Saturday, 25 May 2019 09:23

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩ 8 የመዲናዋ ፕሮጀክቶች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

· “አቧራውን አልፈዋለሁ፤ አሻራዬን አኖራለሁ፤ ታሪኬንም እሠራለሁ”
                     - ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ
             · 56 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻዎች ማስዋብ - 29 ሚሊዮን ብር
            · የአድዋ ማዕከል የዋጋ ግምቱ ያልታወቀ
            · 3ሺ ሰው የሚይዝ ቤ/መፃህፍት   - 1 ቢሊዮን ብር
            · የለገሃር የመኖሪያና ቢዝነስ ማዕከል  - 50 ቢሊዮን ብር

             በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚመሩና በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃሉ ተብለው የሚጠበቁ 8 የመዲናዋ ፕሮጀክቶች ሥራ እየተፋጠነ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ከተማዋን የማስዋብና የማዘመን ሥራ ያላቸውን ቁርጠኝነት በመግለጽ፤ በፕሮጀክቱ ዙሪያ ለሚቀርብባቸው ትችት ትኩረት እንደማይሰጡ ባለፈው እሁድ፣ በብሔራዊ ቤተመንግስት በተካሄደው የሸገር የእራት ፕሮግራም ላይ ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቶችን በከፊል በ“ሸገር ገበታ” ፕሮግራም ላይ ለታዳሚው ያስተዋወቁ ሲሆን ዋነኛው ግዙፍ ፕሮጀክት 56 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻን የማልማትና ከተማን የማስዋብ ሥራ፤ በአጠቃላይ 29 ቢሊዮን ብር የሚፈጅና በ3 አመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ነው፡፡
ሁለተኛው ፕሮጀክት በአዲስ አበባ አስተዳደር ም/ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ የሚመራውና ጠ/ሚኒስትሩ ክትትል የሚያደርጉበት የአድዋ ማዕከል ግንባታ ሲሆን ፕሮጀክቱ በጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ የዋጋ ግምቱም ከጨረታው በኋላ የሚታወቅ ይሆናል ተብሏል፡፡
ሶስተኛው የለገሃር የመኖሪያ መንደርና የቢዝነስ ማዕከል ሲሆን ይኸው በተባበሩት አረብ ኢምሬት ባለሀብቶች የሚገነባው ማዕከል፤ 1 ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ ይገመታል፡፡ ፕሮጀክቱም በርካታ ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎችን፣ ባለ 5 ኮከብ ሆቴሎችን፣ ግዙፍ የገበያ አዳራሾችን፣ ሲኒማ ቤቶችን፣ መዝናኛ ማዕከሎችንና ዘመናዊ የመኖሪያ መንደርን ያካትታል፡፡ በዕቅዱ መሰረት ፕሮጀክቱ በ5 አመት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አራተኛው ፕሮጀክት በአንድ ጊዜ ከ3ሺህ በላይ ሰዎችን የሚያስተናግደውና የከተማዋ መለያ (ላንድ ማርክ) ይሆናል ተብሎ የሚታሰበው ዘመናዊ ቤተ መጽሐፍት ሲሆን አሁን ፕሮጀክቱ በጨረታ ሂደት ላይ ይገኛል:: በአጠቃላይ 1ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅም ተገምቷል፡፡
አምስተኛው የኢዮቤልዩ ቤተ መንግስትና ፍልውሃን አካቶ የሚገነባው መናፈሻ ሲሆን፤ የፕሮጀክቱን ዲዛይኑን ፈረንሳውያን እየሠሩት እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ የዋጋ ግምቱ ገና አልተገለፀም፡፡
