Print this page
Saturday, 25 May 2019 09:15

በቤንሻንጉል ክልል የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ተከለከለ

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(0 votes)

  የመንግስት ታጣቂዎችም ጦር መሳሪያ እንዳይዙ ተከልክለዋል
                                    
        የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግስት የፀጥታ ም/ቤት የክልሉን የሠላምና ፀጥታ የመደፍረስ ሁኔታ ላይ ግምገማ በማድረግ በልዩ ሁኔታ ከተፈቀደላቸው አካላት ውጪ የጦር መሳሪያም ሆነ ድምጽ አልባ መሳሪያዎችን ይዞ መንቀሳቀስን ከለከለ፡፡
ግጭት በተከሰተባቸውም ሆነ በየትኛውም የክልሉ አካባቢዎች ማንኛውንም መሳሪያ  ይዞ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ሲሆን፤ በልዩ ሁኔታ ከተፈቀደላቸው አካላት ውጪ የክልሉ ሚሊሻ አባላትም ሆኑ የቀበሌ ታጣቂዎች የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ አይችሉም ተብሏል፡፡  
በተጨማሪም በተደራጀ መንገድም ሆነ በተናጥል ወደ አማራ ክልል አዋሳኞች ጥቃት ለመፈፀም የሚደረጉ ማናቸውም አይነት እንቅስቃሴዎች በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን የገለፀው የፀጥታ ም/ቤቱ ምክር ቤቱ፤ ከመከላከያ ሠራዊትና ከፌደራል ፖሊስ ውጪ የክልሉ ልዩ ሃይልም ሆነ መደበኛ ፖሊስ በአስተዳደር ወሰን አካባቢዎች በፍፁም አይችሉም ብሏል፡፡ በአምስት ኪሎ ሜትር ራዲየስ የጦር ውስጥ መሣሪያ ይዘው መንቀሳቀስ በፍፁም አይችሉም ብሏል፡፡
የፀጥታ ም/ቤቱ እነዚህ ውሳኔዎች ለጋራ ሠላምና ፀጥታ አስፈላጊ መሆናቸውን በጥልቀት በመመርመር በመተከል ዞን፣ በዳንጉር፣ በማንዳራ፣ በፓዊና በድባጢ ወረዳዎች የተዋቀሩ ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስቶች በጥብቅ እንዲከታተሉና እንዲያስፈጽሙ መመሪያ መስጠቱን አስታውቋል፡፡
ም/ቤቱ ከነዚህ በተጨማሪ በግጭቶቹ ሳቢያ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጐች ወደቀያቸው እንዲመለሱና እንዲቋቋሙ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት ሁሉም ወገን እንዲደግፍና የአካባቢው ሠላም ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ እንዲመለስ ከክልሉ መንግስትና ከፀጥታ ሃይሉ ጋር ይበልጥ ተቀራርቦና ተቀናጅቶ እንዲሰራ በመግለጫው ጥሪ  አስተላልፏል፡፡
ከዚህ ጐን ለጐን፤ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና በብጥብጡ ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የተሳተፉ አካላትን ለህግ ለማቅረብ የተጀመረውን ጥረት ስኬታማ ለማድረግ፣ ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጐን እንዲቆም የፀጥታ ም/ቤቱ ጠይቋል፡፡

Read 1018 times