Sunday, 12 May 2019 00:00

የህግ ባለሙያ - የሰብአዊ መብት ተሟጋች - የሴቶች ባንክ መሥራች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


                “--የተደራጁ፣ የተነቃቁና አቅም ያጐለበቱ እንዲሁም ተገቢውን ቦታቸውን የሚጠይቁ ሴቶች እንዲፈጠሩና እምቅ አቅማቸውን እያወጡ ለቤተሰቦቻቸው፤ ለማህበረሰባቸውና ለአገራቸው ጥቅም የሚያውሉ ሴቶችን ለማየት አልማለሁ፡፡--”

              የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ያሳስበኝ የጀመረው ገና ስለ ቃሉና ምንነቱ ከማወቄ በፊት ነበር:: እናቴ አስካለች ተገኝ፤ በየትኛውም የህይወት ሁኔታ ሃቀኝነት፣ ሚዛናዊነትና ፍትሃዊነት አስፈላጊ እንደሆኑ ለእኛ ለልጆቿ ታስተምረን ነበር፡፡ በደል ወይም መድልዎ ስመለከት አይደላኝም፤ እናም የልቤን ከመናገር ወደ ኋላ ብዬ አላውቅም:: ጥያቄዎችን መጠየቅ እወድ ነበር፡፡ ከኃላፊዎች ጋር የማልስማማባቸው ጊዜያቶችም ብዙ ነበሩ:: ገና ታዳጊ ወጣት ሳለሁ፣ ሁለት ጊዜ በቁጥጥር ስር ውዬ ነበር - የአመጽ ተግባር ፈጽመሻል በሚል፡፡ አንዴ መፈክር በይ ስባል አሻፈረኝ ብዬ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ካምፕ ውስጥ ሳለን ለወንድ ተማሪዎች ምግብ አላበስልም በማለቴ ነበር፡፡
ወንድሜን ክፍሉ ውስጥ ካሉ አንዳንድ ጉልበተኞች እንድከላከል ተብሎ ከእድሜዬ ቀደም ብዬ ት/ቤት እንድገባ ተደረገ፡፡ ይህ በልጅነት የተጓዝኩባቸው መንገዶች፤ ሕግ ለማጥናት ለመወሰኔ ውስጣዊ ጥንካሬ ሰጠኝ፡፡ የኮሌጅ መመረቂያ ጥናቴንም “የአፍሪካ ቻርተር የሰብአዊና የሕዝብ መብቶች” በሚል ርዕስ ላይ አደረግሁ፡፡
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ መሪዎች ቤተሰብ የወጣችው እናቴ፣ በልጅነት ዘመኔ አርአያ በመሆን ጉልህ ሚና ተጫውታለች፡፡ እንዳብዛኛው የዘመኗ ሰዎች የት/ቤት ደጃፍ አልረገጠችም፡፡ ነገር ግን ትምህርት እንድንማር ታበረታታን ነበር፡፡ የቤት ውስጥ ሥራና ዘጠኝ ልጆች (አምስት ወንዶችና አራት ሴቶች) ከማስተዳደር በተጨማሪ፤ በህይወት ስኬታማ ለመሆን በትምህርት ከመበርታትና ተግቶ ከመሥራት ውጭ አቋራጭ መንገድ እንደሌለ ሁላችንንም አስተምራናለች፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው ተወዳጁ አባቴ፣ የልጅነት እድሜያችንን ባሳለፍንበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የአሶሳ ከተማ ከንቲባ ነበር፡፡ በባህርይው ግዴለሽ ሲሆን ይሄም ለእናታችን ባህርይ ጥሩ ማካካሻ ነበር፡፡ ይሄ ጠባይ ታዲያ ለኛ እንጂ ለእናታችን ጠቅሟታል ማለት ግን አይቻልም፡፡
የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ያጠናቀቅሁት በአሶሳ ከተማ ሲሆን፤ ትምህርት በጣም እወድ ነበር፡፡ ሁሌም ከክፍላችን ምርጥ ተማሪዎች አንዱ ነበርኩ፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ሳለሁ፣ በአንድ ዓመት ሁለት ክፍሎችን ተሻግሬ የማትሪክ ፈተና በማለፍ፣ 17ኛ ዓመቴን በያዝኩበት ወር ላይ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገባሁ:: የእኔ ታሪክ በትምህርት ላይ የተመሠረተ ነውና በልጃገረዶች ትምህርት ላይ ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ አቻ የሌለው ት/ቤት አልተማርኩ ይሆናል፤ ነገር ግን ወላጆቼና ወገኖቼ ሊሰጡኝ የቻሉትን ትምህርት በቅጡ ተጠቅሜበታለሁ:: በህይወት ጉዞዬ ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፌአለሁ፤ ሰው በትክክለኛው መንገድ የሚመራው ካገኘና “አዎ እችላለሁ” የሚል አመለካከት እንዲያዳብር ከተበረታታ፣ “ጣራው ሰማይ ነው” እንዲሉ፣ ምንም የሚያቆመው ነገር አይኖርም፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ት/ቤት ስማር፤ መጀመሪያ ላይ 50 ወንዶች በነበሩበት ክፍል ውስጥ ብቸኛዋ ሴት ተማሪ ነበርኩ:: በኋላ ሦስት ሴቶች ተቀላቀሉን፡፡ ይሄ ለእኔ ፈታኝ ቢሆንም ራሴን ለማሻሻልና ለማሳደግ ምቹ አጋጣሚም ሆኖልኝ ነበር፡፡
የሕግ ድግሪዬን ከያዝኩ በኋላ፤ በከፍተኛው ፍ/ቤት የወንጀል ችሎት ለሦስት ዓመት በዳኝነት ሠርቻለሁ፡፡ ህጉና አፈፃፀሙ በሴቶች ላይ አድሎ እንደሚያደርስ ያጤንኩት ያኔ ነው:: በ1985 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን፤ የሰብአዊ መብት ኮሚቴ፤ አማካሪና ተመራማሪ በመሆን ስቀጠር፣ ለሴቶችና ህፃናት መብቶች ማስጠበቂያ ጠንካራ ደንቦችን በመቅረጽ ለማገዝ ቻልኩ፡፡ በዚሁ ጊዜ ለሥልጠና ወደ ኔዘርላንድ ሀገር ሄግ ከተማ ተላኩኝ፡፡ በሄግ ቆይታዬም፣ ከዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ህጐች ጋር ከመተዋወቄም ባሻገር የሴቶችን መብት በማስከበር ሥራ ላይ ይሳተፉ ከነበሩ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ሴቶች ጋር የመተዋወቅና የመወያየት እድል አገኘሁ፡፡
ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ የኮሚቴው ሊቀ መንበርና ታላቁ የሙያ አባቴ ለነበሩት አቶ ክፍሌ ወዳጆ፣ የሴቶችን መብት ለማስከበር የወጡ ህጐችና ደንቦች ተፈፃሚ እንዲሆኑ የሚያግዝ ማኅበር የማቋቋም ሃሳቤን አነሳሁባቸው:: እሳቸውም ሃሳቤን ደግፈው አበረታቱኝ፤ ከዚያም በሕገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን ውስጥ ከሠራችው አፀደወይን ተክሌና ሌሎች የሕግ ባለሙያ ሴቶች ጋር በመሆን የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርን ለማቋቋም መትጋት ጀመርኩ:: የማህበሩ ውጥን የተጠነሰሰው ቤቴ ውስጥ ስለነበር፣ ድርጅቱን በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ ለመቅረጽ ሦስት ተከታታይ ሌሊቶች ስሰራ፣ እንቅልፍ አልተኛም ብዬ ማስቸገሬን እናቴ ሁሌም ታስታውሰኛለች፡፡
