Monday, 13 May 2019 00:00

የአሜሪካ መንግስት ጠ/ሚኒስትሩ ቃላቸውን እየፈፀሙ ነው አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡ ጊዜ ለመፈፀም ቃል የገቧቸውን ማሻሻያዎች በተገቢ ሁኔታ እያከናወኑ መሆኑን የገለፀው የአሜሪካ መንግስት፤ ኢትዮጵያን የበለፀገች ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ አገር የማድረግ ጅምሮች ጠንካራ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአንድ ዓመት የስልጣን ጊዜን አስመልክቶ የመንግስታቸውን ማብራሪያ ያቀረቡት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል የገቡትን እየፈፀሙ ነው፤ ሃገሪቱን ወደ ብልፅግና፣ ሰላምና ዲሞክራሲ የሚወስዱ እድሎችን ፈጥረዋል” ብለዋል፡፡
የሃገሪቱ መጪ ጊዜ ብሩህ መሆኑን የገለፁት አምባሳደሩ አሜሪካ የበለፀገች ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሃገር ለመሆን ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ እንደፈጀባት በማስታወስ፣ በኢትዮጵያ የብልፅግና ዲሞክራሲና ሰላም ጉዞ በአጭር ጊዜ ውስጥ መልካም ውጤት ያመጣል ብለዋል፡፡
አሜሪካ ዛሬ ላይ ለመድረስ ያሳለፈችውን ውጣ ውረድ በስፋት ያብራራው የአምባሳደሩ ሪፖርት፤ ኢትዮጵያ የውክልና ዲሞክራሲን በጥሩ ሁኔታ ጀምራለች ብሏል፡፡  በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን የለቀቁት የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝን በመጥቀስ ስልጣንን በገዛ ፍቃድ በመልቀቅ የዲሞክራሲ ባህል እንዲዳብር አስተዋፅኦ አድርገዋል ብለዋል - አምባሳደሩ፡፡
በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ እያበበ መምጣቱን ተከትሎ አለማቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀን በሀገሪቱ መከበሩ ትልቅ ትርጉም እንዳለው የገለፁት አምባሳደሩ፤ የሃገሪቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም በ10 በመቶ መጨመሩ ሃገሪቱ ለተያያዘችው የብልፅግና ጉዞ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የሃገሪቱን የህግና የፖለቲካ ሁኔታ ለማሻሻልም አፋኝ ህጎችን የማሻሻል ማለትም የፀረ ሽብር፣ የሲቪል ማህበራትና የሚዲያ አዋጆችን የማሻሻል ስራ በስኬት እየተከናወነ መሆኑን፣ በሃገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች ያለ ምንም ገደብ በሃገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እየተሳተፉ መሆኑ ጠ/ሚኒስትሩ ቃል የገቡትን እየፈፀሙ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብሏል - የአሜሪካ መንግስት፡፡
በሪፖርቱ የለውጡ ፈተናዎች ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት መካከል በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች፣ የመንግስት ተግባርና መዋቅር በጥራት ነጥሮ አለመውጣት እንዲሁም አንዳንድ ኢትዮጵያውያን በለውጡ ውስጥ ተሳትፎ አለማድረጋቸው ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ተግዳሮቶች በየትኛውም ጀማሪ የዲሞክራሲ ተለማማጅ ሃገራት የሚከሰት መሆኑንም አምባሳደሩ ገልፀዋል፡፡
አሁንም በሀገሪቱ ጉዳይ ወሳኙ የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑን የገለፁት የአሜሪካው አምባሳደር፤ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው መፃኢ እድል ላይ በነፃነት መወያየት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡


Read 9545 times