Saturday, 02 June 2012 09:48

ሁለት ድንቅ የጥበብ ልጆች የደመቁበት ምርጥ ምሽት

Written by  ዳዊት ንጉሡ ረታ
Rate this item
(0 votes)

ማክሰኞ ምሽት እንዲህ ሆነ፡፡ “የዛሬን ቴአትር በክብር እንግድነት ተገኝተው የሚመርቁልን እጅግ በጣም የምንወዳቸው ጥንዶች ናቸው፡፡ የመጀመሪያውን ላስተዋውቃችሁ…” ማክሰኞ ግንቦት 21 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ የቴአትርና ባህል አዳራሽ መድረክ ላይ ተፈራ ወርቁ፤ በአለማየሁ ታደሰ ተደርሶ ስለተዘጋጀው “የብዕር ስም” የተሰኘ ቴአትር እያስተዋወቀን መድረኩን በመምራት ላይ ነው፡፡“የመጀመሪያው እንግዳችን…” ቀጠለ ተፈራ ወርቁ፡፡ “እጅግ የምንወደውና የምናደንቀው ድምፃዊ፣ የግጥምና የዜማ ደራሲ…” ማንን እንደሚያስተዋውቀን ለመስማት ልባችን ቆሟል፡፡ “የዜማ ደራሲ… ቴዲ አፍሮ” ባልተጠበቀው እንግዳ እዚያ መገኘት የቴአትር አዳራሹ በጩኸት ተናወጠ፡፡ “ሁለተኛዋ እንግዳችን ሞዴልዋ…” አስተዋዋቂውን ማንም ሊያስጨርሰው አልቻለም፡፡ ሁሉም የተመካከረ ይመስል ባንድ ድምፅ “ፀባየ ሰናይ” በማለት ሕዝቡ ቀድሞ ተዋወቃት፡ቴዲ አፍሮ እጅግ ውብ ከሆነችው ባለቤቱ ጋር እጅ-ለእጅ ተያይዞ፣ ወደ አዳራሹ ሲገባ በአዳራሽ የተሰበሰበው ህዝብ በሙሉ ከመቀመጫው በመነሳት በጭብጨባና በፉጨት ተቀበለው፡፡

