Saturday, 18 May 2019 00:00

የጠቅላይ ሚኒስትሩ እራት - በቤተ-መንግሥት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)


                   - “ፕሮጀክቱ ለመጪው ትውልድ ሃውልት የማቆም ያህል ነው” - ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ
                   - እስካሁን 5 ቢ. ብር ገደማ ተሰባስቧል

           በነገው ዕለት “ለሸገር ውበት” በተዘጋጀው የእራት ገበታ ላይ 5ሚ. ብር ከፍለው በቤተመንግስት የሚታደሙ እንግዶች አሁንም እየተመዘገቡ ሲሆን፤ በአጠቃላይ አንድ ሺህ ያህል ባለሃብቶችና የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እንዲሁም የኩባንያ ተወካዮች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለእንግዶች በብሔራዊ ቤተመንግስት ልዩ የጉብኝት መርሃ ግብር መዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡
ከሸገር የእራት መርሃ ግብር በፊት ከጠዋት ጀምሮ የተለያዩ ሸገርን ከማስዋብ ጋር የተያያዙ መርሃ ግብሮች እንደሚከናወኑ ለአዲስ አድማስ የገለፁት የጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ፕሬስ ሰክሬታሪ አቶ ንጉሡ ጥላሁን፤ በጠዋቱ ጠ/ሚኒስትሩ በሚገኙበት በ“አዲስ አበባን እናጽዳ” መርሃ ግብር መሠረት ጽዳት ይካሄዳል ብለዋል፡፡
ከሰዓት በኋላ ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በ“ገበታ ለሸገር” ለመታደም ወንበር የገዙ ኢትዮጵያውያን ባለሀብት፣ የውጭ ሃገር ዜጐች፣ የተቋማት ተወካዮችና አምባሳደሮች፣ በቤተ መንግሥት ተገኝተው ጉብኝት ያደርጋሉ ብለዋል - አቶ ንጉሡ፡፡
እስከዛሬ ለዜጐች ድብቅ ሆነው የቆዩ የቤተመንግስቱ የታሪክ መዘከሪያዎች ለሸገር ገበታ ታዳሚዎች ይታያሉ ያሉት የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊው፤ የአፄ ምኒልክ ቤተመንግስት፣ የአፄ ምኒልክ የግብር አዳራሽ፣ የዙፋን ችሎትና ልዩ ልዩ ታሪክ ሲሠራባቸው የነበሩ ክፍሎች ይጐበኛሉ ብለዋል፡፡
ከጉብኝቱ በኋላ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ጠ/ሚኒስትሩ በተገኙበት የ5 ሚሊዮን ብር የሸገር እራቱ ከ5ሺህ ሰው በላይ ማስተናገድ እንደሚችል በሚነገርለትና ሙሉ ዕድሳት በተደረገለት ታሪካዊው የአፄ ምኒልክ የግብር አዳራሽ ይከናወናል ተብሏል፡፡
በሸገር የእራት መርሃ ግብር ላይ ለመታደም ከአንድ ሳምንት በፊት ከ200 በላይ ሰዎች መፈረማቸውን የጠቆሙት አቶ ንጉሱ፤ ከዚያ ወዲህ ግን በየቀኑ በርካቶች እየተመዘገቡ መሰንበታቸውን ተናግረዋል - አጠቃላይ ቁጥራቸውን ለመግለፅ ባይችሉም፡፡
“ከተማችንን እናጽዳ፤ ሸገርን እናስውብ” ከሚለው አጀንዳ ጀርባም የአስተሳሰብ መቆሸሽን የማጽዳትና በጐ አስተሳሰብን በህብረተሰቡ ውስጥ የማስረፅና የማጐልበት ዓላማ እንዳለ የጠቆሙት አቶ ንጉሡ፤ የአካባቢ ጽዳቱ እንደ ባህል መዳበር አለበት ብለዋል፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ መሬት ያለውን ቆሻሻ በእጃችን ስናፀዳ አስተሳሰባችን ላይ ያለውን የቂም በቀል፣ የቁርሾና የጥላቻ ቆሻሻ በውይይት፣ በፍቅር፣ በይቅርታና በሠላም ማጽዳት ያስፈልጋል ብለዋል - አቶ ንጉሡ፡፡
በዚህ መርሃ ግብር ላይ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም፣ የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ የመሳሰሉ አለማቀፍ ተቋማትን ጨምሮ የጣሊያን፣ የቻይናና የሌሎች ሀገራት መንግስታትና አምባሳደሮች ተሣታፊ መሆናቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶችም በፕሮጀክቱ ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ያላቸው ሲሆን ከባለሀብቶች መካከል ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ፣ አቶ በላይነህ ክንዴ፣ አቶ ወርቁ አይተነውን የመሳሰሉ በእራት መርሃ ግብሩ ላይ ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል ራሳቸው ወይም በተወካዮቻቸው በኩል፡፡
በሦስት ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል የተባለው የሸገር ፕሮጀክት፣ 29 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ የተገለፀ ሲሆን እስካሁን ወደ 5 ቢሊዮን ብር ያህል ገንዘብ መሰብሰቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በፕሮጀክቱ ዕቅድ መሰረት፤ ከሸራተን አጠገብ ባለው ቦታ ላይ በአንድ ጊዜ 100ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል የሙዚቃ ኮንሰርትና የተለያዩ ህዝባዊ ዝግጅቶች ማከናወኛ አደባባይ የሚገነባ ሲሆን በአንድ ጊዜ 3ሺህ ያህል የሚያስተናግድ ዲጂታል ቤተ መጽሐፍትም ይኖረዋል ተብሏል፡፡
