Saturday, 18 May 2019 00:00

የአድማስ ትውስታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ከአዘጋጁ፡-
   ጋዜጣችን አዲስ አድማስ የተመሰረተችበትን 20ኛ ዓመት ከጥቂት ወራት በኋላ ታከብራለች:: የመጀመሪያው የአዲስ አድማስ ዕትም፣ ቅዳሜ ታህሳስ 29 ቀን 1992 ዓ.ም ነበር ለአንባብያን የደረሰው፡፡ ወደ 20ኛው ዓመት በዓላችን በሚያዳርሱን ጥቂት ወራት “የአድማስ ትውስታ” በሚል በሰየምነው በዚህ አዲስ ዓምድ፤ ከቀድሞ ዕትሞች እየመረጥን ጊዜውንና ጋዜጣችንን እናስታውሳችኋለን፡፡

                           አንዳንዴ እብዶችም ጤነኞች ናቸው
                                   ዘካሪያስ አትክልት

             አማኑኤል ሆስፒታል ለሦስተኛ ጊዜ ሄጃለሁ። በሽተኛ ደግፌ ነበር ወደ ሆስፒታሉ የዘለቅኩት:: እንደ ከዚህ በፊቱ ግራ አልገባኝም፡፡ በቃ! ፍርሀት የለ፤ ድንጋጤ የለ፤ ቸስ ነበር ያልኩት:: እማስታምማቸውን አያቴን ወረፋ አይስዤ ወደ መታከሚያ ክፍል አስገባኋቸው፡፡ ብቻዬን ነኝ፡፡ መቶ ብር የለኝ፣ ሀምሳ ብር የለኝ፣ እንዲሁ አንዳንድ ብሮችን ታቅፌ - ብቻዬን:: ቦነት ሚሠማኝ ስቸስት ነው፡፡ ብር ሲጠፋ፣ የደሞዝ ቀን ሲርቅ! አቤት ያን ጊዜ እኔና እኔ ብቻ ምንሆንበት፡፡ ሣቢ ሲኖርማ ጀለሦች ብዙ፣ ሆቴሎች ብዙ … ወይኔ ብር! ብቸኝነቴን ለማርከስ ሠዎች ወደተቀመጡበት መጠለያ አመራሁ፡፡ ገና ቁጭ ከማለቴ ቱታ የለበሰ ታማሚ አጠገቤ መጣ፤ “ጀለሴ ተማሪ ነህ አይደል?” ጠየቀኝ፡፡
ቱታ መልበስ የአዕምሮ እክል ያለባቸው ታማሚዎች ምልክት መሆኑን ስለማውቅ “አዎ” አልኩት፤ በደፈናው ለመጨረስ፡፡
 “የት ነህ?” ብሎ ካጠገቤ ተቀመጠ፡፡
“እዚህ” አልኩት፤ በቸልታ፡፡
 “ካለባበስህና ከጠጉርህ ጋር ፊሎ እንደምታጠና ታውቆኛል፡፡” አለኝ፡፡
ዝም አልኩት፡፡
 “የሚገርምህ እኔም ፍልስፍና ነው እዚህ ያመጣኝ፤ ኦሾ፣ ክርስቶስ፣ ኒቼ ተፈላሠፏ፡፡ የኔ ግን--- የኔ ይለያል፡፡ የራሴ ፍልስፍና ከስብሀት የተለየ አለኝ” አለኝ፤ የተንዠረገገ ጢሙን እየፈተለ፡፡
