Saturday, 18 May 2019 00:00

የሀኪሞች ዋይታና የመንግስት ቋንቋ!

Written by  ደረጄ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

  “ሰሞኑን በሀገራችን ሀኪሞች የተነሳው ጥያቄም የተጠራቀሙ ህመሞች ጥዝጣዜ ቢኖሩትም፣ በዚህ ጊዜ ብቅ ማለቱ ግን አዲሱን የለውጥ መንግስት፣ የዴሞክራሲያዊ በሮች መከፈት ተማምኖ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በፊት የዚህ ዓይነት ጥያቄ ሲነሳ ቀጥሎ የሚመጣው አፈሙዝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ የዓመታቱን ብሶትና ቁስለት አፈረጡት፡፡--”
                
                ከአንድ ዓመት በፊት የቅርብ ወዳጄ የሆነ ሜዲካል ዶክተር፣ በከፍተኛ ህመም ተይዞ እሞት ደጃፍ ደርሶ ተመልሷል፡፡ ሥራው ስለሆነ ዘመኑን ሁሉ ከህመምተኞች ጋር ቀና ደፋ ማለት የህይወቱ አካል ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ቀና ደፋ መሀል ከታካሚ የተረጨበት ደም፣ ጤንነቱን ለከፍተኛ ችግር አጋልጦት፣ ለበርካታ ወራት በሆስፒታልና  በቤቱ ውስጥ በሞት ጣዕር ማሳለፍ ግድ ሆነበት፡፡
ደግነቱ በመንግስት ሆስፒታል ለተወሰኑ ዓመታት ካገለገለ በኋላ የራሱን የህክምና ክሊኒክ ከፍቶ ስለነበር፣ እጁ አልደረቀም፡፡ ለህክምና ከሀገር ውጭ በመሄድ ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጎ፣ የመጨረሻው የጉበት ንቅለ ተከላ ተሳክቶለት ህይወቱ ተረፈ፡፡ ይህ እንግዲህ በዐይኔ ያየሁት፣ በእጅጉ ተሰቅቄ፣ በሀዘን ውስጥ ያለፍኩበት የምወደው ሰው ታሪክ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ከዚህ የከፉ በርካታ ገጠመኞችን በጆሮዬ ሰምቻለሁ፡፡ በህክምና ሙያቸው ለሌሎች ሲሉ በሽተኛ የሆኑ፣ ቤተሰቦቻቸውን በትነው ያለፉ፣ የሰቀቀን ኑሮ የሚገፉ  ጥቂት አይደሉም፡፡ ብዙ ጊዜ የሀኪሞችን ጉድለታቸውንና ግድየለሽነታቸውን ስለምናስብ፣ ባብዛኛው እንደ ጨካኝ ነው የምናያቸው:: ዓይናችን የሰናይ ተግባር ባለቤቶች ላይ ሳይሆን፣ እኩያኑ ላይ ያርፋል:: ህመምተኞቻቸውን ሲያክሙ፣ ሲንከባከቡና አብረዋቸው ሲያምጡ፣ በሽታ እየተጋባባቸው፣ ለራሳቸው ግን የሚያሳክማቸው በማጣት የሞቱትን ማሰብ ያቅተናል፡፡ ብዙዎቹ ሌሎችን ለመርዳት ብለው ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡
ሌላው ሁልጊዜ ከአእምሮዬ የማይወጣው ዶክተር ጌትነት የሚባል አንድ (የእናቶች እናት) የሚባል ሀኪም ነው፡፡ ይህ ባለሙያ በቡታጅራ ሆስፒታል ለብዙ ዓመታት፣ እናቶችን ከሞት ሲታደግ እንደኖረ፣ የቅርቡ ሰው አጫውቶኝ ነበር፡፡ ሃኪሙ የስኳር በሽታ ታማሚ ሆኖ እንኳ፣ ያለ ዕረፍትና ያለ መታከት፣ በተጠራ ቁጥር ሁሉ፣ ከአልጋው ተነስቶ፣ ያገለግል እንደነበር ያገሩ ሰው ሁሉ ያስታውሳል:: አንድ ቀን ስኳሩ በከፍተኛ መጠን ጨምሮ ሳለ፣ የሌላ ሰው ህይወት ለማዳን ሲዳክር፣ ቀዶ ጥገናውን ሰርቶ ካጠናቀቀ በኋላ እንደወቀደ አብሮት የነበረው ሀኪም አውግቶኛል፡፡ ይህ እንደ አፈታሪክ በአድናቆት የሚጠቀስ ሰው፣ ለድሆች ከኪሱ ሳንቲም አውጥቶ መድኃኒት በመግዛት ጭምር  ይታወቃል፡፡
