርተኝነት በቀላሉ የሚጠፋ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሁሉም ሰው መንደሩን ራሱን ይወዳል፤ ነገር ግን ማቀዛቀዝ ወይም ማርገብ ይቻላል፡፡ እኩልነትን በማስፈን ነገሩን ማርገብ ይቻላል፡፡ እኩልነት ነው የዘረኝነት ማርገቢያ መንገዱ፡፡
ወደ ፓርቲያችሁ ጉዳይ እንምጣና፣ አሁን  በሀገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች ውህደት እየፈፀሙ ነው፡፡ መኢአድ ከእነዚህ ውህደቶች ለምን ራሱን አገለለ? ውህደቶቹን በተመለከተ አቋማችሁ ምንድን ነው?
ውህደት እንዲህ በቀላሉ የሚሆን አይደለም፡፡ በአስተሳሰብ፣ በፕሮግራም፣ በቀናነት መመሳሰልን ይጠይቃል፡፡ እንደሚታወቀው በዚህ ሀገር ውስጥ በርካታ ውህደቶች ተፈጽመዋል፡፡ ከመጀመሪያው አንስቶ ብናይ፣ በ1985 አማራጭ ሃይሎች የሚባል ተመስርቶ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ የደቡብ ህዝቦች ህብረት  የሚባል በአሜሪካ ሀገር 15 ድርጅቶች የመሠረቱት ነበር፡፡ የኢዴፓ እና የኦዳግ፣ የብድህ ከመኢአድ ጋር መዋኃድ፣ እንዲሁም ቅንጅት -- ተፈጥሮ ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ ዛሬ የት ገቡ? ለምንና እንዴት ፈረሱ? ብሎ መጀመሪያ መጠየቅ ያስፈልጋል:: ሸርና ተንኮል ነው እነዚህን ድርጅቶች ያፈረሳቸው፡፡ አሁንም የሚመሠረቱት ውህደቶች፣ ከዚህ የፀዱ አይደሉም፡፡ አሁን ውህደት ፈጠሩ ከተባሉት እንኳ “ድርጅታችን አልፈረሰም፤ ውህደት አልፈፀመም” የሚሉ በርካታ አቤቱታዎች ለምርጫ ቦርድ እየቀረቡ ነው፡፡ ይሄ አሁንም ሸር መኖሩን ያመላክታል፡፡ መኢአድ ፓርቲ ማክሰም የሚለውን ሃሳብ አይቀበልም፡፡ ለምን ይከስማል? በመላ ሀገሪቱ ሰፊ አደረጃጀት ያለው ፓርቲ እንዴት ይከስማል? እኛ በፍፁም ከውህደት አልሸሸንም፡፡ አሁንም ከተወሰኑ ድርጅቶች ጋር የጀመርነው ውይይት አለ፡፡ እኛ ከማንም የመዋሃድ  ጥያቄ አልቀረበልንም፡፡ “ግንቦት 7” ራሳችሁን አክስሙና እንዋሃድ ብሎ ጠይቆ ነበር፤ በዚህ ስላልተስማማን አልሆነም፡፡ እኛ መፍረስ በሚባለው ነገር አንስማማም፡፡ በቅንነት ከመጣ አካል ጋር ግን ለመዋሃድ ችግር የለብንም፡፡
መኢአድ እርስዎ ወደ ፕሬዚዳንትነቱ ከመጡ በኋላ ምን ተግባራትን እያከናወነ ነው?  
ለቀጣይ የፖለቲካ አካሄዳችን አጋዥ የሆኑ ሰነዶችን እያዘጋጀን ነው፡፡ ሌላው  መኢአድ ከዚህ ቀደም በመላ ሀገሪቱ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ አባላት የነበሩት ድርጅት ነው፡፡ አሁን ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ አባሎቻችንና ፅ/ቤቶቻችን ላይ ቆጠራና ማጣራት እያደረግን ነው፡፡ መኢአድ እንግዲህ ትልቁ መሠረቱ ደቡብ ኢትዮጵያ ነው፤ ቀጥሎ አማራ ክልል ከደብረ ብርሃን እስከ ትግራይ፣ ጐንደር፣ ጐጃም፣ ኦሮሚያ፣ አፋር ያሉ ጽ/ቤቶችን ያቋቋምነው ቡድን ዞሮ ይቃኛል፡፡ በቀጣይም ከህዝብ ጋር በምርጫና በፓርቲያችን ጉዳይ ላይ በየቦታው ውይይት እናደርጋለን፡፡ በትግራይ 28 ወረዳዎች ላይ ጽ/ቤቶች ነበሩን፤ አሁን እነዚያ ሁሉ ተዘግተውብናል፡፡ አባሎቻችን ግን አሁንም በጠቅላላ ጉባኤያችን እየተሳተፉ፣ በአባልነታቸው ቀጥለዋል:: በፓርቲያችን ላይ በትግራይ እየደረሰብን ያለው ችግር፣ በቀላሉ የሚነገር አይደለም፡፡
እርስዎ የሚመሩት መኢአድ፤ በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምንና ዘረኝነትን የሚያወግዝ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር ግን የአማራ ብሔርተኝነትን ሲያቀነቅኑ ተደምጠዋል፡፡ ይሄ ከሚመሩት ፓርቲ አላማ ጋር አይጋጭም?
