Saturday, 18 May 2019 00:00

የፕ/ር አስራት ወልደየስ 20ኛ የሙት አመት ነገ በመኢአድ ቢሮ ይዘከራል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  የእውቁ ፖለቲከኛና ሃኪም ፕ/ር አስራት ወልደስ 20ኛ የሙት አመት፣ ፓርቲዎች፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ነገ ከ8 ሰአት ጀምሮ በመኢአድ ጽ/ቤት  ይዘከራል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በፕ/ር አስራት የመቃብር ስፍራ ማለትም በአዲስ አበባ መንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል በሶስት የፖለቲካ ድርጅቶች የጉንጉን አበባ የማስቀመጥ የመታሰቢያ መርሃ ግብር የተከናወነ ሲሆን በመርሃ ግብሩ ላይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የመላ አማራ ህዝብ ድርጅት (መዐህድ) አመራሮችና አባላት መገኘታቸውም ታውቋል፡፡
በነገው እለትም የዚሁ መርሃ ግብር ቀጣይ የሆነና መላው የአዲስ አበባ ህዝብ የተጋበዘበት የመታሰቢያ መርሃ ግብር የሚካሄድ ሲሆን ፕ/ር አስራትን የሚያወሱ የኪነጥበብ ስራዎች ለታዳሚያን እንደሚቀርቡና የሻማ ማብራት ስነስርአት እንደሚደረግ  የመኢአድ  ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አማረ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡ ፕ/ር አስራት ወልደየስ በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርስበትን ግፍና በደል ለመታገል የመላ አማራ ህዝብ ድርጅትን መመሥረታቸው አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት በእስር ላይ ሳሉ ባደረባቸው ህመም ህይወታቸው ማለፉም ይታወሳል፡፡

Read 999 times