Monday, 13 May 2019 00:00

‹‹የኢትዮጵያና የአፍሪካን መልካም ገፅታና የላቀ ስኬት በዓለም ዙርያ ለመገንባትና ለማስተዋወቅ እንፈልጋለን››

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

 የታላቅ የአፍሪካ ሩጫ መስራችና ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ጋሻው አብዛ

           በሐምሌ ወር  ዋሽንግተን ዲሲ ላይ  የኢትዮጵያ ቀን  ከመከበሩ አንድ ሳምንት  በፊት ታላቅ የአፍሪካ ሩጫ በሚል መጠሪያ በየአመቱ የሚካሄድና ብዙሃኑን የሚያሳትፍ ውድድር ይጀመራል፡፡ በ5ኪ ሜትር ርቀት የሚካሄደው የጎዳና ላይ ሩጫው  ኖቫ ኮኔክሽንስ በሚባል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ተዘጋጅቷል፡፡ ከኢትዮጵያ ኢምባሲ፣ በዋሽንግተን ዲሲ የአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤት እና በዋሽንግተን ዲሲ የከንቲባ ፅህፈት ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ክፍልና ከስቲምፓወር ጋር በመተባበር ነው፡፡
ባለፈው ሰሞን  በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኝው የአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤት  ጋዜጣዊ መግለጫ ነበር፡፡ በዋሽንግተን የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ፍፅም አረጋ፣ በዋሽንግተን የአፍሪካ ህብረት ዋና ተጠሪዶክተር አሪካና ችሆምቦሪኮ፣ የዋሽንግተን ዲሲ የከንቲባ ፅህፈት ቤት ተወካይ፣ የተለያዩ የአፍሪካ ኢምባሲ ተወካዮች፣ ታዋቂ አትሌቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላችው እንግዶች ተገኝተውበታል፡፡ አምባሳደር አቶ ፍፅም አረጋ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ‹‹ዝግጅቱ ኢትዮጵያን ከሌሎች የአፍሪካ እህቶቻችው እና ወንድሞቻችው ማክበር የሚችሉበት፤ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በአፍሪካ ቀንድ የጀመሯቸውን ግንኙነቶች የሚያጠናክር፤ ትውልደ አፍሪካዊያንን የሚያቀራርብ የሚያግዝ ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ ውድድሩ ከአንድ ቀን ሩጫ የዘለቀ ፋይዳ እንዳለው የተናገሩት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ምስረታ ላይ የጎላ ሚና እንደተጫወተች ሁላ በዚህ ዝግጅትም ከሌሎች አፍሪካዊያን ወገኖችችን ጋር ሆነን ‘አብሮነት መሻል ነው’ (Better Together) በሚል መርህ ‘የኢትዮጵያ ቀን በዋሽንግተን ዲሲ’ ለማክበር መታቀዱን ገልፀዋል፡፡ በዋሽንግተን የአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤት ዋና ተጠሪ የሆኑት ዶክተር አሪካና ችሆምቦሪኮ በበኩላችው ባለፉት ስድስት አስርት አመታት አፍሪካዊያን አትሌቶች አህጉሪቱዋን በመልካም መልኩ እንድትጠራ ማገዛቸውን ጠቁመው፣ የሩጫ ውድድርን እንደመድረክ ተጠቅሞ የአፍሪካዊያኖችን ግንኙነት ማጠናከርና የአትሌቶችንን ጥረትና ድካም ትርጉም መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።  ዝግጅቱ የአፍሪካ ህብረት በአጀንዳ 2063 ያስቀመጠውን ዲያስፖራው በአፍሪካ የሚኖረውን ተሳትፎ የማሳደግ ጥረት አካል መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ  የውድድሩ ዋና አዘጋጅ የሆኑት ዶክተር ጋሻው አብዛ ደግሞ ዝግጅቱ ከሩጫው ጎን ለጎን ለሚኖሩበት የአሜሪካ ማህበረሰብና ለትውልድ አገራችው የጎላ አስተዋፅ ለሚያደርጉ የዲያስፖራው ወገኖችን ሽልማት የሚሰጥበት መድረክ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡
ስፖርት አድማስ ታላቅ የአፍሪካ ሩጫን አስመልክቶ  የቦርድ ሰብሳቢውን ዶክተር ጋሻው ዘርጋው አብዛ በቀጥታ ከሚኖርበት ሜሪላንድ አሜሪካ በስልክ በመገናኘት ጋር የሚከተለውን ቃለምልልስ አድርጓል፡፡ ዶክተር ጋሻው  በታውሰን ዩኒቨርስቲ የኪንሶሎጂ ዲፓርትመንት የስፖርት ማኔጅመንትን በረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ በማስተማር ላይ ናቸው፡፡
ታላቅ የአፍሪካ ሩጫን ለማዘጋጀት መነሻችሁ ምንድነው…ዓላማዎቹስ?