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርን በመራሁባቸው ስምንት ዓመታት እጅግ አስደሳች ጊዜያት አሳልፌአለሁ፡፡ ያ ጊዜ በማህበሩ ውስጥ ለታቀፍነው ሁሉ በተሟሟቀ እንቅስቃሴ፣ በጋለ ፍቅር እንዲሁም በለውጥና በመማር ሂደት የተሞላ ነበር፡፡ የተለያዩ በደሎች ሰለባ ለሆኑ ችግረኛ ሴቶች የመጀመሪያውን የሕግ ምክር አገልግሎት ማዕከላት በአዲስ አበባና በክልሎች አቋቁመናል፡፡ በወረዳና በዞን ደረጃ አገልግሎት የሚሰጡ ስድሳ ያህል የበጐ ፈቃደኛ ኮሚቴዎችንም መስርተናል፡፡ ከዚህ አገልግሎት ከመቶ ሺህ በላይ ሴቶች ተጠቃሚ ከመሆናቸውም በተጨማሪ የህፃናት ጠለፋን ጨምሮ ሌሎች ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከል ረገድ ጉልህ ፋይዳ ያላቸው ጥቂት ለፍ/ቤት የቀረቡ ትላልቅ ጉዳዮችም እንደ ማስተማሪያ የሚጠቀሱ እንዲሆኑ አብቅተናል:: ማህበሩ ምርምር በማካሄድ፤ በመሟገት፣ የህብረተሰብ ንቅናቄ በመፍጠርና ሰፊ የህብረተሰብ ትምህርት በመስጠት፤ የቤተሰብ ሕግ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግና በሴቶች ላይ አድሎ የሚያስከትለው የዜግነት ሕግ እንዲሻሻል ግፊት አድርጓል፡፡
የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ የማበረታቻ እርምጃ ጉዳይንም ያነሳን ሲሆን በ1992 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ከሰላሳ በላይ ሴቶች ለፓርላማ እንዲወዳደሩ ድጋፍ ሰጥተናል:: በምርጫው አንዳቸውም ባያሸንፉም የሴቶች ፖለቲካዊ እኩል ተሳታፊነትና የማበረታቻ እርምጃ የመንግስትን ትኩረት አግኝቷል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የሴቶችን ድምጽ ለማጉላትና የጋራ መድረክን ለመፍጠር እንዲያስችል፣ ማህበሩ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ጥምረት በመፍጠር የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅትን መሠረተ:: ብዙ ፈተናዎችና መሰናክሎች ቢገጥሙትም የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር፤ የሴቶች መብት ጉዳይ በብሔራዊ አጀንዳ ውስጥ ትኩረት እንዲሰጠውም አድርጓል፡፡ ከሁሉም ከባዱ ግን በ1993 ዓ.ም ማህበሩ መታገዱ ነበር፡፡ እጅ ግን አልሰጠንም፤ እናም እየታገልን ያንን አስቸጋሪ ወቅት ተወጣነው፡፡ በዚህም የማህበራችን ነፃነት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አሳየን፡፡
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር የአመራር ጊዜዬን ሳጠናቅቅ፣ የኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ተጠባባቂ ዳሬክተር ሆኜ ተሾምኩ፡፡ በዚህ ኃላፊነቴም ለ1997 ዓ.ም ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ክርክር አስተባብሬአለሁ፡፡ በእርግጥ ይሄ የተለየ ሥራ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ በተባበሩት መንግሥታት የትምሀርት፤ የሳይንስና የባህል ድርጅት በተሰጠኝ የነጻ የትምህርት ዕድል፣ ወደ አሜሪካን ሀገር ሄጄ፣ የማስተርስ ትምህርቴን ለመከታተል በቃሁ፡፡
