Saturday, 18 May 2019 00:00

ለተፈናቃዮች ማቋቋሚያ ከ34 ሚሊዮን ብር በላይ ተለገሰ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 “ከተባበርንና ልብ ከገዛን መከራችንን ማሳጠር እንችላለን”  አርቲስት ታማኝ በየነ
                                       

               “ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት”፤ ከጉጂና ከጌዲኦ ለተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል 31.4 ሚሊዮን ብር የለገሰ ሲሆን በአማራና ቅማንት ግጭት ለተፈናቀሉ  ወገኖች 3 ሚሊዮን ብር ለግሷል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ረፋድ ላይ ቦሌ በሚገኘው ስካይ ላይት ሆቴል በተካሄደ ሥነ-ሥርዓት ላይ የጌዲኦና ጉጂ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የሚሰራውን አጠቃላይ ስራ “ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ” ሊያከናውን ከ“አለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት” ጋር የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረመ ሲሆን ለዚሁ ዓላማ የሚውለውን 31.4 ሚ. ብር፣ በወርልድ ቪዥን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር፣ ሚስተር ኤድዋርድ ብራውን፤ ከትብብሩ መስራችና ዋና ዳይሬክተር፣ አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ተረክበዋል፡፡
በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች በ“ጐፈንድሚ” አካውንትና አለምአቀፍ ትብብሩ ካስቀመጠው ተውጣጥቶ 3 ሚ. ብር፣ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መሰብሰቡ የተገለጸ ሲሆን ይህንንም ገንዘብ በአማራ ክልል፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ፣ ሰብሳቢ ዶ/ር ጌትነት አለሙ ከተረከቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ “የአማራን ተፈናቃይ ለየት የሚያደርገው፣ ላለፉት 28 ዓመታት ሲፈናቀል መኖሩና ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሄዱ ነው” ብለዋል፡፡ “አለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት” አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ገንዘቡን አሰባስቦ ለወገኑ በመድረሱ ትብብሩን፣ በትብብሩ ውስጥ ያሉ የቦርድ አባላትንና የለገሱ ወገኖችን ዶ/ር ጌትነት አመስግነዋል፡፡
የትብብሩ መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ አቶ በትሩ ገ/እግዚአብሔር በበኩላቸው፤ የተሰበሰበው ገንዘብ እንደ እስካሁኑ ለምግብና ለቁሳቁስ የሚውል ሳይሆን ከጉጂና ጌዲኦ ተፈናቃዮች የተወሰኑትንና ችግሩ የፀናባቸውን 1710 ቤተሰቦች፣ መኖርያ ቤቶች ሰርቶ ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመመለስ  ጠቁመው፤ በተጠናው ጥናት በአማካይ አንድ ቤተሰብ ስድስት ሰዎች እንደሚይዝና 10 ሺህ 260 ሺህ ሰዎች ከመጠለያ ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንደሚመለሱ ተናግረዋል፡፡ የቤት ተጠቃሚ የሚሆኑት የጉጂም የጌዲኦም ተፈናቃዮች መሆናቸውንም አክለዋል፡፡