መልካም በመጀመርያ አመሰግናለሁ:: ባለፈው ዓመት ሃምሌ ወር ላይ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በሰሜን አሜሪካ በሶስት ከተሞች ተገኝተዋል፡፡ ከኢትዮጵያዊያንም ጋር መወያይታችው የሚታወስ ነው፡፡ በዋሽንግተን ከተማ ኢትዮጵያዊያንን ባነጋገሩበት ወቅትም የከተማዋ ከንቲባ መሪያል ባውሰር (Muriel Bowser) በየዓመቱ ቀኑ ‘የኢትዮጵያዊያን ቀን በዲሲ’ ተብሎ እንዲከበር መወሰናቸው ይታወቃል:: ስለሆነም ታላቅ የአፍሪካ ሩጫ ‘የኢትዮጵያዊያን ቀን በዲሲ’ በየዓመቱ በድምቀት ለማክበር  ታስቦ አዘጋጅተነዋል፡፡
ውድድሩን ያዘጋጀንባቸዋው ዓለማዎች  ኢትዮጵያውያን ከሌሎች አፍሪካውያን ጋር በዓሉን እንዲያከብሩ፤ በአሜሪካ የሚገኙ እና ስኬታማ የሆኑ ወጎኖቻችን ትኩረት እንዲያገኙ፤ የተደበቁ ጀግኖችን በማውጣት እንዲከበሩና ልዩ ሽልማትና እውቅና እንዲሰጣቸው ለመስራት ነው፡፡ በየዓመቱ በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያውያን ቀን ሲከበር ኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያንን ለማገናኘት እንፈልጋለን፡፡ በዋሽንግተን ዲሲ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአሜሪካ ከተሞችና በአጠቃላይ በሰሜን አሜሪካ አህጉር ከፍተኛ ትምህርት የወሰዱ እና ምርምር እየሰሩ የሚገኙ፤ በቴክኖሎጂው መስክ የላቀ ደረጃ ያላቸው ኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያን ብዛት ይገኛሉ፡፡ ብዙዎቹ የአፍሪካን ገፅታ የሚገነባ መልካም ስራ እየሰሩ ናቸው፡፡ ስለሆነም በታላቅ የአፍሪካ ሩጫ ይህን መልካም አስተዋፅኦቸውን ለማጉላትና እውቅና ለመስጠት ነው  የምንፈልገው፡፡
ስለዚህም ዝግጅታችን ከአንድ ቀን ያለፈ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ቀኑን ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን ሌሎች አፍሪካውያንም ተሰባስበውበት በጋራ ስናከብረው ማህበራዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ሃይማኖታዊ፤ ዓለም አቀፋዊ ምልከታዎች ይኖሩታል:: ስለዚህም የኢትዮጵያውን ቀን የምናከብረው ለዓመታት የሚያሻግሩ አጀንዳዎችን በማራመድ ነው፡፡ ለምሳሌ የቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የአፍሪካ መሪዎችን አሰባስበው የአፍሪካ ህብረት እንዲመሰረት ያደረጉትን ጥረት፤ አበበ ቢቂላ የመጀመርያውን የወርቅ ሜዳልያ በማግኘት አፍሪካን በኦሎምፒክ ካርታ ላይ ያሰፈረበትን ፈርቀዳጅ ታሪክ የምናስታውስበት ነው፡፡ ለሩጫ ስፖርት የሚኖረንን ማህበራዊ እይታ እና ዋጋ ለማስፋት ፤ የስፖርቱን ሃብት ከግንዛቤ ውስጥ አስገብተን ለመስራት የሚያስችለን ነው፡፡
ኖቫ ኮኔክሽን ታላቁ የአፍሪካ  ሩጫን ሲያዘጋጅ  ሌሎች ትብብር ያደረጉ እነማናቸው?