በቅርቡ በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን፤ የሥርዓተ ፆታና የማህበራዊ ፖሊሲ ልማት ክፍል፤ በሴቶች መብት አማካሪነት ከመሥራቴ ጐን ለጐን፣ ከባልደረቦቼ ጋር በበጐ ፈቃደኝነት ባከናወንኩት ሥራም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሴቶች ባንክ የሆነውን እናት ባንክ ማቋቋም ችያለሁ፡፡ ባንኩ ሰባት ሺህ ባለቤቶች ያሉት ሲሆን ስልሳ አራት በመቶ የሚሆነው የአክሲዮን ድርሻ የተያዘው በሴቶች ነው፡፡ በምሥረታው ሂደት የባንኩ መሥራቾች የሆኑ አስራ ሁለት አደራጆችን ያካተተውን ኮሚቴ በሊቀ መንበርነት የመራሁ ሲሆን፤ በ2000 ዓ.ም ባንኩ በይፋ ሥራ ሲጀምር የቦርድ ሊቀ መንበር ሆኜ ተመረጥኩ፡፡ የእናት ባንክን የምስረታ ሂደት በምመራበት ወቅት፣ አንዳንዴ ፈጽሞ የማይፈቱ የሚመስሉ የውስጥና የውጭ ከባድ ችግሮች ይገጥሙኝ ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ ፈተናዎች በገጠማት ወቅት ሽንፈትን እንደ አማራጭ የማትቀበል እልኸኛና ጽኑ ሴት፣ በእርግጠኝነት ለስኬት ትበቃለች ብዬ አምናለሁ፡፡ በቅርቡ ሁለቱን የባንኩን ቅርንጫፎች መክፈታችንና ሦስተኛውንም ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆናችንን ስመለከት ታላቅ ኩራት ይሰማኛል፡፡ እናም ባንኩን ስኬታማ ለማድረግ በቁርጠኛነት መሥራቴን እቀጥላለሁ:: ባንኩ ለሴቶች የኢኮኖሚ አቅም መጐልበትና ሁሉን አቀፍ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ማግኘት፣ የድርሻውን በማበርከት ብዙ ርቀት ይጓዛል ብዬ አምናለሁ፡፡
በእስካሁኑ ጉዞዬ ብዙ ተመክሮዎችን አግኝቻለሁ:: ተግታችሁ ከሠራችሁ፣ በሃቀኝነት ከተመላለሳችሁ፣ ለሰዎች አስተዋጽኦ እውቅና ከሰጣችሁና ብርታት ከሆናችሁ የምትሰሩትም ሆነ ያሰባችሁት በእጅጉ እንደሚሳካላችሁ ተገንዝቤአለሁ፡፡ በምሰራው ሥራ ለነገ ሳልል ያለኝን አቅም ሁሉ አሟጥጬ እጠቀማለሁ:: እያንዳንዷን ነገር እራሴ ከመሥራት ይልቅ ለሌሎች በመወከል፣ በቡድን መሥራትን እመርጣለሁ፡፡ ሥራዎቼ ሁሉ የተሳኩልኝ በቡድን በመሥራቴም ነው፤ በዚህ በኩል በጣም እድለኛ ነኝ እላለሁ፡፡
የሥራ አጋሮችን መምረጥ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብኝ እንዲሁም የቡድኑንም ሆነ የራሴን ጥንካሬና ድክመት ማወቅ ወሳኝ መሆኑንም ተገንዝቤያለሁ፡፡ በተቻለኝ መጠን የሰው ጉድለት ላይ ሳይሆን ጥንካሬ ላይ ለማተኮር እሞክራለሁ:: ሁሉም አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበትን ሁኔታ ለመፍጠርም እጥራለሁ፡፡  ሥራዬን የተቃና በማድረግ ረገድ የሙያ አማካሪና ደጋፊ ወዳጆቼ ያበረከቱልኝን አስተዋጽኦ መቼም አልዘነጋውም፡፡ ሁሌም እውቅና እሰጣቸዋለሁ:: ስኬትንና እውቅናን የሚያቀዳጀው በተሻለ ሁኔታ እንሰራዋለን ብላችሁ በምታምኑበት የሥራ መስክ ላይ በጽናት መቀጠል ነው፡፡