እርዳታ በማሰባሰቡ ሂደት 1.3 ሚ ዶላር መሰብሰቡንና በዚህም ልገሳ 18ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን መሳተፋቸውን የጠቆሙት አቶ በትሩ፤ ገንዘቡ ለ18ሺህ ሲካፈል እያንዳንዱ ሰው 74 ዶላር ከስራውና ከኑሮው ላይ ቀንሶ ለወገኑ ለመድረስ ቀናነት አሳይቷል ብለዋል፡፡ ገንዘቡ በሶስት ዘርፎች አገልግሎት ላይ የሚውል ሲሆን ግድግዳው ጭቃ የሆነ ቆርቆሮ ቤት ለተፈናቃዮች ይሰራል፤ ተፈናቃዮቹ አርሶ አደር ከነበሩ ለማረስ የሚያስፈልጋቸው ዘርና የማረሻ መሳሪያ፣ አርብቶ አደር ከሆኑም ከብቶችና መሰል ወጪዎች ለመሸፈን እንደሚውል ጠቁመው፤በሌላ በኩል ግጭቱና መፈናቀሉ ተመልሶ እንዳይመጣ በሁለቱ አጐራባች አካባቢዎች እንደ ሞዴል የሚያገለግል የሰላም ግንባታ ሥራ እንደሚሰራና በአጐራባቹ የሚገኙ የሁለቱ አካባቢ ሰዎች ባህል እንዲለዋወጡ፣ ገበያ እንዲገበያዩና ጥሩ መንፈስ እንዲፈጥሩ ለማድረግም ይውላል ብለዋል፤የቦርድ ሰብሳቢው፡፡  
ወርልድ ቪዥን አጠቃላይ ሥራውን እንዲያከናውን ለምን ተመረጠ በሚል ከጋዜጠ ለቀረበ ጥያቄ፣ የትብብሩ መስራችና ዳይሬክተር አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ሲመልስ፤ “ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ውስጥ ከ40 ዓመት በላይ የመስራት ልምድ ያዳበረ፣ ከዚህም በፊት በተመሳሳይ ጉዳይ ከትብብሩ ጋር በሰራው ውጤታማና ታማኝ ሥራ ከመመረጡም በላይ የቤቶቹን ግንባታ፣ መልሶ ማስፈሩንና አጠቃላይ ለስራው ማስኬጃ ያስፈልግ የነበረውን 200ሺህ ዶላር (ከ5.7 ሚ. ብር በላይ) ራሱ ሸፍኖ፣ በትብብሩ የተገኘው ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እንዲውል ድጋፍ በማድረጉ ነው፡፡” ብሏል፡፡
ወርልድ ቪዥን በቅርቡ ወደ ተግባር በመግባት ክረምት ሳይጠባ ቤቶችን ለተፈናቃዮች ገንብቶ ለማጠናቀቅና መልሶ ማስፈሩን ለማካሄድ የተፈራረመ ሲሆን የየሶስት ወሩን የስራ አፈፃፀም አገር ውስጥ ለሚገኘው የትብብሩ ድጋፍ ሰጪ አባላት ሪፖርት እንደሚያቀርብና ድጋፍ ሰጪዎቹም የወርልድ ቪዥንን ሥራ በቅርበት እንደሚከታተሉ ተገልጿል፡፡
አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ፣ ለተፈናቃዮች የተሰበሰበውን ገንዘብ በተመለከተ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተጀመረውን ዘመቻ በተመለከተ መረር ያለ ምላሽ ሰጥቷል፤ “ረሃብና መከራ ደጋግሞ ጐብኝቶናል፤ አሁንም እየደረሰ ያለው ሰቆቃና ችግር የዓለም ማህበረሰብ ጠቅላላ የአንድ አመት በጀቱን ሰብስቦ ቢሰጠን የሚቀረፍ አይደለም፤ሆኖም የአቅማችንን ለማድረግ ለአንዲት ህፃን እንኳን ተስፋ ለመሆን በምናደርገው እንቅስቃሴ እርዳታውን በብሔርና በዘር ልንመነዝረው እየሞከርን፣ ወደ እንስሳነት እየወረድን ነው፡፡ እኔ ከመላው ዳያስፖራ እርዳታ ሰብስቤ ለብሔሬ እንደምሰጥ ተደርጐ ዘመቻ ተከፍቷል፤ በእኛ እምነት የትኛውም ዜጋ መፈናቀል የለበትም፤ ዛሬ አጥንቷ ገጥጦ የሚታየው የጌዲኦ እናት የሁላችንም እናት ናት የሚል ሥነ-ልቦና ነው የሚያንቀሳቅሰን፤የእርዳታ ስንዴን በብሔር መመንዘር አይቻልም” በማለት፡፡