… አይኑን ወለሉ ላይ ተክሎ ፀጥ አለ፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ፤ “What is Philosophy?” ብሎ ጠየቀኝ፡፡ “Philosophy is love of wisdom” መለስኩለት፡፡
ጨበጠኝ፡፡ ተጨባበጥን፡፡ «መጣሁ ጠብቀኝ» ብሎኝ ትቶኝ ሄደ፡፡
ከተቀመጥኩበት መጠለያ ፊት ለፊት ወደ አስራ አምስት ቱታ የለበሱና ጥቂት “ሲቢል” ታማሚ ወንዶች ይታዩኛል፡፡ ሁሉም ስራ ያለባቸው ይመስል ከግራ ወደ ቀኝ፤ ከውስጥ ወደ በረንዳው ይወጣሉ፤ ይገባሉ፡፡ አካሄዳቸው አቀማመጣቸው … ሁሉ ነገራቸው ይገርማል፡፡ ፍዝዝ ብዬ እየሾፍኩ ነው:: “ኢትዮጵያ ትቅደም፡፡ ኢትዮጵያ ትቅደም” እያለ ወታደራዊ አካሄድ የሚሄድ ጐልማሳ ቀልቤን ሳበው:: ይሄድ ይሄድና፣ ሁለት እግሮቹን ገጥሞ ከተረከዙ ከፍ ይልና፣ ቀኝ እጁን ግንባሩ ላይ ተክሎ፣ ወታደራዊ ሠላምታ ያሳያል፡፡ “ጓድ ምን ልታዘዝ?” ይጠይቃል:: ማንም ካጠገቡ የለም፡፡ ከአፍታ በኋላ “እሺ እሺ” ይላል፡፡ ቆይቶ ልክ እንደ ኮረኮሩት ህፃን ከት ብሎ ይስቃል፡፡ …
“አንድ ብር አለህ?” አሉኝ፤ ቅጥን ያሉ ሽበታም ሽማግሌ፡፡
 “አዎ” አልኳቸው፡፡
“ስጠኝ?” ሰጠኋቸው፡፡ ሄዱ፡፡ ሲሄዱ እግራቸውን ደረጃ እንደሚያወርዱ ዓይነት በጥንቃቄ ከጉልበታቸው ሰበር እያደረጉ፣ ሁለት እጃቸውን በተራ እያፈራረቁ፣ አየሩን ይቀዝፉታል፡፡ አየር ላይ የሚዋኙ እንጂ የሚራመዱ አይመስሉም፡፡
“ጀለሴ ጥዬህ ጭልጥ ልበል? ምን ላድርግ ብለህ ነው፤ ፈለጥ ፈለጥ (መቀፈል ወይም ዲሞክራሲያዊ ልመና) ለማጨስ ነው፡፡” ቅድም ካጠገቤ የነበረው ወጣት ታካሚ፣ አፍታ ሳይሰጠኝ በዚያው ቀጠለ፤ “መቀሌ ዩኒቨርስቲ የmanagement ተማሪ ነበርኩ:: ሁለት ሴሚስተር Four ዘግቻለሁ፡፡ ጋንጃ  ስነፋ ተምታታብኝና እዚህ ላኩኝ፡፡ እኔ ግን ጤነኛ ነኝ፡፡ ለሲጋራ ኤካ ላኪ?” ሰጠሁት፡፡ ሲጋራ ገዝቶ መጣ:: ብቻውን ሣይሆን ሁለት ጓደኞቹን ጨምሮ ነበር:: “ተማሪ ነው ተዋወቁት፡፡” አላቸው፡፡ ተዋወቅን፤ ካስዬ፣ ዮናስ፣ ዘካሪያስ፡፡
 “ያንተን ስም’ኮ አልነገርከኝም?” አልኩት፡፡
“ቤንጃሚን፣ ኬቲ፣ ሸበላው፣ አህመድ… ብለህ ብትጠራኝ ሁሉም ያውቀኛል እሺ my brother from another mother!” አለ፡፡ ሣቅሁኝ፡፡ «Ok! My brother from another mother» አልኩት፤ እየሣቅኩኝ፡፡