እኔና ባልደረቦቼ ያደረግነውን አስተዋጽኦ ለማወደስ የተበረከቱልን ሽልማቶች፣ ያልተጠበቀ ደስታና እርካታ አጐናጽፈውናል፡፡ ተዓማኒነትና ተቀባይነት ያለው ድምጽ ካላችሁ፣ ድምፃችሁን ማሰማት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የኃላፊነት ጉዳይ መሆኑን እንድንገነዘብም አድርጐናል፡፡
በእርግጠኝነት መናገር የምችለው፣ ለሴቶች መብት መከበር ያለኝ ቁርጠኝነት መቼም ቢሆን አይለቀኝም፡፡ እኔ መታወስ የምሻው፤ ሴቶች ላይ የሚደርሰው የፆታ ጥቃትና መድልዎ፣ ከእግዚብሔር የተጻፈላቸው እጣ ፈንታ ሳይሆን በማህበረሰቡ የተጫነባቸው እዳ መሆኑንና ይሄንንም መለወጥ እንደሚቻል ለሴቶች ለማሳወቅ እንደጣረች የሕግ ባለሙያ ነው፡፡
ከመቶ ዓመታት በላይ ተጠናክሮ የዘለቀውን በሴቶች ላይ የሚፈፀም አድልዎ የማስወገድ  ሥራ፣ በአስርት ዓመታት ውስጥ እንደማይጠናቀቅ አሳምሬ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ባሉት ለውጦች ላይ ማከልና ከወሬ ያለፈ ተግባር ማከናወን ይገባናል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ነውና የኢትዮጵያ ሴቶች፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አስተዳደር ውስጥ ተገቢውን ቦታ ማግኘት አለባቸው፡፡ የተደራጁ፣ የተነቃቁና አቅም ያጐለበቱ እንዲሁም ተገቢውን ቦታቸውን የሚጠይቁ ሴቶች እንዲፈጠሩና እምቅ አቅማቸውን እያወጡ ለቤተሰቦቻቸው፤ ለማህበረሰባቸውና ለአገራቸው ጥቅም የሚያውሉ ሴቶችን ለማየት አልማለሁ፡፡ በእርግጥ መንግሥትና ማህበረሰቡ ሴቶችን የማስተማር፣ ማህበራዊና ባህላዊ እንቅፋቶችን የማስወገድ፣ ከፍረጃ ጋር የተያያዙ ችግሮችን የመገዳደር እንዲሁም የኢኮኖሚና የፖለቲካ መዋቅራዊ መሰናክሎችን የመቅረፍ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ወንዶች ደግሞ የቤት ውስጥ ኃላፊነትን ለመወጣት እንዲችሉ አቅማቸው መጐልበት አለበት፡፡
ለዛሬዎቹ ልጃገረዶችና ሴቶች፤ ራሳችሁን አስተምሩ እላለሁ፡፡ አዕምሮአችሁን ክፍት አድርጉ:: ጉጉና ጠያቂም ሁኑ፡፡ መብቶቻችሁ ተሟልተው እንዲከበሩላችሁ ለመጠየቅ አትፍሩ:: ዓይናችሁን ሽልማቱ ላይ በማተኮር ተግታችሁ ሥሩ፡፡ ከእኔ ትውልድ የበለጠ ቴክኖሎጂ ለናንተ ግንኙነትንና ትስስርን የመፍጠር እድሎችን እንደሰጣችሁ እወቁ:: እነዚህን እድሎች ተጠቅማችሁ የለውጥ እርምጃውን አፍጥኑት፡፡
ምንጭ፡- (የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት በመስከረም 2007 ዓ.ም “ተምሳሌት” በሚል ርዕስ ካሳተመውና የስኬታማ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ታሪክ ከሚተርከው መጽሐፍ የተወሰደ)



Read 2992 times