ይሁንና ይህ  ለህመምተኞች ፈጥኖ በመድረስ ትጋቱ የሚታወቅ ሃኪም፤ ሄፒታይተስ ቢ (አደገኛው) ይይዘዋል፡፡ ያ ለሰዎች ራሱን የሰጠ ሰው፣ በህክምና ሙያው ሳቢያ ለደረሰበት ጉዳት ማንም ሊደርስለት አልቻለም፡፡ ደሞዝ እንኳ የተከፈለው ለተወሰኑ ወራት ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ባወጣ ያውጣህ ተብሎ፣ ሚስቱና ልጆቹ የመከራውን ገፈት አብረውት ቀምሰው፣ በመከራና እንግልት ህይወቱ አልፏል፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን አጠገቡ ያሉ ሀኪሞች ያያሉ፣ በተለይ ወጣቶቹ የነገ ዕጣ ፈንታቸውን ያስባሉ፡፡ “ለእርሱ ያልሆነ መልካምነት!” ማለታቸውም አይቀርም፡፡
ሀኪሞች ነርሶችና የጤና መኮንኖችን ጨምሮ፣ ቀን ሙሉ ከህመምተኞች ጋር ላይ ታች ሲሉ ይውላሉ:: የተለያዩ ሰዎች ጠረን፣ ቁስል፣ ሽታ፣ ኡኡታ፣ ማቃሰት … ብዙ ሰቆቃዎችን ያደምጣሉ፡፡ አብረው ይሰቃያሉ፡፡ ህክምና፤ ቢሮ ተቀምጦ ባለጉዳይ እንደማነጋገር ቀላል አይደለም፡፡ ባብዛኛው የእፎይታ ጊዜ እንኳን የለም፡፡ በዚያ ላይ የሚመጣው ሰው አብዛኛው መንፈሱ ያዘነ፣ ተስፋ የቆረጠ የመረረው ስለሆነ የሚናገራቸውን ቃል የማይመርጥበት ጊዜ ጥቂት አይደለም፡፡ ይህ የቀኑ ነው፡፡ የሌሊቱ ደግሞ ሌላ ጣጣ ነው፡፡ ማታ ተረኛ ሲሆኑ፣ እንቅልፍ እያዳፋቸው ያነጋሉ፡፡ አንዳንዴም በተቀመጡበት ወንበር፣ አሊያም ባገኙት ጠረጴዛ ላይ እየባነኑ ያሸልባሉ፡፡ በተለይ እንደ አማኑኤል ሆስፒታል ያሉት ትዕግስት ፈታኝ ቦታዎችን ስናይ ደግሞ ለሀኪሞች የሚኖረን አድናቆት ይጨምራል፡፡ ቤተሰብ እንኳ የማይታገሰውን ታግሰው፣ አግባብተው፣ አንዳንዴም ተቆጥተው ወደ ጤንነት ለመመለስ ይደክማሉ፡፡  
ማንም ሰው ችግር ሲበዛበትና ሲባክን መንፈሱ አይረጋጋም፡፡ ቀኑን ሙሉ በሰዎች ስቃይ ውስጥ መዋል፣ በራሱ ከባድ ነው፡፡ በዚያ ላይ ህመምተኞችን በመርዳት ውስጥ ለህይወት አስጊ የሆኑ በሽታዎች ያጋጥማሉ፡፡ ኤችአይቪ ኤድስና ሄፒታይተስን የመሳሰሉት በሽታዎች፣ በቅርቡ የሀኪሞች ዋነኛ ስጋት እየሆኑ ነው፡፡ አሳዛኙ ነገር ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት፣ በህክምና ስራ ላይ ሳሉ በተያዙበት በሽታ ተሸንፈው ቤት ሲቀሩ እንኳ ልክ በራሳቸው እንዳመጡት ችግር ደሞዝ እንኳ አይከፈላቸውም፡፡ ዘመናቸውን ሁሉ እንዳላገለገሉ ባብዛኛው ተጥለው ይቀራሉ፡፡ ልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸውም ሌላ መከራ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡
በርግጥ ሀኪሞች እንደ ማንኛውም ሰው በሁለቱም ክንፍ አሉ፡፡ መልካም የሆኑ ለሰው የሚራሩ፣ ሰዎችን በተቻላቸው አቅም ተረባርበው ለማዳን የሚዳክሩ በአንድ በኩል ሲኖሩ፣ ሰውን ከመጤፍ የማይቆጥሩ፣  ጥሩ ቃል ከአፋቸው የማይወጣ፣ የሚገላምጡና የሚሳደቡ ሞልተዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ራሳቸው ሴቶች ሆነው ሌሎች ነፍሰ ጡሮች ምጥ ይዟቸው ወደ ሆስፒታል ገብተው ሲያምጡ፤ “መጀመሪያ ማን እግርሽን ስቀይ አለሽ!” ዓይነት የማይገባ ቃል የሚናገሩ ሁሉ አሉ፡፡ በግድየለሽነት የሰው ህይወት የሚቀጥፉ፣ ማዳን ሲቻላቸው ሰውን ያህል ትልቅ ፍጡር ለሞት የሚዳርጉም መኖራቸው አይታበልም::
