Print this page
Monday, 13 May 2019 00:00

የልብ ማዕከሉ ይፈተሽ!

Written by  ይድነቃቸው ከበደ
Rate this item
(1 Vote)


          “አንድ ብር ለአንድ ወገን” በማለት በህዝብ መዋጮ፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ የተገነባው የልብ ህክምና ማዕከል ሥራ ከጀመረ አስር አመት እየሞላው ነው፡፡ ይህ የልብ ማዕከል በለጋሽ አገራት እርዳታ ለበርካታ የልብ ታማሚዎች እርዳታ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬ በፋይናንስ እጥረት ሳቢያ አገልግሎቱን እንዳያቆም ተሰግቷል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ  የልብ ማዕከሉ መዋቅር አልባ በመሆኑና ሥልጣን ወይም ሀላፊነት ምንም የህክምና እውቀት በሌለው ግለሰብ እጅ እንዲገባ በመደረጉ ነው፡፡ በዚህም የተነሣ ለልብ ማዕከሉ በእርዳታ የሚመጡ የህክምና መሳሪያዎችና ውድ መድሀኒቶች ሳይቀር ለብክነትና ለዝርፊያ ተጋልጠዋል፡፡
ከሦስትና አራት ዓመታት በፊት የተለያዩ የውጭ ሀገር የህክምና ቡድኖች፣ ለማዕከሉ የተሟላ መሳርያ ከመለገስም ባሻገር በየጊዜው ለበርካታ የልብ ህሙማን ሕክምና ሲሰጡ ነበር፡፡ አሁን ግን እነዚህ አቅም ያላቸው የህክምና ቡድኖች ከማዕከሉ ርቀዋል::
የሚገርመው ዛሬ የልብ ማዕከሉን የሚያስተዳድሩት ግለሰብ ወይም ኃላፊ፤ በሂሳብ ሰራተኛነት የተቀጠሩት፣ ከማዕከሉ መሥራች ከዶ/ር በላይ አበጋዝ ጋር በነበራቸው ቅርበት ነው፡፡  ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዶ/ሩ ባልታወቀ ምክንያት ከልብ ማዕከሉ ራሳቸውን አግልለዋል፡፡ እሳቸውን ተክተው የተቀመጡት እኒህ  ከሙያው ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው የሂሳብ ሰራተኛ፤ የቦርድ ዋና ሰብሳቢ፣ የማዕከሉ ዋና አስተዳዳርና የሰው ኃይል ሀላፊ እንዲሁም  የፋይናንስ ኃላፊ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ:: ይህን ሁሉ ሃላፊነት ጠቅልለው መያዛቸው የልብ ማዕከሉ ከእሳቸው ውጪ ኃላፊና ለምን ብሎ ጠያቂ እንዳይኖረው ያደረገ  ሲሆን ማዕከሉን ለዝርፊያና ለብክነትም አጋልጦታል፡፡
በልብ ማዕከሉ ውስጥ በሙያው ብዙ የሰሩና እውቀቱና ልምዱ ያላቸው በርካታ ሰራተኞች፣ በእኒሁ ግለሰብ ያለ በቂ ምክንያት ከሥራቸው ተሰናብተዋል:: በጣም የሚያሳዝነው፣ ከለጋሽ አገራት የሚመጡ የህክምና ቡድን አባላት የሚለግሷቸው ውድ የልብ ህክምና መሳሪያዎች፣ ከአንድ ዙር በኋላ ሲመጡ ባለማግኘታቸው፣ ተስፋ በመቁረጥ፣ በጣም እያዘኑ እርዳታቸውን ወደ መቀነሱ አዘንብለዋል:: ስለዚህም ማዕከሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ መስራት በሚችልበት አቅም ልክ እየሰራ አይደለም፡፡ ዛሬ ከ10 ሺህ በላይ የልብ ህመምተኞች ወረፋ እየጠበቁ ናቸው፡፡ የባሰባቸው ህጻናትና ልጆችም ህክምናውን ሳያገኙ ይሞታሉ፡፡
በሌላ በኩል የሚመለከተው የመንግስት አካል፣ የልብ ማዕከሉ ሥራውን በአግባቡ እንዳይሰራ የሚያደርጉ የውስጥ ደንቃራዎችን ፈትሾ ማስወገድ ሲችል፣ ዝምታን መርጧል፡፡ ለምን ይሆን? ግድ የላችሁም! ከገንዘብ ወጪ ጀምሮ ውስጡን ፈትሹ! ለልብ ማዕከሉ ድጋፍ ይሆናሉ ተብለው የተገነቡ ሁለት ህንጻዎችስ በምን ሁኔታ ላይ ናቸው? አይታወቅም! ገቢስ አላቸው? ይፈተሽ! ይህ የልብ ማዕከል የግለሰብ ሳይሆን የህዝብ ሀብትና ንብረት ነው፡፡ መንግሥትና ህግ ባለበት ሀገር፣ ስልጣንንና ኃላፊነትን ከለላ በማድረግ ዝርፊያ መቆም አለበት፡፡          

Read 1500 times