“ካሴ ቀልድ ይነገራት?” አለ ቤንጃሚን፣ ኬቲ፣ ሸበላው፣ አህመድ፡፡
“የትኛው ይነገረው?” ጠየቀ ካሴ፡፡
 “ቆይ የጥንቱን ልንገረው፡፡” አለ፤ የመጀመሪያው ባለ አራት ስሙ፡፡  ለጨዋታው ደርዝ አንዱን ስም መርጬ እቀጥላለሁ፡፡
“አዎ”
“አንድ በጣም ቀጭን ወጣት ነበር፡፡ ጫካ ገብቶ ጅብ በላው፡፡ እናትየው ልጄን ጅብ በላብኝ ብላ ላካባቢው ዳኛ ታመለክታለች፡፡ ዳኛውም “ከመቼ ወዲህ ነው ሸንኮራን ጅብ የሚበላው?” አላት፤ ሣቅን … ሌላ ቀልድ ቀጠለ፡፡
“አንድ ሊስትሮ ገንዘብ አጠራቅሞ ቡና ቤት ይሄዳል፡፡ አንድ ሁለት ሲል ሞቅ ይለዋል፡፡ ‘ነይ አንቺ’ ይልና ቺኳን (ሸሌዋን) ይጋብዛል፡፡ ተመቸችው:: ‘እሙ አዳር ስንት ነው?’ ይላታል፡፡ ‘ስድስት መቶ  ብር’ … ከስንት ክርክር በኋላ ‘ወንዳ ወንድነትህ ስለማረከኝ፣ አንድ መቶ ብር ብቻ ትከፍላለህ’ ትለዋለች፡፡ ‘ኧረ! Sister ትንሽ ቀንሺ’ ሲላት ቱግ ብላ፣ «ካልቻልከ ከቀበሌ የነፃ ወረቀት አጽፈህ ና” አለችው” በጋራ ሣቅን፡፡
ቦርጫም ጐልማሣ ታማሚ እየሮጠ ወደ ተቀመጥንበት ወንበር መጣ፡፡ “ቤንጃሚን፣ ዮናስ፣ ካሴ፣ ዴች ተቀፈለ፡፡ ቡ… ቡና… ቡ… ቡቡና ይጠጣል” አለ፤ በእልህ፡፡ “ሴት ፐ! … ዴች!” እየተባባሉ ወደ ህሙማን መዝናኛ ካፍቴሪያ መሄድ ጀመሩ፡፡ ሙዳቸው ተመችቶኛል፡፡ ቢጠሩኝ እያልኩ ሳስብ “ጀለሴ፤ ለአንድ ቀን ብታብድ ቅር ይልሀል?” አለኝ ቤንጃሚን፤ የአብረን እንሂድ ምልክት እያሣየ፡፡ አመነታሁ፡፡ ልሂድ አልሂድ፤ ብሄድ ይመቱኛል፣ ይገሉኛል ወይስ የናፈቀኝን አዲስ ዓለም ያሳዩኛል … ብሄድ ብዬ በመከራ ወስኜ አብሬያቸው ሄድኩ፡፡
ካፍቴሪያቸው ገባን፡፡ ካፍቴሪያዋ ውስጥ ካንዲት ቡና ከምታፈላ ሴት በቀር ማንም የለም፡፡ መግቢያዋ ጋ ለሁለት ትከፈላለች - ካፌና ሬስቶራንት ዓይነት ነገር መሠለኝ፡፡ መከፈያዋ መለስተኛ ሱቅ ነች፡፡ ከሱቋ ግርጌ እስከ ግድግዳው ያለው ቦታ በኮንበርሣቶ ተሞልቷል፡፡ … ወገግ ያለ ብርሀን የሌላት፣ አፈር አፈር እምትሸት ካፍቴሪያ፡፡ ተቀመጥን፤ አምስት ቱታ የለበሱ ህሙማንና እኔ፡፡ ከገባሁ በኋላ ፈራኋቸው:: ምን ዓይነት ድፍረትና ራስን መጣል ነው እዚህ ያመጣኝ --- ምናምን እያልኩ ራሴን ወቀስኩት:: በተለይ ከፊቴ የተቀመጠውን ታማሚ ሳይ ልቤ ተንጫጫች፡፡ ጥቁር ነው፤ ሙሉ ጥቁር፡፡ ራሱን ሊያንቅ ሲሞክር አንገቱን የሞዠለቀው በቀጭኑ ያንገቱን ስጋ ያሣያል፡፡
