Saturday, 11 May 2019 14:58

የሙሴ ጭንቀቱ

Written by 
Rate this item
(12 votes)

የሙሴ ጭንቀቱ


             ህዝበ እስራኤልን ነፃ እንዲያወጣ እግዜር ሲመርጠው
የፈርኦን ክንድ አይደለም ሙሴን ያስጨነቀው፤
እንቢ ይላል ብሎ ህዝቡን ነው የፈራው፡፡
በጨለማ ሰርቶ በቀን ለሚተኛ
ብርሃን ፅልመት ነው የፍርሃት መገኛ፤
በመጨቆን ህይወት መብቱን ለማያውቀው
ምዕራብ ተቀምጦ ምስራቅ ለሚመስለው
ወደ ምስራቅ መሄድ፣ ወደ ምዕራብ ነው፤
ውሸት እንጂ እውነት፣ እውነቱ ውሸት ነው፡፡
ይህ ነው እውነታቸው፣ ይህ ነው የነሱ እምነት፤
ስለዚህ ከፈርኦን ዛቻ ከፈርኦን ጉልበት
ያለ እምነት ተስፋ፣ ያለ እውነት ድፍረት
ትጥቅን ያስፈታል
ጉልበትን ያዝላል፤
ይህ ነው ምክንያቱ የሙሴ ፍርሃቱ፡፡
ዛሬም በዚች ምድር እስራኤል ተማርኳል
ነፃነትን ረስቶ ባርነትን ለምዷል፤
ከነዓን ሳይደርሱ ብዙዎች ሞተዋል
በጀግንነት ወኔ ፍርሃት ተወልዷል፤
በማጣት ተፋቅሮ፣ በማግኘት ተጋድሏል፡፡
ሙሴም፤
በእምነቱ ተስፋ አጥቶ፣ እውነትን ፈርቷታል
በበትሩ እራሱን አሻግሮ አሮንን ይለካል፡፡
ህዝቡም፤
እሺ ብሎ ባይከተለው
የህይወት ሐቅ አለው
ምክንያቱም፤
ዘመንን ላላየ ለፈርኦን አምላክ ለነበረ ሲምል
ታፍኖ ለቆየ ንፁህ አየር መተንፈስ እጅጉን ይጨንቃል፡፡
(ባንተ ደሳለኝ)

Read 3315 times