የቤተመንግስቱን እድሳትና ማስዋብ ጨምሮ የወንዝ ዳርቻው ልማት ንድፍ በአመዛኙ በኢትዮጵያውያን የንድፍ ባለሙያዎች መዘጋጀቱንም አቶ ንጉሡ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ከእንጦጦ እስከ አቃቂ የሚዘረጋው 56 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ ልማት ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ባሉት የሦስት ዓመታት ጊዜያት ውስጥ ፕሮጀክት ከ10ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥርም ታውቋል፡፡
በወንዝ ዳርቻ ልማቱ ሰው ሰራሽ ኩሬዎች የሚፈጠሩ ሲሆን፤ በኩሬዎቹ ዳርቻም የተለያዩ መናፈሻዎችና የብስክሌት ማሽከርከሪያ መንገዶች ይገነባሉ፡፡ ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ ለህዝብ ክፍት የሚደረገው የቤተ መንግስቱ መናፈሻም የእንስሳት ፓርኩን ጨምሮ የህፃናት የመጫወቻ ሥፍራ እንደሚኖረው ታውቋል:: ፕሮጀክቱ የከተማዋን ከማዘመንና ውበት ከማላበስ ባሻገር የወንዝ ዳርቻ ሪል ስቴትንም ያስፋፋል ተብሏል፡፡  
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠንሳሽነት የተጀመረው ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት፤ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የአለማቀፍ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ መቀመጫ እንደመሆኗ ጠቃሚና ከተማዋን የሚመጥን ነው ያሉት የኢኮኖሚ ምሁሩ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ ፕሮጀክቱ የከተማዋን ገጽታ በከፍተኛ ሁኔታ የሚለውጥ ነው ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የተለጠጠ ነው የሚል እምነት የለኝም የሚሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ እንዲህ ያለው ፕሮጀክት ሁሉም ሰው የሚፈልገው በመሆኑ የመሳካት እድሉ ከፍተኛ ነው ባይ ናቸው፡፡
ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገው 29 ቢሊዮን ብር ቢሆንም በሚገባ የማስተዋወቅና የማስገንዘብ ስራ ከተሠራ ከሀገር ውስጥም ከውጪም ከተያዘው እቅድ በላይ ገንዘብ ሊገኝ የለገፁት የኢኮኖሚው ምሁር፤ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ሃገራት አምባሳደሮችም መዲናዋ ውብ እንድትሆን ይፈልጋሉ፤ ለዚህም ድጋፍ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡
በከተማዋ የአስፋልት መንገድ ለመዘርጋት ብቻ በየአመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር እንደሚወጣ የገለፁት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ አዲስ አበባን አረንጓዴ ለማድረግ ቢሊዮን ብሮችን ማፍሰስ ለመጪው ትውልድ ሃውልት የማቆም ያህል ነው ብለዋል፡፡
እንዲህ ያሉ ፕሮጀክቶች በታይላንድ፣ በሲንጋፖር፣ በቻይና፣ በአሜሪካና ሌሎች ከተሞች ተከናውኑው ውጤታማ እንደሆኑ የጠቀሱት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፣ ከዚህ የበለጠ የተባረከና የተቀደሰ ሃሳብ ለአዲስ አበባ ይኖራል ብዬ አልገምትም ይላሉ፡፡
በፕሮጀክቱ አስፈላጊነት ላይ ሙሉ በሙሉ የሚስማሙት የባንክ ባለሙያውና የኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሙሼ ሰሙ ከመንግስት የቀድሞ ተሞክሮ ተነስተው ጥርጣሬያቸውን ይገልፃሉ፡፡ በበኩላቸው፤የእኔ ጥርጣሬ ፕሮጀክቱን ለማስፈፀም የሚያስችል በቂ ዝግጅት ተደርጓል ወይ በሚለው ላይ ነው ይላሉ - አቶ ሙሼ፡፡
ከዚህ ቀደም ለ3 አመታት የባቡር መስመር ለመዘርጋት በከተማዋ በርካታ ማህበራዊ መጐሳቆሎች ማጋጠማቸውን ያስታወሱት አቶ ሙሼ፤ ይህ ፕሮጀክትም 56 ኪ.ሜ የሚሸፍን እንደመሆኑና በወንዙ ዳርቻም ነዋሪዎች ከመኖራቸው አንፃር፣ ዜጐችን ላልተገባ መፈናቀልና መጐሳቆል እንዳይዳርግ ስጋት አለኝ ባይ ናቸው:: ለዚህም ፕሮጀክቱ መተግበር ከመጀመሩ በፊት መንግስት ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ይመክራሉ::
ፕሮጀክቱን በወቅቱ መርቶ ማስፈፀም የሚችል የሰው ሃይል፣ እውቀትና ገንዘብ መኖሩን እጠራጠራለሁ የሚሉት አቶ ሙሼ፤ ፕሮጀክቱ የተለጠጠ መሆኑን አሁን ማወቅ ባይቻልም ሠፊ መሆኑ ግን አያከራክርም፤ ከዚህ አንፃር 29 ቢሊዮን ብር ይበቃዋል የሚል ግምት የለኝም ብለዋል፡፡
ለዚህ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 500 ሚሊዮን ብር፣ ሼህ መሐመድ አሊ አላሙዲ 75 ሚሊዮን ብር፣ ባለሀብቱ አቶ ወርቁ አይተነው 25 ሚሊዮን ብር የሰጡ ሲሆን ከውጪ ደግሞ የአፍሪካ ልማት ባንክ 6 ሚሊዮን ዶላር (180 ሚ. ብር ገደማ)፣ የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት 100 ሚሊዮን ዶላር (3 ቢሊዮን ብር ገደማ) እንዲሁም የጣሊያን መንግስት 5 ሚሊዮን ዶላር (150 ሚ. ብር ገደማ) መስጠታቸው ታውቋል፡፡

Read 9969 times