Monday, 13 May 2019 00:00

አዴፓ ህገ መንግስቱ እንዲሻሻል፤ ሥርዓቱ ፕሬዚዳንታዊ እንዲሆን ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሃሳቡን ደግፈውታል

          ህገ መንግስት እንዲሻሻልና የሀገሪቱ የፖለቲካ ስርአት ፕሬዚዳንታዊ እንዲሆን የአማራ ክልል ም/ቤት ሃሳብ ያቀረበ ሲሆን፤ ይህን የምክር ቤቱን ሃሳብ በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ደግፈውታል፡፡
የአማራ ክልል ም/ቤት ከሰሞኑ በህግ አውጪው፣ በህግ ተርጓሟና ህግ አስፈፃሚ አካላት መካከል ባለው ግንኙነትና በሀገሪቱ ዲሞክራሲ ግንባታ ላይ በመከረበት ወቅት የሀገሪቱን የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት የህገ መንግስት ማሻሻያ ማድረግና ስርአቱን ከፓርላሜንታዊ ወደ ፕሬዚዳንታዊ መለወጥ አስፈላጊ ነው ተብሏል፡፡
በምሁራን በቀረቡ ጥናቶች ላይ ስለ ህገመንግስት ማሻሻልና ፕሬዚዳንታዊ ስርአት በስፋት ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን ጉባኤተኛውም በተለይ የዜጐችን መብት በእኩል የሚያስጠብቅ ህገመንግስት ለሀገሪቱ ያስፈልጋል ብሏል፡፡ ስርአቱ ፓርላሜንታዊ መሆኑ በህግ አውጪው፣ ህግ ተርጓሚውና አስፈፃሚው መካከል የስራ ድርሻ ልዩነት እንዳይኖር ማድረጉ በጥናቱ የተጠቆመ ሲሆን ዜጐችንም የሚያቀራርብ አይደለም ተብሏል፡፡
በሀገሪቱ መረጋጋትና ሠላም ለመጥፋቱና በህዝብ መካከል መተማመንና መግባባት ለመቀነሱ ፓርላሜንታዊ ስርአቱ ተጠያቂ ነው ተብሏል - በቀረቡት ጥናቶች፡፡
ለሀገሪቱ ፓርላሜንታዊ ወይስ ፕሬዚዳንታዊ ስርአት ይጠቅማል? የሚለው ለህዝብ ውይይት ቀርቦ ህገመንግስቱም ተሻሽሎ ሀገሪቱ ወደ ፕሬዚዳንታዊ ስርአት የምትሸጋገርበት ሁኔታ መመቻቸት እንዳለበት የአማራ ክልል ምክር ቤት ሃሳብ አቅርቧል::
በቅርቡ የተቋቋመውና ህጋዊ እውቅና ያገኘው “ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ” በፖለቲካ ፕሮግራሙ ላይ ስርአተ መንግስቱ ፕሬዚዳንታዊ መሆን እንዳለበት አስቀምጧል፡፡ ፕሬዚዳንታዊ ስርአትን አስፈላጊ ነው ያለበት ምክንያትም፤ ሀገር የሚመራው ሰው በቀጥታ በህዝብ ስለሚመረጥ ሀገርን አግባብቶ መምራት ይቻላል ከሚል መነሻ ነው፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)ም ተመሳሳይ አቋም ያራምዳል፡፡ ስርአተ መንግስቱ ፕሬዚዳንታዊ ሲሆን እያንዳንዱ ሰው የሚመርጠው በመሆኑ አሁን ያለውን የአንድ ፓርቲ ተወካይ ሀገርን የመምራት ስርአት ያስቀራል፣ በዚህም ህዝብ በትክክልም በመረጠው ሰው መመራት የሚያስችል ይሆናል ይላል አብን፡፡ ህዝብ የተሻለ ውክልና የሚኖረው የሀገሪቱ ስርአተ መንግስት ፕሬዚዳንታዊ ሲሆን ነው የሚል ጽኑ አቋምም አለው - ፓርቲው፡፡
ዜግነትን የፖለቲካ መሠረቱ አድርጐ የተመሠረተው የኢትዮጵያውያን ዜጎች ማህበራዊ ፍትህ፣ የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ በተመሳሳይ የሀገሪቱ ስርአተ መንግስት ፕሬዚዳንታዊ መሆን አለበት የሚል አቋም አላቸው፡፡