በህዝብ ዘንድ ያላችሁን ተቀባይነትና በገንዘብ ማሰባሰቡ ያሳያችሁትን ስኬት ተጠቅማችሁ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ለምን ከአለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ከመንግስትና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር አትሰሩም? በሚል ከአዲስ አድማስ ለቀረበው ጥያቄም፤ “እርግጥ ነው አሁን ከዚህ መግለጫ ስንወጣ ሌላ ቦታ መፈናቀል ተፈጥሮ ሊጠብቀን ይችላል፡፡ አሁን ያለንበት ችግር ከቀጠለ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት ቀርቶ የምንደበቅበት እናጣለን” ያለው አርቲስት ታማኝ፤ “የሚመለከተው ሁሉ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ መረባረብ አለበት፡፡ እኛም ከእርዳታው በተጨማሪ የሰላም ግንባታ የናሙና ሥራ ለመስራት እቅድ ይዘናል፤ አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ሚዲያውም ችግሩን ማሳየት ብቻ ሳይሆን የመፍትሔ አካል የመሆን ሃላፊነትም አለባችሁ” ብሏል፡፡
“አለምአቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት” ያለው ጉልበት፤ እንባና ልመና ነው፤ እኔ ከፊት ለፊት ወጥቼ በቴሌቪዥን ሽፋን ባገኝም፣ ከጀርባ ሆነው ታሪክ የሚሰሩ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው አላማችንን የሚያሳኩት ያለው አርቲስቱና አክቲቪስቱ፤ ለነዚህ ወገኖች ክብርና አድናቆት አለኝ ብሏል፡፡ “ባለፉት 28 ዓመታት አሉታዊ ነገር እየጠጡ መኖር ለጤናም ጥሩ አይደለም፤ የአንድ ወገን ተስፋ መሆን ስለሚያጓጓ እንጂ፡፡ አንዳንዴ በስልክ በኢሜይል ሰው እያለቀ ነው ምን እየሰራችሁ ነው ስንባል፣ መጥፋት ያምረኛል ግን ወዴት?” ሲል ጠይቋል አርቲስት ታማኝ፡፡ አክሎም ሲናገር፤ “ያሉትን ችግሮች በመቋቋም ተስፋ ሳንቆርጥ በተቻለን ለወገን መድረስ አለብን፤ መጪው ጊዜ ተስፋ የሚታይበት ነው፤ ወደዚህ ምድር ስንመጣ እንደ ከብት በልተን ብቻ ለመሞት አይደለም፤ አንድ ታሪክ ሰርተን መሞት አለብን” ብሏል፡፡
በዕለቱ በትብብሩ የተሰራ “አገሬ የት ነው?” የተሰኘ በጌዲኦና በጉጂ የተቀረፀ የ10 ደቂቃ ዘጋቢ ፊልም በመግለጫው ለታደሙት የቀረበ ሲሆን የተፈናቀሉ ወገኖች ያሉበትን ሰቆቃ፣ እናት ለልጇ የምታልሰው አጥታ ስትሰቃይ፣ ሰዎች በረሃብ የሞቱትን ለመቅበር እየተላቀሱ ወደ ቀብር ሲሄዱ፣ ህፃናት በባዶ አንጀታቸው አንጋጠው ሰማይ ሰማይ ሲመለከቱ ---- የሚያሳየው ፊልሙ ታዳሚውን በእንባ አራጭቷል፡፡
“ከተባበርንና ልብ ከገዛን መከራችንን ማሳጠር እንችላለን”
ከጋዜጣዊ መግለጫው መጠናቀቅ በኋላ አርቲስት ታማኝ በየነ  ከአዲስ አድማስ ጋር አጭር ቆይታ ያደረገ ሲሆን ሶስት ጥያቄዎች ቀርቦለት ነበር፡፡ የመጀመሪያው፤ አሁን ባለው የአገሪቱ ሁኔታ መከራችንን እንዴት ማሳጠር እንችላለን? የሚል ሲሆን ታማኝም ሲመልስ፤ “ከተባበርን ልብ ከገዛን መከራችንን ማሳጠር እንችላለን፤ ይህን የማናደርግና አሁን ባለው የጽንፍ ለጽንፍ አተካራ ከቀጠልን፣ እውነቴን ነው እንኳን መነጋገር ልጆቻችንን የምንደብቅበት ቀዳዳ እናጣለን፤ስለዚህ ወደ ቀልባችን ተመልሰን ኢትዮጵያዊነታችን ላይ በመስራትና አንድ በመሆን  የመከራ ጊዜያችንን እናሳጥር” ሲል አሳስቧል፡፡
የሀይማኖት አባቶች፤ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች፣ የቤት ሥራዎቻቸውን ባለመስራታቸው ችግሩ ከመቀረፍ ይልቅ ተባብሷል የሚሉ ወገኖች አሉ:: አንት ታምንበታለህ? በሚል ለተጠየቀውም፤ “ምን ጥርጥር አለው፤ እስካሁን በሚያለያየንና በሚያነታርከን ላይ እንጂ አንድነት ላይ ቢሰሩ ችግራችን የማይፈታበት ምክንያት አይኖርም ነበር:: የ27 ዓመት ታሪካችን በልዩነት፣ በጐጥና በብሔር ፖለቲካ ስንታመስ የኖርንበት ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራንም ሆኑ ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች መቶ በመቶ ባይሆንም በአንድነታችን ላይ ስላልሰሩ ለአሁኑ መከራ ተዳርገናል፡፡ አሁንም የባሰ ሳይመጣ፣ የምንደበቅበት ሳናጣ በአንድነታችን ላይ፣ በእርቅና መግባባት ላይ መስራት አለብን፡፡ ይህን የሚሰራ መንግስት ያቋቋመው ኮሚሽንም ያለ ይመስለኛል” በማለት አብራርቷል፡፡