መቼም ሁላችንም ኢ-ሰብአዊነትን ነው የምንፀየፈው፡፡ ጌዲኦ ላይ ግፍ ሲፈፀም መጀመሪያ መግለጫ የሰጠነው እኛ ነን፡፡ ባለፉት 28 ዓመታት ደግሞ በየቦታው የሚሳደደው አማራው ነው፡፡ ስለዚህ ያንን ችግር ነቅሼ ነው ድርጊቱን ያወገዝኩት::
በንግግርዎ “ፊደሉ የአማራ ነው፤ አክሱም የአማራ ነው፤ ቅኔው የአማራ ነው … አማራ ነው ይሄን አገር፣ አገር ያደረገው” ሲሉ ተደምጠዋል ---
ይሄን ንግግር ያደረግሁበትን መድረክ የጋበዘኝ የአማራ ወጣት ማህበር ነው፡፡ በዚያ መድረክ ላይ ልናገር የምችለው ስለ አማራ ህዝብ ነው፡፡ አክሱም የኔ ነው ስል ወልቃይት ላይ ብቻ ቆማችሁ አታውሩ፤ አክሱምም የአባቶቻችሁ የጣት አሻራ ነው ለማለት ነው የፈለግሁት፡፡ ጅማ፣ ባሌ ላይ የእናንተ የጣት አሻራ ነው ያለው ለማለት ነው የፈልግሁት፡፡ ቋንቋው ፊደሉ የእናንተ ነው ስል፣ የእናንተ ብቻ ነው እያልኩ አይደለም፡፡ አክሱም አሁንም የስልጣኔያችን መነሻ፣ የአባቶቻችን አሻራ ነው፡፡ ይሄ እምነቴ ነው፡፡ እኔ የአማራን ህዝብ ከሌላው የማግዘፍ አላማ የለኝም፤ መኢአድም የአማራ ድርጅት አይደለም፡፡ 70 በመቶ ያህሉ አባላችን የደቡብ ሰው ነው፡፡ ትልቁ መሰረታችን ደቡብ ኢትዮጵያ ነው፡፡ እኔ የማወግዘው ኢ-ሰብአዊነትን ነው፡፡  
እርስዎ የአማራ ብሔርተኛ  ነዎት?
እኔ መጀመሪያ የተነሳሁት አማራ ለምን ተገደለ ብዬ ነው፡፡ በ1984 ዓ.ም ከፕ/ር አሥራት ጋር ለምን ህዝብ ያልቃል? ለምን ይገደላል? ብዬ ነው የተነሳሁት፡፡ በበደኖ፣ በአርባጉጉ በአማራ ላይ የደረሰ ግፍ ነው ወደ ፖለቲካው የከተተኝ፡፡ ያኔ 18 ዓመቴ ነበር፤ በወቅቱ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ ገዳዮቹም ራሳቸው ቢያዩት የሚቃወሙት ይመስለኛል:: ስለዚህ እኔ ጥሩ አማራ ነኝ፤ ጥሩ ኢትዮጵያዊም ነኝ:: አማራን ያገለለች ኢትዮጵያ፣ ትግሬን ያገለለች፣ ኦሮሞን ያገለለች ኢትዮጵያ እንድትኖር አልፈልግም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁላችንም በእኩልነት እንድንኖር እፈልጋለሁ፡፡ አማራነቴን ጠብቄ ኢትዮጵያዊነቴን ይዤ መሄድ እሻለሁ፡፡ አማራነቴን ከኢትዮጵያዊነቴ አላስበልጥም፤ኢትዮጵያዊነቴን ደግሞ ከአማራነቴ አላሳንስም፡፡ ሁለቱም በተመጣጠነ መንገድ እንዲሄዱ እፈልጋለሁ፡፡ ስለ አማራ ብዙ መከራ ተቀብያለሁ:: ምርጥ ኢትዮጵያዊ አማራ ነኝ፡፡ እኔ የምጠላው ግፈኝነትን ነው፡፡ የማስቀድመው ሰብአዊነትን ነው:: ስለዚህ ኢ-ሰብአዊነትን እቃወማለሁ፡፡ ኦነግ እና ህወሓትን ስቃወም ድርጊታቸውን ነው:: ለኔ እነዚህ ድርጅቶች ገዳዮች፣ ጨፍጫፊዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ስላወገዝኩ የአማራ ብሔርተኛ፣ የአማራ ፅንፈኛ ልሆን አልችልም፡፡ ብሆንም ብዙ አይከፋኝም:: ምክንያቱም አትግደል፣ አታሳድድ፣ አታፈናቅል ብሎ መቆም ሰብአዊነት ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ሲገደል ፊት ለፊት እቃወማለሁ፣ የትግራይ ህዝብ ሲገደል ፊት ለፊት እቃወማለሁ፡፡ እኔ ኦነግንና የኦሮሞ ህዝብን፣ ህውሓትንና የትግራይ ህዝብን አንድ አድርጌ አላይም፡፡ ደጋግሜ ህወሓትንና የትግራይ ህዝብን አትቀላቅሉ ብዬ ተቃውሜያለሁ፤ ምክንያቱም ህዝቡን አይቼዋለሁ፡፡ ያ ድሃ ህዝብ ዛሬም እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ድሃ ነው፤ ባለስልጣናቱ ግን በስሙ እያጭበረበሩና እየነገዱበት ነው፡፡ ስለዚህ እኔ ቅድሚያ ሰጥቼ የምቆመው ለሰብአዊነት ነው፡፡ በሃገሬ የህግ የበላይነት ሰፍኖ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ያለ ህግ  ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ተፈጽሞብኝ ቀምሸዋለሁ፡፡ ጌታቸው አሰፋ እኔ ላይ ግፍ ፈፅሞብኛል፤ ዛሬ እሱ በተራው ግፍ እንዲፀምበት አልፈልግም፡፡ ነገር ግን በህግ መጠየቅ አለበት፡፡ 

Read 957 times