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ በበኩሉ፤ አሁን ያለው ፓርላሜንታዊ ስርአት መቀጠል አለበት የሚል አቋም ያራምዳል፡፡ የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ፤ ፓርላሜንታዊ ስርአት መከተላችን የመድብለ ፓርቲ ስርአትን ለማበልፀግ በእጅጉ ጠቃሚ ስለሆነ ምርጫችን አድርገነዋል ብለዋል፡፡ ስርአቱን ፕሬዚዳንታዊ ለማድረግ የግድ ህገ መንግስቱን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ የሚያስረዱት የስርአተ መንግስቱ አራማጆች፤ ህገመንግስታዊ ማሻሻያና ፕሬዚዳንታዊ ስርአትን እውን የማድረግ ተግባር ተነጣጥለው የሚታዩ አይደለም ይላሉ፡፡
ኦፌኮን ጨምሮ አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው ሁሉም ፓርቲዎች፤ “ህገመንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፤ በእጅጉ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ማሻሻያው እንዲደረግ የሚሹበትን የየራሳቸውን ምክንያት ይዘረዝራሉ፡፡
ሀገር የሚተዳደርበት ህገመንግስት በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ተቀባይነት ሊያገኝ ይገባል የሚለው “ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ”፤ ከዚህ አንፃር የሀገሪቱ ህገመንግስት የህዝብን ፍላጐት መሠረት አድርጐ መሻሻል አለበት ብሏል፡፡
ህገ መንግስቱ ሲሻሻልም የሀገሪቱን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት በሚያስከብር፣ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚያስጠብቅና ሀገሪቱ ካለችበት ዝቅተኛ የኢኮኖሚ እድገትና አስከፊ ድህነት እንድትላቀቅ በሚያስችል መልኩ መቃኘት አለበት ይላል - “ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ”
መገንጠልንና መለያየትን የሚጋብዙ አንቀፆች ሊሻሻሉ  እንደሚገባ የሚጠቁመው ፓርቲው፤ ቋንቋ፣ ባንዲራ፣ የክልሎች አመሠራረትና የወሰን ጉዳይም በህገ መንግስት ማሻሻያ መታየት አለባቸው ይላል:: ዜጐች በአሁኑ ወቅት በሀገራቸው በሠላም መኖር ባልቻሉበት ሁኔታ መጀመሪያ በስራ ላይ ያለው ህገ መንግስት ሙሉ ለሙሉ መከበር አለበት የሚል አቋም ያለው መኢአድ በበኩሉ፤ ሃገሪቱ ስትረጋጋ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብሏል፡፡
አሁን በሀገሪቱ የሚከሰቱ ችግሮች በሙሉ የጐሣ ፌደራሊዝም እና አንቀጽ 39 መሆኑን የገለፀው መኢአድ፤ ዜጐች ይሄ ያንተ አካባቢ አይደለም እየተባሉ የሚፈናቀሉትና የሰው ልጅ በቀስት መለማመጃ የሆነው በህገ መንግስቱ ምክንያት ነው ብሏል፡፡
ኦፌኮ በበኩሉ፤ የመሬት ጉዳይ በህገመንግስቱ፣ የመንግስት ሆኖ መደንገጉ እንዲሻሻልና የግለሰብ በሚለው እንዲለወጥ እንደሚፈልግ የገለፀ ሲሆን ስልጣኔ ከህገ መንግስቱ ውጪ መያዝ የለበትም ከሚለው አንቀጽ ጐን ለጐንም ስልጣን ላይ ከህገመንግስቱ ውጪ ያለአግባብ ተደላድሎ መቀመጥ የማይቻልበት ድንጋጌም እንዲቀመጥ ይሻል፡፡
ህገመንግስቱ ከመግቢያው ጀምሮ ስለሰብአዊ መብት ከተደነገጉ አንቀፆች ውጪ ሙሉ ለሙሉ መሻሻል አለበት የሚለው አብን በበኩሉ ትልቁ የመታገያ ጉዳዬም የዚሁ ህገመንግስት መሻሻል ጉዳይ ነው ብሏል፡፡

Read 10894 times