Saturday, 18 May 2019 00:00

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የመጀመሪያ የሥራ አፈፃፀም ሪፖርታቸውን አቀረቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  - “ምርጫ ቦርድ ተዓማኒ አልነበረም” መባሉን አንዳንድ አባላት ተቃወሙ
       - ቦርዱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ሌሎች የማሟያ ምርጫዎችን ለማከናወን ዝግጁ ነው ተብሏል


                ከሰባት ወር በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ የመጀመሪያ የሥራ አፈፃፀም ሪፖርታቸውን ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያቀረቡ ሲሆን፣ ከም/ቤቱ አባላት ክርክርና አወዛጋቢ ጥያቄዎች አስተናግደዋል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን፤ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በህዝቡ ዘንድ ተአማኒ ለማድረግ ያስችላሉ ያሏቸውን የማሻሻያ ተግባራት ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ለም/ቤቱ ባቀረቡት የ9 ወር የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርታቸው ጠቁመዋል፡፡
ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ የሚያደርጉ ስራዎችን እየሠራን ነው ያሉት ሰብሳቢዋ፤ በምርጫ ጉዳይ ላይ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ስልጠና መሰጠቱን፣ ቀጣዩን ምርጫ የሚያዘምኑ ማንዋሎች መዘጋጀታቸውን እንዲሁም የምርጫ ህጉን ጨምሮ የተለያዩ የምርጫ ህግ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን  አስረድተዋል፡፡
የሰብሳቢዋን ሪፖርት ተከትሎም ከቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፤ “ከዚህ ቀደም የነበረው ምርጫ ቦርድ ተአማኒ አልነበረም” የሚለው የወ/ት ብርቱካን አገላለጽ ከአንዳንድ አባላት ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
“እኛ እዚህ ተመርጠን ያለነው ተአማኒ በነበረ ምርጫ ቦርድ ነው” ሲሉ አንድ የቋሚ ኮሚቴው አባል የተቃወሙ ሲሆን ሌላኛው በበኩላቸው፤ “የቀድሞ ምርጫ ቦርድ ተአማኒ አልነበረም ለማለት የህብረተሰቡ ግልጽ አቋም መታወቅ አለበት፣ ጥናትም መደረግ አለበት አሊያ ግን ተአማኒ አልነበረም ማለቱ አሁን በፓርላማ ያሉት በህጋዊ መንገድ አልተመረጡም እንደማለት ነው” ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
እየተገባደደ ባለው የ2011 ዓ.ም ይካሄዳል የተባለው የአዲስ አበባ ከተማና የአካባቢ ምርጫ  ምን ላይ ደረሰ? ቀጣዩ ብሔራዊ ምርጫ በጊዜው ይከናወናል ወይ? በህጋዊነት ያልተመዘገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲመዘገቡ ምን ጥረት እየተደረገ ነው? የሲዳማ ህዝብ የክልል እንሁን የሪፈረንደም ጥያቄ ምን ላይ ደረሰ? የሚሉት በዋናነት ከአባላቱ የተነሱ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለጥያቄዎቹ በሰጡት ማብራሪያና ምላሻቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ሌሎች የማሟያ ምርጫዎችን ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት ቦርዱ በበቂ ሁኔታ ማድረጉን ገልፀው፤ ለዚሁ ተግባር 45ሺህ 822 የምርጫ ጣቢያዎችን ማደራጀቱንና ከ230 ሺህ በላይ የምርጫ አስፈፃሚዎችን ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ምርጫውን ለማከናወን የሚጠበቀው የመንግስት ውሣኔ መሆኑን  አክለው ገልፀዋል - ሰብሳቢዋ፡፡
በ2012 ለሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫም ቦርዱ የራሱን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን በመግለጽ የምርጫ ህግን ማሻሻልና በምርጫ ጉዳይ ስልጠና መስጠት እንዲሁም ዘመናዊ የምርጫ ማኑዋሎችን ማዘጋጀት ለምርጫው የሚደረግ ዝግጅት አካል ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የፓርቲዎች ምዝገባን በተመለከተም ቦርዱ ከፓርቲዎች አስፈላጊውን ሰነድ አሰባስቦና አደራጅቶ አዲስ ለሚቋቋመው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት ውሣኔ ለማቅረብ ዝግጅት ማጠናቀቁን ወ/ት ብርቱካን ጠቁመዋል፡፡  የሲዳማ ህዝብ የሪፈረንደም ጉዳይም የአዲሱን ቦርድ መቋቋም የሚጠብቅ ጉዳይ መሆኑን ሰብሳቢዋ ለም/ቤቱ አባላት አስገንዝበዋል፡፡ ሌላው ወ/ት ብርቱካን ለም/ቤቱ ያቀረቡት ጉዳይ ለፖለቲካ ድርጅቶች ከመንግስት የሚሰጠው የ10 ሚሊዮን ብር የድጐማ ገንዘብ ክፍፍልን የተመለከተ ነው፡፡  ይህ ገንዘብ እስከዛሬ ሲከፋፈል የቆየው ፓርቲዎች በፓርላማ ባላቸው ወንበር መጠን የሚል መመዘኛን መሠረት አድርጐ እንደነበር ያስታወሱት ሰብሳቢዋ፤ አሁን ፓርላማው ሙሉ ለሙሉ በአንድ የፖለቲካ ድርጅትና አጋሮቹ በተያዙበት ሁኔታ ይሄን የክፍፍል ቀመር ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም ብለዋል፡፡ ለዚህም አዲስ የክፍፍል ቀመር መዘጋጀቱንና ለዚሁ አላማ ከመንግስት የተሠጠው 10 ሚሊዮን ብር የዚህን የድጐማ ክፍፍል ስልት ተግባራዊ መደረግ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአጠቃላይ ባለፉት ወራት ምርጫ ቦርድን ለማዘመን፣ በህዝብና በፖለቲካ ድርጅቶች ዘንድ ተአማኒ ለማድረግ አስፈላጊ ያሏቸውን ተግባራት እያከናወኑ መቆየታቸውን የገለፁት ወ/ት ብርቱካን፤ ነገር ግን በርካታ ጉዳዮች አዲስ የሚቋቋመውን የቦርድ አባላትና የረቂቅ ህጐችን መጽደቅ እየተጠባበቁ መሆኑን ለም/ቤቱ አስረድተዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ፤ ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ በተያዘለት ጊዜ እንዲከናወን የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች እንዲደረጉ በማሳሰብ፣ አዲስ የቦርድ አባላት እስካልተተኩ ድረስ ነባሩ ቦርድ ተግባሩን ማከናወን አለበት የሚል አስተያየት ሰጥቷል፡፡     

Read 7240 times