ቴዲም በተለመደው ትህትናው ወገቡ እስኪቀነጠስ አጐንብሶ እጅ በመንሳት፣ አድናቂዎቹን አመሰገነና  ወደተዘጋጀለት መቀመጫ ከባለቤቱ ጋር አመራ፡፡አለማየሁ ታደሰ“ቴአትር ሕይወቴ ካልሆነ ሞት ምርጫዬ ነው” ያለው አርቲስት ማን ነበረ?... አለማየሁን ለመግለፅ ከዚህ የተሻለ አባባል ሊመጣልኝ አልቻለም፡፡ ለትወና የተፈጠረ፣ ድንገት መድረክ ላይ ብቅ ሲል፤ የማይደክመው የማይሰለቸው፤ የሚተውን ብቻ ሳይሆን የሚፅፍና የሚያዘጋጅ፤ በመድረክ ብቻም ሳይሆን በፊልምና በተከታታይ ቲቪና የሬዲዮ ድራማዎች ላይ የማናጣው፣ ከንጉስ እስከ የንጉስ አጫዋች፣ ከጀግና እስከ ፍቅረኛ፣ ከምንጠላው ክፉ ባህሪ እስከምንሳሳለትና የምናለቅስለት ምስኪን ሰው … ኧረ አሌክስ ምን ሆኖ ያልተጫወተው ነገር አለ?ባንድ ወቅት ግርም ይለኝ ነበር፡፡ ከሰኞ በስተቀር የተቀሩትን ቀናት በሙሉ በመድረከ ላይ እጀግ የተለያዩ ባህሪያትን በመላበስ መሪ ተዋናይ በመሆን ይጫወት ነበር፡፡ አንድ ሰው በሳምንት ውስጥ 6 ቀናትን እንዴት የተለያዩ ሰዎችን ይሆናል?... ያ ጊዜ የአሌክስ ወርቃማ ዘመን ነበር እለዋለሁ፡፡ ይሄንኑ ያዩ የጥበቡ ዳኞች የጊዜው የ”ቴአትር ንጉስ” በማለት የወርቅ ሀብል ባንገቱ ላይ አጥልቀውለታል፡፡ይህ ሰው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብቶ የ1ኛ ዓመት ትምህርቱን እስኪከታተልና እስኪያጠናቅቅ ድረስ በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ የቴአትር ዲፓርትመንት እንዳለ አያውቅም ነበር ብላችሁ ታምናላችሁ? ታዲያ ጥበብ አሽከርክራ ወደ ራሷ ጠራችዋ! ያኔ “ቴአትር ሕይወቴ” ብሎ ቃለ መሃላ ፈፀመላት፡፡ ተፈተነላት፡፡ ደረሰላት፡፡ አዘጋጀላት፡፡ በመድረኳም ተውረገረገላት፡፡ውበዚህችየቅርብአመታትታሪክእንኳን“ምስጥረኞቹ”ንና “ደመነፍስ”ን ፅፎና ተውኖ፤ “ባቢሎን በሳሎን” ላይ እጅግ የተዋጣለት ትወናን አሳይቶ የጥበብ ልጅነቱን አስመስክሯል፡፡ አሌክሶ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ከጓደኞቹ ጋር በጋራ ሆኖ የጀመረው ሆሊላንድ የጥበብ አካዳሚ ያሰበበት ቦታ ላይ ሳይደርስለት ቢቀርም አሁንም ግን የሙያውን ተተኪዎች ለማፍራት የግሉን ሰፊ ጥረት ያደርጋል፡፡ የወጣት ክበባትና ማህበራት ጋር በመሄድ ከሰፊ የሥራና የህይወት ልምዱ ለታዳጊ ወጣቶች ያካፍላል፡፡ ያሰለጥናል፤ ይመክራል፡፡ አቅጣጫን ያሳያል፤ ያበረታታል፡፡ ተሳክቶላቸው የጥበብ ሥራቸውን በመድረክ ለማቅረብ ለታደሉት ደግሞ የቴክኒክ ዳይሬክተር እየሆነ ያግዛቸዋል፡፡ (“የምሁራን ፍቅር” ቴአትርን ልብ ይሏል)ያም ሆኖ ይህ የጥበብ ሰው እዩኝ እዩኝ አያበዛም፡፡ ዘወትር አንዳች አዲስ ነገር ለጥበቡና ለጥበቡ አፍቃሪዎች ለማበርከት ደፋ ቀና ይላል እንጂ፡፡ አሌክስ አግብቶና ወልዶም የማህበራዊ ህይወቱን ስኬትም አሳይቶናል፡፡“የብዕር ስም” ቴአትር ዛሬ ዛሬ በቴአትር ቤቶቻችን ለዚያውም ገንዘባችንን ከፍለን እየገባን የምንመለከታቸው እጅ እጅ የሚሉ “ልማታዊ ቴአትሮች” ሊማሩ የሚችሉበት መልካም አጋጣሚ ተፈጠሮላቸዋል፡፡ በአለማየሁታደሰ “የብዕር ስም” ቴአትር፡፡በዚህ ቴአትር ላይ ፈፅሞ ልብ ያላልናቸው በሴቶች ላይ የሚደርሱ ተፅእኖዎች፤ የሞራልና የስነ ምግባር ዝቅጠት፣ ሙስና፣ የወሲብ ቅሌት፣ ብልሹ አሰራር ወዘተ ሁሉ እንመለከታለን፡፡ እነዚህእንግዲህ ልማትን ከሚያደናቅፉ ችግሮቻችን ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን አሌክስ እነዚህን ችግሮቻችንና መፍትሄዎቹን እጅግ በሚያስደንቅ ቴክኒክና የፈጠራ ጥበብ ዘወትር ማክሰኞ ለመድረክ እይታ በበቃው የ”ብዕር ስም” ቴአትር ላይ አንስቶታል፡፡ ጥርስ በማያስከድን ውብ ብዕሩና የትወና ጥበቡ የተመልካችን ስሜት ተቆጣጥሮ ዳግመኛ ወደ ንግስናው ተመልሷል፡፡ማርታ ጌታቸው (የአለማየሁ ታደሰ ባለቤት) እና ታዋቂዋ አርቲስት አዳነች ወልደገብርኤል (የማርታ ጌታቸው እናት የአሌክስ አማት)ቴአትሩይበብቃትውነውበታል፡፡ እናንተዬ እኛ አገር እኮ የሪከርድ አያያዝ ድክመት ስላለብን ነው እንጂ ከአንድ ቤተሰብ ሦስት ሰው በአንድ ቴአትር ላይ ሲገናኝ ይሄ የመጀመሪያው አይመስላችሁም?... ሌሎች ካሉ መረጃው ያላችሁ ብትነግሩን፡፡ የሆነው ሆኖ ማርቲና አዳነች በዝምድና በቻ ሳይሆን በፍፁም ችሎታቸው መድረኩን ሲቆጣጠሩት በአይኔ በብረቱ ተመልክቻለሁ፡፡ሌላው አንድ ሳላነሳው የማላልፈው አድናቆት አለኝ፡፡ ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ ባህሪ ስለሚጫወቱ ተዋናዮች በዚሁ ጋዜጣ ላይ በታተመልኝ ፅሁፍ የአንድ ተዋናይ ስምንም ጠቅሼ ነበረ፡፡ የተዋናይ ፍቃዱ ከበደን፡፡ፍቄ ዛሬ በከፍተኛ ሁኔታ የባህሪ ለውጥ አሳይቶአል፡፡ “ባቢሎን በሳሎን” ላይ ያለው ገፀ-ባህሪ እሁድ ዕለት በዚያው በብሄራዊ ቴአትር በሚቀርበው “እንደኬ” ቴአትር ላይ ካለው ገፀ ባህሪ ጋር ፈፅሞ አይገናኝም፡፡ ሁን ደግሞ በ”ብዕር ስም” ቴአትር ነሲቡ የተባለውን ጫት አፍቃሪ ጋዜጠኛ በመወከል ድንቅ ትወና አሳይቷል፡፡ ብራቮ ፍቄ! ተመልካች የከፈለህን ጭብጨባ አስተውለኸዋል?ወደ ቀደመው ነገር ልመለስ፡፡ “የብዕር ስም” ገላዋን ለርካሽ ዓላማ ማስፈፀሚያ አላውልም ያለቺዋን ጠንካራ ሴት በትረ አዳምን ያስተዋውቀናል፡፡ በስልጣን የማባለግን መጨረሻ “ይሄውላችሁ” ይለናል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ጥርሳችን ከሳቅ ሳይለይ ነው፡፡ ብራቮ አሌክሶ! የሁለቱ የጥበብ ልጆች መንገስአንዳንዴ በስራዬ ፀባይ የተነሳ እየተጋበዝኩ ሌላ ጊዜ ደግሞ ገንዘቤን በመክፈል በተለያዩ የቴአትርና የፊልም ምረቃ በዓላት ላይ የመገኘት እድሎችን አግኝቼአለሁ፡፡ ሆኖም ግን እንደ ግንቦት ሃያ አንዱ ማክሰኞ አይነት እጅግ የደመቀ የምረቃ ስነ ስርዓት ፈፅሞ አልገጠመኝም፡፡ቴዲ አፍሮ ከባለቤቱ ሞዴልና አክትረስ አምለሰት ሙጬ ጋር በቴአትሩ ላይ ለተሳተፉ ባለሙያዎችና ተዋናዮች የምስክር ወረቀትና አበባ ለማበርከት “ፀባየ ሠናይ” በሚለው ዘፈኑ ታጅበው ወደ መድረክ ሲወጡ አዳራሹ እንደገና በጩኸት ተናጋ፡፡ አብዛኛው ተመልካች የሞባይል ካሜራውን በመደቀን ወደ እነ ቴዲ አነጣጠረ፡፡ ለሁሉም ባለሙያዎችና ለተዋናዮቹ አበባና ሰርተፍኬት ከተበረከተ በኋላ፣ የመጨረሻው ተራ የአለማየሁ ታደሰ ሆነ፡፡ ተፈራ ወርቁ የአሌክስን ስም ጠራ፡፡ አሌክስ ወደ እነ ቴዲ አፍሮ ቀረበ፡፡ ቴዲና አሌክስ ተናንቀው ተቃቀፉ፡፡ ያኔ ምድር ቀውጢ ሆነች ማለቱ ይቀላል፡፡ ሁለቱ የጥበብ ልጆች በጋራ ነገሱ፡፡ቴዲ ንግግር እንዲያደርግ ተጋበዘ፡፡ “አለማየሁ ታደሰ ታላቅ ብቃት ያለው አርቲስት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በዚሁ ቴአትር ቤት “እስረኛው ንጉስ” የሚለው ቴአትር ላይ ሲተውን ተመልክቼዋለሁ፡፡ ዛሬ ደግሞ ይሄንን ለማየትድያለሁ፡፡ አሌክስ የፃፈው በጣም አሪፍ ቴአትር ነው ተደስቻለሁ…” ብሏል፡፡ይህ የጥበብ ልጆች ፍቅር መከባበርና መደናነቅ ታላቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ ቴዲተዋናዮቹንም ባለሙያዎቹንም ተመልካቹንም አክብሮ ድንገት በተገኘበትና ከአሌክስ ጋር በጋራ በነገሱበት ምሽት አንድም ታዋቂ ተዋናይ/ይት፣ የፊልም አክትር/አክትረስ በአዳራሹ አለማየቴ ግን በሙያው ላይ ያሉ ሰዎችን አብሮነት ጥያቄ ውስጥ እንድከተው አድርጐኛል፡፡ የሆነው ሆኖ አሌክስና ቴዲ አንድ መንገድ አሳይተዋል፡፡ ይሄ ነዋ የሚፈልገው፡፡ መልካም ቅዳሜ!!

 

 

 

 

 

 

Read 27209 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 11:06