የጎዳና ላይ ሩጫው  ኖቫ ኮኔክሽንስ ያዘጋጀው ከኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ በዋሽንግተን ዲሲ የአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤት እና በዋሽንግተን ዲሲ የከንቲባ ፅህፈት ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ክፍልና ከስቲምፓወር ጋር በመተባበር ነው፡፡ ኖቫ ኮኔክሽን ማለት ለትርፍ ያልተቋቋም እና መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው:: መስራቾቹ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እና አፍሪካውያን ናቸው፡፡ በስፖርቱ እና በመዝናኛው ኢንዱስትሪ ከአስር ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ተገናኝተው ኖቫ ኮኔክሽንን ተሰባስበን አቋቁመነዋል፡፡ ስፖርታዊ እና ባህላዊ መድረኮችን በመፍጠር አፍሪካውያንን ለማቀራረብ የምንሰራበት ነው፡፡ ዘንድሮ ውድድሩን ለመጀመርያ ጊዜ ስናዘጋጅ በአሜሪካ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ በዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ልዩ ኮሚሽን፤  ከዋሽንግተን ዲሲ ከንቲባ ፅህፈት ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ክፍል ጋር በመተባበር ነው፡፡
ምን አይነት የጎዳና ላይ ሩጫ ነው የተዘጋጀው? ውድድሩ የሚካሄድበት ቀን በዋሽንግተን  ከሚከበረው ‹‹የኢትዮጵያውያን ቀን በዲሲ›› ጋር ይገጣጠማል? ምዝገባውስ?
ያዘጋጀነው በተደላደለ እና ቀጥተኛ መንገድ ላይ የሚካሄድ፤ ብዙሃንን የሚያሳትፍ እና አዝናኝ የጎዳና ላይ ሩጫ ነው፡፡ ውድድሮቹ በሁለት ምድብ ሲካሄዱ ዋናው በ5ኪ ሜትር ርቀት እድሚያቸው ከ11 ዓመት በላይ የሚሆናቸውን የሚያሳትፍ ሲሆን ሌላው ለህፃናት የተዘጋጀው የ1 ኪሜትር ሩጫ  ነው፡፡ ከሩጫ ውድድሮቹ ባሻገር የተለያዩ ማህበራዊ ሁነቶችም ይካሄዳሉ፡፡የህፃናት ውድድሩ በሁለት የእድሜ መደቦች ከ6 እና ከ8 ዓመት እንዲሁም ከ9 እስከ 12 እድሜ ተከፋፍሎ በአበበ ቢቂላ መታሰቢያነት የተዘጋጀ ነው፡፡ በ1960 በሮም ኦሎምፒክ አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ በመሮጥ የማራቶን የወርቅ ሜዳልያ ማስመዘገቡን አውቀው ጀግንነቱን እንዲያደንቁና ከሩጫ እና ከስፖርት እንቅስቃሴዎች ጋር እንዲተዋወቁ ይደረጋል፡፡
