Print this page
Saturday, 25 May 2019 09:09

እርግዝናና የጀርባ አጥንት (አከርካሪ) ጉዳት

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)


             የጀርባ አጥንት ወይም አከርካሪ፣ በእንግሊዝኛው አጠራር ደግሞ (Spinal cord) ተብሎ የሚጠራው የሰውነት ክፍል ላይ አንዲት ሴት ጉዳት ቢደርስባት፣ ጉዳቱ እንስቷን ከማርገዝና ጤናማ ልጅን ከመውለድ የሚያግዳት ጉዳይ እንዳልሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ አንዲት ሴት ጉዳቱ እያለባት ማርገዝና መውለድ ቢቻላትም፣ የራሷንም ሆነ የልጇን ጤንነት ጠብቃና የከፋ ጉዳት በሁለቱም ላይ እንዳይደርስ ግን ማድረግ የሚገቧት ቅድመ ጥንቃቄዎች አሉ፡፡
የጀርባ አጥንት አሊያም አከርካሪያቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች ጤናማ በሆነ መልኩ የእርግዝና ጊዜያቸውን እንዲያጠናቅቁና ጤናማ የወሊድ ሂደት እንዲኖራቸው፤ ጽንስ ከመፈጠሩ በፊት፣ በእርግዝና ሰዓት፣ በምጥ ጊዜ፣ በወሊድ ጊዜና ከወሊድ በኋላ ባሉት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ መከናወን የሚገባቸው ቁልፍ ሂደቶች አሉ፡፡  
በርካታ ሴቶች የጀርባ አጥንት ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ የሚኖራቸው ጽንስ የመቋጠር ሂደት ጉዳቱ ሳይደርስባቸው በፊት ከሚኖረው ሂደት ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በመሆኑም አንዲት ሴት የጀርባ አጥንት ጉዳት ኖሮባት መጸነስ ብትፈልግ ልዩ የሆነ የህክምና ሂደት እንደማያስፈልጋት ይጠቀሳል፡፡ ጉዳቱ ግን ለመጸነስ ከታቀደበት ጊዜ እምብዛም ያልራቀ ከሆነ እርግዝናው እንዳይፈጠር የተወሰነ ግዜ ሊሰጥ እንደሚገባና ሴቲቱም ከጉዳቷ ቅድሚያ ልታገገም እንደሚገባ በጥናቶች ላይ ይጠቆማል፡፡
አንዲት ሴት የጀርባ አጥንት ጉዳት ከደረሰባት በኋላ የወር አበባ ዑደቷ ተፈጥሯዊ ጊዜውን ጠብቆ በየወሩ እስኪመጣ ድረስ ከሁለት እስከ ስምንት ወራት ይወስዳል፡፡ በመሆኑም ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ተገናኝቶ ጉዳቱ የደረሰባት ሴት ጉዳቱ በተከሰተ በመጀመሪያው ዓመት መጸነስ ከፈለገች ውስብስብ ችግሮች ሳይፈጠሩ በፊት ቅድሚያ ከሐኪሟ ጋር ልትነጋገር እንደሚገባ ይመከራል፡፡
እነዚህን ሂደቶች ማለፍ የቻለቸ ሴት ብትጸንስም ከደረሰባት ጉዳት እንድታገግም የምትወስዳቸው መድሃኒቶች እርግዝናዋም ላይ ሆነ ጽንሱ ላይ ምንም አይነት ችግር አለመፍጠራቸው ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ የእርግዝናው ሂደት አለምንም እንቅፋት ተሳክቶ እናቲቱ ብትወልድም ልጇን ጡት ማጥባቷ ስለሚቀጥል ለጀርባ አጥንት ጉዳቷ የምትወስደው መድሃኒት ጡት በማጥባት ሂደት ህጻኑ ላይ ጉዳት የማይፈጥር መሆኑን አሁንም በሐኪም ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት መድሃኒቶቹ የጽንሱንም ሆነ የህጻኑን እድገት ሊያስተጓጉሉ ስለሚችሉ እንደሆነ ጥናቶቹ ይጠቁማሉ፡፡ በመሆኑም ከሐኪም ጋር በሚደረግ ምክክር መሰረት ለጉዳቱ የሚወሰዱት መድሐኒቶች መጠንን መቀነስ አንድ መፍትሔ ሲሆን እንዳንድ የመድሐኒት አይነቶችንም ጭርሱን እንዳይወሰዱ ማድረግ ደግሞ ሌላው አማራጭ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ ተተኪ የመድሀኒት አይነቶችና ለጉዳቱ ተብሎ ቤት ውስጥ የሚዘጋጁ የመድሐኒት ምትኮችም ሊከለከሉ አሊያም አይነታቸው ሊቀየር እንደሚችሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ማንኛዋም ሴት በእርግዝናዋ ወቅትና ጡት በምታጠባበት ጊዜ ልትወስደው እንደሚገባው ጥንቃቄ ሁሉ፣ አንዲት ሴት የጀርባ አጥንት ጉዳት ደርሶባት የእርግዝናና ጡት የማጥባት ሂደት ላይ ከሆነች ከአልኮል መጠጥና ሲጋራን ከማጨስ ልትታቀብ ይገባል፡፡  