እዚህ ቦታ እጓለ ገብረዮሐንስ፣ ቱቢንግ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆነውን ኤድዋርድ ሸፕራንግርን ጠቅሰው፣ የጻፉትን የሰዎች ማንነት መጥቀስ እፈልጋለሁ:: መምህሩ ሰዎችን በዝንባሌያቸው ሶስት ቦታ ይከፍሏቸዋል፡፡ ከነዚያ ውስጥ አንዱ እንዲህ ሰፍሯል፡-
“በዚህ ዓለም ሌላ ነገር አይታየውም፤ ከገንዘብና እርሱ ከሚያገኘው ተድላ በስተቀር፡፡ ይህንን homo oeconomicus ብሎ ጠርቶታል፡፡ የቁጠባ የልማት፣ የሀብት ሰው ነው፡፡ ጥረቱ ግረቱ ሀብቱን ለማዳበር ብቻ ነው፡፡ ቁር ሃሩር ሳይል፣ ባህር ተሻግሮ የብስ ቆርጦ፣ ብር ወርቅ ወዳለበት ይደርሳል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይገባውም፡፡ ለሱ ይህ ሁሉ “ፅላሎት ወህልም ነው፡፡” እንደ ጥላ እንደ ህልም ኃላፊ ነው፡፡”
ሦስተኛውን ማንሳት አያስፈልገኝም፡፡ ሁለቱ በቂ ናቸው፡፡ ከነዚህ ከሁለቱ አንዱ ለገንዘብ ብለው የሰው ህይወት ከመጤፍ የማይቆጥሩ፣ አጥንቱን ለተሰበረው ደምና ሽንት ምርመራ የሚያዝዙ፣ ህመምተኛን ከእነ ስቃዩ ትተው፣ ወደ ሌላ ሽቀላ የሚሄዱትን ይወክላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ልባቸውንና ሀሳባቸውን ሁሉ ለወገናቸው የሰጡ፣ ከሚያገኙት ገንዘብ ይልቅ ወገናቸውን መርጠው፣ የማይገባቸውን ኑሮ የሚመሩ  አሉ፡፡ ውጭ ሀገር ሄዶ የመስራት ዕድል እያላቸው፣ “ወገኔን  አገለግላሁ” ብለው መስዋዕት የሆኑም ጥቂት አይደሉም፡፡
ታዲያ እዚህ ላይ እኛ ተገልጋዮቹ በንግግራችንና በአመለካከታችን ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ብዙ ጊዜ ለእኩዮቹና ለጋጠ ወጦቹ የወረወርነው ቀስት፣ እነዚያን ስለ እኛ ጤንነት ዋጋ የሚከፍሉትንና ህይወታቸውን ሳይቀር መስዋዕት የሚያደርጉትን ቅን ልቦች  ይወጋል፡፡ የነዚህን ቅኖች ልብ መውጋት ደግሞ አገልግሎታቸው ላይ ጥላ ያጠላል፡፡ ርህራሄያቸውን ዋጋ ቢስ ሊያደርገው ይችላል፡፡  
መነሻዬ ሰሞኑን የተነሳው የሀኪሞች የክብርና የክፍያ ጥያቄ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ሆስፒታል በሄድኩ ቁጥር ድካማቸውና ስራቸው፣ ከክፍያቸው ጋር ያለመመጣጠኑ ያሳዝነኛል፡፡ ቀኑን ብቻ ሳይሆን ምሽቱን ሳይተኙ ማደራቸው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሳስበው፣ አንዳች የተሻለ ነገር እንዲያገኙ በሚል ነፍሴ ታምጣለች፡፡ ነገሩን መለስ አደርገን ወደ መንግስት ስንወስደው፣ ከዚህ ቀደም ያየናቸው መንግስታት ሁሉ ባብዛኛው ትኩረታቸው፣ ስልጣናቸውን እንዴት እንደሚያራዝሙ በማስላት ላይ ነበር፡፡ ደርግ ለየትኛውም ጥያቄ “ፀረ ህዝብ” በሚል አፈሙዝ የሚነቀንቅ፣ ሽጉጥ የሚመዝ ነው:: “ለእናት ሀገርህ እንኳን መስራት መሞት አለብህ!” ባይ ነው፡፡ ሞት ያኔ ቀላል ነው፡፡ ሀኪሙ ያኔም ቢሆን መከራውን አይቷል!