ውድድሩን ለመጀመርያ ጊዜ ያዘጋጀነው በመሆኑ የተሳታፊዎችን ብዛት ከወዲሁ መወሰን አልፈለግንም:: ዋሽንግተን ዲሲ የአሜሪካ ዋና ከተማ መሆኗንና የዓለም ፖለቲካ መናሐርያነቷን ከግምት ውስጥ ካስገባን  በውድድሩ ቀን መንገዶችን ማዘጋት በቀላሉ የሚሳካ አይደለም፡፡ ስለዚህም የተሳታፊዎችን ብዛት፤ የውድድሩን ርቀት እና የመሮጫ ጎዳናውን ዘላቂ አድርገን የምንወስነው  በመጀመርያው ዓመት ውድድሩን አካሂደን ከምናገኘው ልምድ በመነሳት ነው፡፡ በየዓመቱ የምናሳትፈውን ተወዳዳሪዎች ብዛት ለመጨመርና የውድድሩን ርቀት ከ5 ኪሜትር  ወደ 10 ኪሜትር ለማሳደግ ነው እቅዳችን፡፡
የጎዳና ላይ ሩጫውን ለመጀመርያ ጊዜ ስናዘጋጀው ልዩ ትኩረት የሰጠነው ከሌሎች አፍሪካውያን ጋር በድምቀት ለማክበር የምንችልበት ወቅት ነው፡፡ ስለዚም ዋናውን ውድድር የምናደርግበት  ሃምሌ 14 ቀን ጁላይ 21፤ 2019 እኤአ በዋሽንግተን ዲሲ ከሚከበረው የማንዴላ ቀን አንድ ሳምንት በኋላ  እንዲሁም ከኢትዮጵያ ቀን በዲሲ አንድ ሳምንት በፊት ነው፡፡ በሁለቱ በዓላት መካከል ያሉት ቀናት፤ በዋሽንግተን ዲሲ የአፍሪካ ሳምንት በሚል የሚከበርበት ነው፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ምናልባትም ውድድሩን በየዓመቱ ከሚከበረው የኢትዮጵያውያን ቀን በዲሲ ጋር በአንድ ላይ እናዘጋጀዋለን፡፡
ለጎዳና ላይ ሩጫው ምዝገባ የምናካሂደው በአካል አይደለም በኦንላይን ብቻ ነው፡፡  ሚያዚያ 22 ምዝገባውን ጀምረን እየሰራን ሲሆን ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት የሚቀጥል ነው፡፡ ምዝገባውን በውድድሩ ኦፊሴላዊ ድረገፅ www.africanrun.com  በፌስቡክ ገፅ Grand African Run  ከአዘጋጆች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ማከናወን ይቻላል፡፡ Eventbrite፤ RunSignup፤ እና ACTIVE በተባሉ ገፆችም የምዝገባውን ሊንክ በማግኘት ማመልከት ይቻላል፡፡  ለእያንዳንዱ ተመዝጋቢ 15 ዶላር ክፍያ የሚያስፈልግ በቡድን አራት እና ከዚያም በላይ ሆነው ለሚመዘገቡ ቅናሽ ይኖረዋል፡፡ ተሳታፊዎች በውድድራቸው ላይ በልዩ የኮምፒውተር ሰዓት የገቡበትን ሰዓት በሚገጠምላቸው ቺፕ እንዲያውቁ ይደረጋል፡፡ በየውድድሮቹ ከ1 እስከ 3ኛ ደረጃ የሚያገኙ የገንዘብ ሽልማት የሚያገኙ ይሆናል፡፡
የተሳካ ምዝገባውን ያከናወኑ ተሳታፊዎች ውድድሩ ሲቃረብ በሚኖሩት ዋዜማ ቀናት በዋሽንግተን ዲሲ አማካይ ቦታ ቲሸርታቸውን፤ የመወዳደርያ ቁጥራቸውን፤ በተጨማሪም ከስፖንሰሮች የሚለገሱ ሌሎች ቁሳቁሶችን የሚወስዱ  ይሆናል፡፡ ይህን አድራሻም ውድድሩ አንድ ወር ሲቀረው የምናሳውቅ ይሆናል፡፡  
የመሮጫ ጎዳናውን ያርድ ፓርክ በመጠኑ ብትገልፀው?