በእርግዝና ወቅት ጽንሱ እያደገ በመጣ ቁጥር የእናትየዋ የሽንት ፊኛ ላይ ጫና(ግፈት) ስለሚፈጥር ሁኔታው የሽንት ፊኛዋ መያዝ ከሚችለው የሽንት መጠን ያነሰ እንዲይዝ ያሰገድዳል፡፡ በዚህም ምክንያት ነፍሰጡር ሴቶች ሽንታቸውን ቶሎ ቶሎ እንዲሸኑ ይገደዳሉ ማለት ነው:: ይህ ሁኔታ የተለያዩ ምክንያቶችን ባማከለ መልኩ ከበድ ያሉ የጤና እክሎችን ሊፈጥር የሚችልባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ሁኔታዎች የከፋ ደረጃ ላይ ከደረሱ ጸንሱ ያለጊዜው እንዲወለድ ምክንያት ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የጀርባ አጥንት ጉዳት የደረሰባት ነፍሰጡር ላይ የመድረስ እድሉ ሰፊ በመሆኑ ሁኔታው የከፋ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት ከሽንት ፊኛ ጋር በተያያዘ ጠለቅ ያለ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የጀርባ አጥንት ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች የመውለጃ ጊዜያቸው እየተቃረበ በመጣ ቁጥር ጉዳት ካልደረሰባቸው ሴቶች በበለጠ የክትትል ጊዜያቸው ሊጨምር እንደሚገባ ይጠቀሳል፡፡ የከትትል ጊዜያቸው አልቆ ለመውለድ ምጥ ሲጀምራቸው፣ ለተለያዩ የህክምና ፈሳሾች ማስገቢያነት ተብሎ በታችኛው የእጅ ክፍል ባለ የደም ስር ላይ የሚቀጠለውን ኢንትሮቪነስ (አይ ቪ) ወደላይኛው የእጅ ክፍል እንዲቀየር ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ የሚረዳው ምጥ ላይ ያለችው ሴት አተኛኘቷን እንደፈለገች እንድትቀያይር ስለሚረዳትና የጀርባ አጥንቷ ላይም ጫና እንዳይፈጠር  ስለሚረዳ ነው፡፡    
የጀርባ አጥንት ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች መውለጃቸው ጊዜ ላይ ኢፒደራል አኔስቴቲክ (Epidural Anesthetic) ሊሰጣቸው እንደሚገባ ይገለጻል፡፡ በተጨማሪም ምጥ ላይ ላለችው እናት እየተከታተሉ የደም ግፊቷን መቆጣጠር ይገባል፡፡ ምጡ ጸንቶ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ ከሆነ ደግሞ እናትየዋ የተኛችበት የአካሏ ክፍል ሊፈገፈግና ህመም ሊሰማት ስለሚችል ይሄንንም ለማስወገድ ተከታታይ በሆነ መልኩ አተኛኘቷን እንድትቀያይር ማድረጉ ይመከራል፡፡
የምጡ ሂደት ተጠናቆ እናትየዋ አዲሱን ልጇን ከተገላገለች በኋላ ለቀጣይ ጥቂት ቀናትና ጥቂት ሳምንታት ልታቅድና ልትተገብራቸው የሚገቧት በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ የጀርባ አጥንት ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች ጉዳቱ ካልደረሰባቸው ሴቶች ለየት ባለ መልኩ ከወሊድ በኋላ ድካም የሚሰማቸው በመሆኑና ከወሊድ ጋር ተያያዘው ከተፈጠሩ ጉዳዮች ወላዷ ማገገም ይኖርባታል፡፡ በዚህም ምክንያት ወላዷ የተለየ ድጋፍ የሚያስፈልጋት በመሆኑ በሆስፒታል በሚኖራት ቆይታም ሆነ ወደቤቷ ከተመለሰች በኋላ ህጻኑንም ሆነ ሌሎች ልጆችን በመንከባከብ ረገድና የቤት ውስጥ ሥራዎችን በማከናወን ረገድ ሊያግዟት የሚችሉ ሰዎች ሊኖሯት ይገባል፡፡   