መደናገጤን አይቶ ነው መሠለኝ፤ “ጀለሴ ጀግና ነህ” አለኝ፤ ቤንጃሚን፡፡
ፍርሀቴን ገድዬ፤ “በዚህ ሠውነት ጀግና ይኮናል!” አልኩት፤ ተከታትለው የሚገቡ ታማሚዎችን በፍርሀት እያስተዋልኩ፡፡
“ልብ ነው፤ የጀግንነት መሠረቱ፡፡ ጐሊያድን የጣለው እረኛው ዳዊት አይደለም” አለ፤ እየሣቀ፡፡
በሀሣቡ ተጽናናሁ፡፡ ያ እረጃ በጠጠር ጥሩር የለበሰውን ከጣለ፣ እኔም አንድ ሁለቱን በቡጢ ዘርሬ ወይም ሮጬ ማምለጥ አያቅተኝም ብዬ ለመጫወት ተመቻቸሁ፡፡ ቡናው ቀረበ፡፡ ሁላችንም ያዝን፡፡
“ተጫወት እንጂ ወንድማችን?” አለኝ፤ ካስዬ ብሎ ራሱን ያስተዋወቀኝ፡፡
ፈራ ተባ እያልኩ፤ “እ … እ ምን አመጣህ ወደዚህ?” አልኩት፡፡
“ጃንቦ ጉድ አረገኝ፡፡ ጠዋት አራት ሠዓት ጀምሬ ሌት ድረስ እቀመቅምልሀለሁ፡፡ ፉዞ ሳያረገኝ ይቀራል ብለህ ነው፡፡ አንድ ሁለት ወር Substance ለማስወጣት ብዬ ነው የመጣሁት” አለ፡፡
ቤንጃሚን ሲጋራ ያጤሳል፡፡ አንዱ የራሱን ጂም ፈጥሮ ቁጭ ብድግ ይሰራል፡፡ ሌላኛው ከንፈሩን እያንቀሳቀሰ ሌሎችን በማይረብሽ አኳኋን ያወራል፡፡ ሌላው ይስቃል፡፡ ቁጭ ብድግ የሚሰራውን እያየሁ፤ “ቤንጃሚን ይህ ምን የሚሉት ስፖርት ነው?” አልኩት፡፡
 “ማርሻል አርት ጀምሮ ነው የለቀቀው፡፡” አለኝ፡፡
“እንዴት?” ጠየኩት፡፡
“እንዴት እንዴት ትላለህ? ማርሻል አርት መማር ጀመረ፡፡ የሆነች Bird ቺክ ሾፈ፤ ፎነቀቀ፤ ነቀለ::” ሣቅሁኝ፡፡ ከት ብዬ ሣቅሁኝ፡፡ ጨዋታችንን የሠሙም፤ ያልሠሙም በህብረት ሣቁ፡፡ ከቡና አፍይዋ በስተቀር ሁሉም ከት ብሎ ሣቀ፡፡ ደነገጥኩ:: ‘ፀጥ አልኩ፡፡ አሁንም ይስቃሉ፡፡ ካ-- ካ-- ካ-- ካ፡፡’
“ካሴ የሆነ ጫወታ ጣል አርግ እንጂ ሣቁ እንዳይደበዝዝ” አለ ቤንጃሚን፡፡
“የትሪሱ፣ የቅምቅሞን፣ የሸበጡን የቱን ልንገረው?” ካሴ ጠየቀ፡፡
 “በናትህ እኔ የቅምቅሞውን ልንገረው፡፡” አለ ዮናስ፡፡