ዘ ያርድ ፓርክ ማለት በዋሽንግተን ከተማ ረጅም እድሜ ያስቆጠረ አካባቢ ነው፡፡ በዚሁ የከተማ ክፍል ያለው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እየቀነሰ መጥቶ ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ባለሃብቶች ከመንግስት ገዝተው በመረከብ እያለሙት ነው፡፡ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ከፍ እያለ የመጣ የዋሽንግተን አካባቢ ነው፡፡ በዚሁ የከተማው ክፍል በዋሽንግተን ዲሲ ትልቁ የቤዝቦል ቡድን ይገኝበታል፡፡ ቲኤፍ ኬ የሚባል እውቅ የእግር ኳስ ስታድዬምም አለ፡፡ልዩ መናፈሻ ፓርክ ያለው ሲሆን ለሩጫ ውድድርም የተመቸ ነው፡፡
በዋሽንግተን ዲሲ ባዘጋጃችሁት መግለጫ ላይ ከኢትዮጵያ ታዋቂ አትሌቶች መካከል አትሌት ሚሊዮን ወልዴ ከክብር እንግዳዎቹ መካከል ነበር፡፡ በዋናው ውድድር ላይ ታላላቅ አትሌቶች ይሳተፋሉ ወይ?
አዎ በሲድኒ ኦሎምፒክ በ5ሺ ሜትር ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳልያ ያስገኘው አትሌት ሚሊዮን ወልዴ የክብር እንግዳችን ነበር፡፡ ሩጫው መዘጋጀቱን በይፋ ባስታወቅንበት እና ባስተዋወቅንበት መድረክ ሌሎችም እንግዶች ነበሩን፡፡ በዋሽንግተን ከተማ የሚገኙ ስፖርተኞችና ሌሎች ዝነኞችም መግለጫውን ታድመውታል፡፡ በዋናው ውድድር ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የምንጋብዛቸው አትሌቶች ይኖራሉ፡፡ የውድድር ሰሞኑ ሲቃረብ  እነማን እንደሆኑ እናሳውቃለን፡፡ ከታዋቂ አትሌቶች ባሻገር በዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች፤ እና ሌሎች ተቋማት ብዙ ተሳታፊዎችን እንደምናገኝ  እንጠብቃለን፡፡ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ያሉ ትውልደ አፍሪካዊ አትሌቶች፤ ስፖርተኞች ፤ ዝነኛ እና ታዋቂ ሰዎች፤ ሙዚቀኞች፤ ተዋንያን፤ ፖለቲከኞች …ሌሎችም ተሳታፊ ሆነው ልዩ ድምቀት ይፈጥራሉ፡፡
ከውድድሩ ምን ስኬት ትጠብቃላችሁ?
በአንድ እጅ ማጨብጨብ የማይቻል ነው:: ስለዚህ የኢትዮጵያውያን ቀንን በዲሲ ታላቅ የአፍሪካ ሩጫን በማካሄድ ስናከብር ከአፍሪካውያን ጋር ሆነን ነው፡፡ የውድድሩን መርህ ‹‹አብሮነት መሻል ነው›› በሚል ሰይመነዋል፡፡ በዋሽንግተን ዲሲ ከሚከበረው የማንዴላ ቀን አንሰቶ እስከ የኢትዮ_ያውያን ቀን በዲሲ ባለው አንድ ሳምንት ታላቁ የአፍሪካ ሩጫን በደንብ እናስተዋውቃለን፡፡ አፍሪካዊው የነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ስፖርት  ለአፍሪካውያን ያለውን ማህበራዊ ፋይዳ በተለያየ መድረክ ባሰሙት ንግግር ገልፀዋል፡፡ አፍሪካውያን ለማቀራረብ ሁነኛ መሳርያ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ገፅታን በመገንባት፤ ብራንድን በማስተዋወቅ እና የገበያ እድሎችን በመፍጠር ከሰሜን አሜሪካ የምንማረው ብዙ ነው:: አሜሪካ በየትኛውም የዓለም ክፍል በመገናኛ ብዙሓናት በመልካም ሁኔታ እንድትታይ ያለፉትን 60 ዓመታት እና 70 ዓመታት ሰርተዋል፡፡ በየትኛው ዓለም የአሜሪካን ስም የሚነሳው  ከኃያልነት፤ ከታላቅነትና ከብልፅግና ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ታላቁ የአፍሪካ ሩጫም በዚህ አቅጣጫ በመስራት የኢትዮጵያና የአፍሪካን መልካም ገፅታና የላቀ ስኬት በዓለም ዙርያ ለመገንባትና ለማስተዋወቅ ይፈልጋል::

Read 27830 times