በወሊድ ጊዜና ከወሊድ በኋላ ባሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በወላዷ ሰውነት ላይ ለውጦች ይታያሉ፡፡ እነዚህ ለውጦች የሰውነት ማበጥና የመቁሰል ስሜትን ያካትታሉ፡፡ ቢሆንም ግን የወላዷ ሰውነት የተፈጠሩበትን ለውጦች በራሱ ጊዜ የመፈወስ ሂደቱን አከናውኖ እስከሚጨርስ ድረስ ወላዷ የምትገለገልባቸው መሰረታዊ ቁሳቁሶች ሊስተካከሉላት ይገባል፡፡ ከእነዚህ ቁሶች መካከል ለመጥቀስ ያህል ቁመቱ ረዘም ያለ የመጸዳጃ ቤት መቀመጫና ገላ መታጠቢያ ወንበሮች ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ጥንቃቄዎች መከናወን የሚገባቸው ወላዷ የጀርባ አጥንት ጉዳት ቀድሞውኑ የደረሰባት በመሆኑ ጉዳቷ የባሰ ደረጃ ላይ እንዳይደርስ ለመከላከል ሲባል ነው፡፡
ለወሊድ አዲስ የሆኑ እናቶች ከመውለድ ጋር ተያይዞ የሚመጡ የአእምሮና የስሜት ለውጦችን እንደሚያስተናግዱ ቀድሞውኑ ሊያውቁ እንደሚገባ ይመከራል፡፡ አዲስ ወላድ የሆኑ በርካታ እናቶች ያልተረጋጋ ስሜት ይኖራቸዋል፣ ብቻቸውን የተተዉ ይመስላቸዋል፣ ድጋፍ እንደሌላቸው ይሰማቸዋል እንዲሁም እራሳቸውን ከአዲሱ ልጅ ጋር ለማግባባት በሚያደርጉት ትግል ብቁ ያልሆኑ አድርገው ራሳቸውን ይወስዳሉ፡፡ የጀርባ አጥንት ጉዳት ያለባቸው ወላዶች እንቅስቃሴያቸው ስለሚገታ ቀደም ሲል የተዘረዘሩት ችግሮች በእነሱ ላይ ጎልተው ይታያሉ፡፡
በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የቤተሰብ እርዳታ፣ የህክምና ክትትልና ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ እናቶች ድጋፍ መኖሩ ከዚህ ስሜት ቶሎ ለመውጣትና ራስን ለማስተካካል እንደሚረዳ የተለያዩ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ቢሆንም ግን አንዳንድ የስሜት መዋዠቆችና ለውጦች ወላዷን ወደ ተባባሱ ሁኔታዎች ውስጥ ሊያስገቡ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች በመኖራቸው ይበልጥ ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባል፡፡ ሁኔታውንም ጠንቅቆና ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ለመፍትሔውም የህክምና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ክትትልና ህክምና ሊያደርጉ ይገባል፡፡
ከወሊድ በኋላ የሚኖረው የድብርት አይነት የጀርባ አጥንት ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች ላይ የተለመደ ሲሆን ለምልክቱም የተለያዩ አይነት ስሜቶች ይንጸባረቃሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ለመጥቀስ ራስን ያለመሆን ስሜት፣ ማዘን፣ መስጋት፣ አለመረጋጋት፣ የጥፋተኝነት ስሜት መኖር፣ የእንቅልፍ ችግር፣ ረዥም ጊዜ መተኛት፣ የረሃብ ስሜት አለመኖር፣ በአዲሱ ልጅ መበሳጨትና መናደድ፣ ስለአዲሱ ልጅ እጅግ በበዛ መልኩ መጨነቅ አሊያም ባነሰ መልኩ አለመጨነቅ ይገኙበታል፡፡
አንዲት አዲስ እናት የጀርባ አጥንት ጉዳት የነበረባትም ይሁን ያልነበረባት ከላይ የተጠቀሱትን ስሜቶች የምታስተናግድ ከሆነ የህክምና እርዳታ ቶሎ ማግኘት እንደሚኖርባትና እነዚህ ስሜቶች እሷ ብቻ የምታስተናግዳቸው አለመሆናቸውን መረዳት እንደሚገባት ጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥተው የተደረጉ ጥናቶች ያስረዳሉ:: ጥናቶቹ አያይዘውም የጀርባ አጥንት ጉዳቷ ከፍ ያለ እናት ጡት ማጥባትን በተመለከተ አካላዊ ተግዳሮት ስለሚኖርባት ሁኔታውን አስመልክቶ የህክምና ውይይት እንደሚያስፈልጋትም ይጠቅሳሉ፡፡

Read 10313 times