Print this page
Saturday, 18 May 2019 00:00

“ህብር ኢትዮጵያ” ፓርቲ፤ ለእርቀ ሠላምና መግባባት እሠራለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ፓርቲው በመስራች ጉባኤው አመራሮቹን መርጧል

                 መስራች ጉባኤውን ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ያከናወነው የአምስት ፓርቲዎች ውህደት የሆነው አዲሱ “ህብር ኢትዮጵያ” ፓርቲ በቅድሚያ በሀገሪቱ እርቅና ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር እሰራለሁ  አለ፡፡
ከአገር ውስጥ የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት ፓርቲ፣እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ም/ቤት፣ ቱሣ የኢትዮጵያ ህልውና ዲሞክራሲያዊ ድርጅት፣ ደቡብ አረንጓዴ ኮከቦች ቅንጅትና “ኢትዮጵያችን” የተሰኙ ከውጭ የመጡ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው “ህብር ኢትዮጵያ” የተሰኘውን ሁለተኛውን  ውህድ ፓርቲ ሰሞኑን  የመሠረቱት፡፡
የፓርቲው መስራች ጉባኤ ከትናንት በስቲያ (ሚያዚያ 8) በአዲስ አበባ በተካሄደበት ወቅት የፓርቲው ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ የጸደቀ ሲሆን  የፓርቲው አመራሮችም ተመርጠዋል፡፡ በዚሁ መሰረትም፤  የፓርቲው ሊቀመንበር በመሆን አቶ ግርማ በቀለ፣ ም/ሊቀመንበር አቶ አበራ በቀለ እንዲሁም ዋና ፀሐፊ አቶ መላኩ መሠለ ሆነው ሲመረጡ፣ ኢ/ር ዘለቀ ረዲ ደግሞ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ፓርቲው በምስረታው ማግስት ቅድሚያ ሰጥቶ በሚሠራቸው ተግባራት ላይ ለአዲስ አድማስ ማብራሪያ የሰጡት ዋና ፀሐፊው አቶ መላኩ መሰለ፤ የፓርቲው የመጀመሪያ ተግባር በመላ ሀገሪቱ የራሱን አደረጃጀት መዘርጋትና በየክልሎች ተንቀሳቅሶ ሰፋፊ ህዝባዊ መድረኮችን ማዘጋጀት ነው ብለዋል፡፡ ከዚሁ ጐን ለጐን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በሀገሪቱ ብሔራዊ እርቅና መግባባት እንዲሁም መረጋጋት እንዲፈጠር በትጋት እንደሚንቀሳቀስ ዋና ጸሃፊው  አስታውቀዋል፡፡
ፓርቲው በቀጣይም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ውህደት፣ ጥምረት፣ ትብብር ወይም ቅንጅት ለመፍጠርም በትኩረት እንደሚሠራ አቶ መላኩ ጠቁመዋል፡፡

Read 8301 times