ስድስተኛው ፕሮጀክት፤ ለብሔራዊ ቤተ መንግስቱ ጐብኚዎች የመኪና ማቆሚያና የገበያ ማዕከል ግንባታ ሲሆን፤ ይህም በቤተ መንግስቱና በሒልተን ሆቴል መካከል ባለው ክፍት ቦታ ላይ የሚያርፍ ነው፡፡ ቦታው በአሁኑ ወቅት የመኪና ፓርኪንግ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፤ ግንባታውን ለማከናወን ጨረታ መውጣቱም ታውቋል፡፡
ሠባተኛው ፕሮጀክት ከሣር ቤት እስከ ጐተራ ያለው መንገድና የትራፊክ ማሳለጫ ድልድዮች ግንባታ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ በጨረታ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡
ስምንተኛው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመዲናዋ ፕሮጀክት፤ መጠኑ ባልታወቀ እና ከተባበሩት አረብ ኤምሬት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ፤ ግንባታውና እድሳቱ እየተጠናቀቀ የሚገነው ብሔራዊ የቤተ መንግስት የእንስሳት ማቆያ ፓርክ ግንባታ ነው፡፡
እነዚህ ስምንት የመዲናዋ ዋነኛ ፕሮጀክቶች ከ1 አመት እስከ 5 አመት በሚደርስ ጊዜ ግንባታቸው ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ባለፈው እሁድ ባዘጋጁት ለሸገር የ5 ሚሊዮን ብር የእራት ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የአዲስ አበባን ውበት ለማስጠበቅና ከተማዋን ለነዋሪዎች ተስማሚና ዘመናዊ ለማድረግ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለሚቀርብባቸው ትችት እምብዛም ትኩረት እንደማይሰጡ ገልፀው ከዚያ ይልቅ አሻራቸውን ለማኖርና ታሪክ ለመስራት እንደሚተጉ ገልፀዋል::
“ዛሬ ስለ አቧራና አሻራ ጉዳይ ነው የምንነጋገረው” ሲሉ ንግግራቸውን የጀመሩት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “አቧራን ማስነሳት ቀላል ነው፤ አሻራን ማኖር ግን ከባድ ነው በቀላሉ አይታይም” ብለዋል፡፡
“አሻራ የአቧራን ያህል ቶሎ አይታይም፤ ቶሎም ወደ ላይ አይነሳም፤ በቶሎም ስም አያስጠራም፤ ሃሜትና ትችት ነቀፋና ውረፋ ያስከትላል፤ ያልተረዱ እስኪረዱ፣ የተረዱ እስኪሰሩ፣ የሚሠሩ እስኪፈጽሙ ጊዜ ይወስዳል፤ ትዕግስትን ይፈታተናል በአለም ላይ የትውልድ አሻራን ያኖሩ ሁሉ ይሄ ገጥሟቸዋል” ብለዋል፡፡
ለእሳቸውና የመዲናዋን ውበት ለማስጠበቅ ለሚረባረቡ ባለሀብቶች የቀረበው ፈተና “አሻራ ወይስ አቧራ?” የሚል መሆኑንም  - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ ለሸገር ገበታ እንግዶች ተናግረዋል፡፡  
ስም የማያስጠራውን አቧራ ወደ ጐን በመተው አሻራን ማኖር እንደሚገባ ደጋግመው ያስገነዘቡት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የተጀመሩት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ብቻ ከመባል አልፋ የአፍሪካ ውብና ፅዱዋ ከተማ የምትባልበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ብለዋል፡፡
ወደዚያ የሚያደርሰው ከባዱ የመጀመሪያ እርምጃም አሃዱ ተብሎ መጀመሩን የገለፁት ዶ/ር ዐቢይ፤ ከ3ዐ አመት በኋላ ግን እርምጃዎች በሙሉ ፍሬ አፍርተው፣ ስም አስጠሪ ሃውልቶች እንደሚኖሯቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በልበ ሙሉነት ተናግረዋል - በምኒልክ አዳራሽ ለታደሙ የፕሮጀክቱ አጋሮቻቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ማጠቃለያም፤ “አቧራው ይጭስ ተውት፤ ስለእርሱ አታስቡ፤ እኛ አሻራችንን በክብር እናኖራለን፤ በክብርም በዚህች ሀገር ታሪክ እንታወሳለን” ብለዋል፡፡ ለአዲስ አበባ የማስዋብና የማዘመን ፕሮጀክት ያላቸውን ቁርጠኝነት ሲገልፁም፤ “አቧራውን አልፈዋለሁ፣ አሻራዬን አኖራለሁ፤ ታሪኬንም እሠራለሁ” ብለዋል፡፡

Read 12079 times