ወያኔ/ኢሕአዴግ ሲመጣ በአፈ ሙዝ መጥቶ፣ በአፈ ሙዝ የመቆየት ህልም ስለነበረው የእርሱም ትኩረት፣ ዕድሜ ማራዘም ነበር፡፡ የእርሱ ትንሽ የሚለየው፣ በብሔር ከፋፍሎ፣ ለአንዱ የተመቸች፣ ለሌላው የሰቀቀች ሀገር መፍጠሩ ነው፡፡ እርሱም እንደ ታላቅ ወንድሙ ለጥያቄ የሚለጥፈው ታርጋ፣ የሚሰጠው ስም አለው፤ “ፀረ ልማት! ፀረ ሰላም!” ይልና ወህኒ ይወረውራል፡፡ ያኛው በጥይት፣ ይህኛው በቁም ይገድላል!
ያየናቸው መንግስታት እጃቸው የሚፈታው፣ ፖለቲካቸውን ለሚያቀነቅኑላቸው ካድሬዎችና በየወረዳውና ቀበሌው ለሾሟቸው ካቢኔዎች ነው:: ወያኔ/ኢሕአዴግ ፖለቲካውን “አሜን” ብለው ለተቀበሉ ካድሬዎቹ ብር ዘግኖ ሲሰጥ እልል እያለ ነው፡፡ በየቢሮው የተቀመጡት የየዘርፉ ኃላፊዎችም የአንድ ወር አበል አልበቃ ብሏቸው፣ በተለያዩ ሰዎች ስም ካዝና ሲያራቁቱ ቅር አይለውም፡፡ የራሱ ቡችሎች ናቸዋ! ነገ በእርሱ እግር ተተክተው፣ መርዙን ለትውልድ የሚያቀብሉ፣ ቢጤዎቹን ለማን ይጥላቸዋል?
በነገራችን ላይ ይህ ዘረፋ በየወረዳው ብንሄድ ዛሬም አልተለወጠም፡፡ ምናልባት በጊዜው ያሉት የፖለቲካ ውጥረቶች ሰከን ሲሉ፣ የለውጡ መንግስት ያስተካክለዋል የሚል እምነት ወይም ምኞት አለኝ፡፡ ምክንያቱም የመንግስት ኃላፊነት ሀገሩን ማስተዳደርና ፍትህና እኩልነትን ማስፈን ነዋ! … ዛሬ በሰፈር ተወስነው ባንድ ጉዳይ ላይ ብቻ የሚያላዝኑት ፕሬሶችና መገናኛ ብዙኃን፣ እግራቸውን ፈትተው ይህንን ጉዳይ ይመረምራሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ኩዋኔ ብራንድሌይ እንዳለው፤ “The business of the government is governing the country. The business of the press is reporting the news” ነው፡፡
ከላይ እንደጠቀስኩት የመንግስት ገንዘብ በካድሬዎችና በዘራፊዎች ሲበላ፣ ደም እየተፋ የሚሰራውና ከቁስልና ከስቃይ ጋር የሚንገላታው የህክምና ባለሙያ፣ የቤት ኪራዩን ከፍሎ፣ ልጆቹን የሚያስተምርበት አቅም ሲያጣ ይስተዋላል፡፡ ሰሞኑን በሀገራችን ሀኪሞች የተነሳው ጥያቄም የተጠራቀሙ ህመሞች ጥዝጣዜ ቢኖሩትም፣ በዚህ ጊዜ ብቅ ማለቱ ግን አዲሱን የለውጥ መንግስት፣ የዴሞክራሲያዊ በሮች መከፈት ተማምኖ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በፊት የዚህ ዓይነት ጥያቄ ሲነሳ ቀጥሎ የሚመጣው አፈሙዝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ የዓመታቱን ብሶትና ቁስለት አፈረጡት፡፡ የጤና ባለሙያዎቹ ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ደረጃውን የጠበቀ፣ ከደረጃም በታች የሆነ ጥያቄ ተነስቷል:: ይሁን እንጂ ከሞላ ጎደል እውነትነት ያለው ነው:: ሌላው ቀርቶ የህክምና ማዕከላቱ በቂ የመገልገያ መሳሪያ ሳይኖራቸው፣ ለፖለቲካ ፍጆታና ለሪፖርት ከርስ መሙያ ሲባል፣ ጣሪያና ግድግዳቸውን የገተሩ ናቸው፡፡