“እየውልህ ጀለስ! አንዱ ከጀለሡ ጋር ይቀመቅማል፡፡ አንድ ሁለት ይሉና ይደንሣሉ:: ያስነኩታል፡፡ አንዱ ጋባዥ ሌላው ተጋባዥ ነበር፡፡ አንዱ ከገፋ በኋላ ያስነኩታል፡፡ ዳንሡ ያልጣመው ተጋባዥ፣ የጋባዡን ስሜት ለመጠበቅ ያስነካዋል፡፡ በነጋታው “ትላንት ጋበዝኩህ አይደል” ይላል፤ ጋባዡ “ኧረ ባክህ በላቤ ነው የጠጣሁት” አለው ተጋባዡ:: ሣቅን … ካ … ካ … በመደነስ ያወጣው ላብ … ካ … ካ….፡፡ ”
አያቴ ትውስ አሉኝ፡፡ ተነሣሁ፡፡ “ጀለሶች እጠይቃችኋለሁ፡፡ በቃ ቻዎ!” ብዬ ብሮቼን አደራጅቼ፣ አስር ብር ለቡና ልከፍል ስል “ኧረ ተማሪ ነህ፡፡ እኛ ነን እምንከፍለው፡፡” ምናምን አሉ:: በስንት ጭቅጭቅ ከፍዬ ሁሉንም አቅፌ ወጣሁ፡፡
በቅጽበት ትውውቅ በአዕምሮ ህሙማን መሀል ያለውን ፍቅር አየሁ፡፡ የምወደውን ቡና በጋራ ጠጣሁ፡፡ በልክፈል አትክፈል ንትርካችን ደቂቃዎች ቢያልፉም፣ የእነርሱ ትህትናዊ ፍቅር ልቤን ነካው:: ለምነው ተካፍለው እሚበሉ፣ እሚጋብዙ፣ መሆናቸው ደነቀኝ፡፡ አንዳንዴ ዕብዶች ጤነኞች ናቸው ብንል ሳያስኬደን አይቀርም፡፡
አያቴ ገና ህክምና ላይ ናቸው፡፡ ተመልሼ መጠለያው ጋ ተቀመጥኩ፡፡ ከፊቴ ሦስት ታማሚዎች ቆመዋል፡፡ አንዱ ሲጋራ ያጤሣል:: ሁለቱ ሲጋራዋን ትክ ብለው ያዩዋታል፡፡ ምጥጥ ሲያደርጓት ደማቸውን የመጠጧቸው ይመስል ፊታቸውን ቁምጭጭ ያደርጉታል፡፡ “አስጭሰና” ይላል አንደኛው፡፡ “ቆይ መቼ ጀመርኩትና ነው እማስጨስህ” ብሎ መለሠ፤ የሲጋራው ባለቤት፡፡ ተስፋ በቆረጠ ስሜት ሲጋራዋን ያዩዋታል፡፡ አንዱ ተናዶ “በእጅህ እንዳለ አስበኝ” ብሎ በእጁ እንዳለ ስቦ፣ መንገዱን ቀጠለ፡፡ ሌላው ተስፋ ቆርጦ፣ በዓይኑ ብር እሚለምነውን ሰው መፈለግ ያዘ፡፡
አማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ ወርቅ፣ ጥሩ አለባበስ፣ ቄንጠኛ ሞባይል ወዘተ … ዋጋ የላቸውም:: ሲጋራ የያዘ ብቻ ነው፤ ሀብታም፡፡ በረንዳው ላይ ከሠፈሩት አብዛኞቹ ሲጋራ ሲመጡ ማየት የተለመደ ነው፡፡
ትህትና፣ ቅንነት፣ ታታሪነትና አዋቂነት የተጐናፀፉትን የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ሳላመሰግን ባልፍ ጽሁፌን ጐደሎ ያደርጋታልና ተመስገኑ፡፡ ፈጣሪ ጥበብን አብዝቶ ይስጣችሁ!
Saturday, 01 September 2012 10:42

Read 571 times