የመጨረሻው ጥያቄ፤ “አለምአቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት” በቀጣይ ምን አቅዷል? የሚል ነው፡፡ “ትብብሩ ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት አቅም የለውም፤ አቅምና ጉልበቱ ቅን ልብና ልመና ነው፡፡ እስካሁን ወገናችን አላሳፈረንም፤ ጥሪያችንን ተቀብሎ ምላሽ እየሰጠ ነው፡፡ መልሶ ማስፈሩን በምሳሌነት መጀመር፣ ሌላውም ለዘለቄታዊ መፍትሔ እንዲነሳሳ ማድረግ ነው፡፡ አሁን ቤት ተሰርቶ የምናሰፍራቸው 1700 ገደማ ቤተሰቦች ብቻ ናቸው፤ ያለው ተፈናቃይ እጅግ ብዙ ነው፤ በቀጣይ የምንችለውን እናደርጋለን፤ በሰላምና በእርቅም ላይ ልክ እንደ መልሶ ማስፈሩ ሞዴል የሆነ ሥራ ለመስራት አቅደናል፡፡ በተቻለን መጠን ጥረታችንን እንቀጥላለን፡፡ አሁን የመልሶ ማስፈሩን ውጤት እያየ፣ በውጭም በአገርም ያለው ወገን ከተባበረ፣ ችግሩን እንቀንሰዋለን የሚል ተስፋ አለን” በማለት የመለሰው የትብብሩ ዳይሬክተር አክቲቪስትና አርቲስት ታማኝ በየነ፤ለዚህ ተግባር መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉትን በሙሉ አመስግኗል፡፡
የዓለም አቀፍ ትብብሩ አመሰራረት---
“ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት” ከ6 ዓመት በፊት በሳኡዲ አረቢያ የሚገኙ ለስራ የሄዱ ኢትዮጵያዊያን ወገኖች ከአገሪቱ ሲባረሩ፣ ሲደበደቡና ክብራቸው ሲነካ፣ ወገን እንዳላቸው ለማሳየት፤  እነሱን ለመርዳት በሚል ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የሚኖሩ ስራውን ከዋና ሥራቸው እኩል የሙሉ ሰዓት ሥራ አድርገው የሚሰሩ 11 የቦርድ አባላትና በቋሚነት የአባልነት መዋጮ የሚከፍሉ 1ሺህ ያህል አባላት ያሉት ሲሆን ከሳኡዲ አረቢያ የተባረሩ ወገኖችን በመርዳት የጀመረውን የበጐ ስራ ተግባሩን፤ የዛሬ ዓመት ገደማ ከቡራዩና አካባቢው ለተፈናቀሉና የአካልና የስነ ልቦና ጉዳት ለደረሰባቸው እንዲሁም ጧሪዎቻቸውን በሞት ለተነጠቁ ወገኖች፣ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር (13 ሚሊዮን ብር ገደማ) በማሰባሰብ ለግሷል፡፡ መንግስት በፕሬሱ ላይ በወሰደው የአፈና እርምጃ የተደናገጡ 38 ጋዜጠኞች በአንዴ ከኢትዮጵያ ተሰድደው ኬንያ በገቡ ወቅት ለእያንዳንዱ ጋዜጠኛ የ1 ወር የቤት ኪራይ በመክፈል የደገፈው ትብብሩ፤ ቆሼ ላይ በደረሰው የቆሻሻ መደርመስ አደጋም ድጋፍ አድርጓል:: ይኸ አሁን ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ለተፈናቃዮች ደርሶላቸዋል፤ከ34 ሚሊዮን ብር በላይ አሰባስቦ በመለገስ፡፡ በኢትዮጵያውያን የተቋቋመውን ይሄን የበጎ አድራጎት ድርጅት፤ አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ በዳይሬክተርነት ይመራዋል፡፡  
በአገር ውስጥም አርቲስት ደሳለኝ ሀይሉ፣ ጋዜጠኛ ክብሬ ተስፋዬ ፣ዶ/ር ተዋበች ቢሻው፣ አመሃ መኮንን፣ ዳዊት በቀለ፣ ዮናስ ጐርፌና ሌሎችም ደጋፊ ቡድን ያለው ሲሆን አሁን የተሻሻለው የበጐ አድራጐትና ማህበራት ኤጀንሲ የህግ ማዕቀፍ አበረታች በመሆኑ በአገር ውስጥ ተመዝግቦ ለመንቀሳቀስ ዕቅድ እንዳለው የትብብሩ መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ አቶ በትሩ ገ/እግዚአብሔር ገልጸዋል፡፡  

Read 7265 times