ዛሬ ሀገሪቱ ያለችበት የሽግግር ሁኔታ ጥያቄዎቻቸውን ሁሉ ለመመለስ የሚያበቁ አይደሉም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሀኪሞቹ ጋር የነበራቸው ቆይታ፣ ጉዳዩን ለፖለቲካ መጠቀሚያነት ሊያጦዙት የሚሞክሩትን ያህል መጥፎ አልነበረም፡፡ ለቀረቡት ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክንያት ላይ የተመሰረተ ምላሽ የሰጡ ይመስለኛል፡፡ በፍቅርና ለድካማቸው ዕውቅና በመስጠት የታጀበ ቢሆን ደግሞ ይበልጥ ጥሩ ይሆን  ነበር፡፡ ግን ደግሞ እሳቸውም ባገሪቱ ሺህ ጣጣ ታክተውና ተሰላችተው ሊሆን እንደሚችል ማሰብም ደግ ነው፡፡   
ሀኪሞቹስ ለዚህ የጠቅላዩ ምላሽ ስራ በማቆም አፀፌታውን መመለስ ነበረባቸው? በበኩሌ አይመስለኝም፡፡ ብዙ የታገሱትን ያህል አድማ በመቱ ቀን አብሯቸው የቆመውን ህዝብ ባለማከም ራሳቸውን ማስገመት አልነበረባቸውም፡፡ ሀኪሞቹ የሚጎዱት እንደ ልባቸው ባንኮክና ህንድ ወይም አሜሪካ እያማረጡ የሚታከሙትን ባለስልጣናት ሳይሆን ደሀ ወገናቸውን እንደሆነ ማሰብ አያዳግታቸውም፡፡ ጣዕር ላይ ያለን ሰው ሆስፒታል አልጋ ላይ ጥሎ፣ ለመብትና ጥቅም መጮህ፣ በሰው ልጆች ህሊና የሚፈጥረው መጎርበጥ ቀላል አይደለም፡፡ እንደኔ እንደኔ የስራ ማቆም አድማው አውዱንና ጊዜውን የጠበቀ አይደለም፡፡   
አዎ ለውጥ ያስፈልጋቸዋል፤ የተወሰኑ ማሻሻያዎች ይገባቸዋል፡፡ በተለይ በተለይ በህክምና ስራ ላይ ታምመው ሲወድቁ ደሞዛቸው የመቋረጡ ጉዳይ በእጅጉ ያሳምማል! የተለየ ስራ ለሚሰሩ የተለየ ጥቅምና ክፍያ ሊያገኙ  ይገባል! “ሀገሪቱ ድሃ ናት” ለሚለው መልስ ግን “ካድሬዎቻችሁ ከሚዘርፉት አበልና ደሞዝ ላይ ቀንሳችሁ ለጥቂት ሀኪሞች መክፈል መልመድ አለባችሁ! … የየስብሰባውን ድግስና ግብዣም ቀንሱና ለሀኪሙ ክፈሉት!” የሚል ነው ሀሳቤ!
ለቅኖቹ ሀኪሞች አድናቆቴን ሰጥቼ፣ ለአልማጭ ሀኪሞች የገጣሚ ወንድዬ ዓሊን ግጥም እጋብዛለሁ:: እነሆ፡-
አንዳንዴ ግን … አንዳንደዜ፣
ብቻ አንዳንድ ጊዜ፣
ስንዴው … እንክርዳድ ያበቅላል፣  
ርሚጦ … ረመጥ ያነዳል፣
ሰንበሌጥ … ገደል ይንዳል፣
አይቀሬነቱ የማይቀር … ዝንጋኤ ያልነቃች ለታ፣
የዘመን ድጥ የማይቀና … መስሎ ሚታይ የዐይን ቧልታ
    እኮ … አንዳንደዜ
ሽው … ሲል - ድንዛዜ፣
ስንዴው … እንከርዳድ ያበቅላል፣
ርሚጦ … ረመጥ ያነዳል፣
ሰንበሌጥ … ገደል ይንዳል፡፡
ስለዚህ ጥንቃቄ … ማስተዋል … አርቆ ማሰብ … ለሀኪሞችም፣ ለመንግስትም!!

Read 1767 times