Print this page
Monday, 13 May 2019 00:00

በየመን ከ3ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በስቃይ ላይ ታስረው ይገኛሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ሳውዲ አረቢያ የታላቁን የረመዳን ፆምን ምክንያት በማድረግ 1400 ኢትዮጵያውያንን ከእስር ስትለቅ፣ በየመን ከ3ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በአንድ ስታዲየም ውስጥ ታስረው በስቃይ ላይ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡
በእርስ በእርስ ጦርነት እየታመሰች በምትገኘው የመን፤ ኢትዮጵያውያን፣ ሶማሊያውንና ጅቡቲያውያን ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰትና እንግልት እየተፈፀመባቸው መሆኑን  አለማቀፉ የስደተኞች ተቋም (IOM) ከትላንት በስቲያ አስታውቋል፡፡
በኤደን የስታዲየም እስር ቤት ከሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ታግተው የከፋ ሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመባቸው እንደሚገኝ የጠቆመው ተቋሙ፤ አብላጫውን ቁጥር የያዙት ሴቶች እንደሆኑና 800 ያህል ህፃናትም እንደሚገኙበት አስታውቋል፡፡ አብዛኞቹ ወንድ ስደተኞች ታዳጊዎች ናቸው ብሏል - ተቋሙ፡፡
ኢትዮጵያውያኑ ከየመን ዋና ከተማ ሠነአ የገጠር አካባቢዎች፣ ላዥ፣ ኤደን እና ኦቢያን ከተሞች ተሰብስበው የታሠሩ መሆናቸውም ተገልጿል:: የተወሰኑ ኢትዮጵያውያን ከስታዲየሙ እስር ቤት በተጨማሪ ወደ ጦር ካምፕ እስር ቤቶች መወሰዳቸውንም ተቋሙ ገልጿል፡፡
በየመን በእስር፣ በእንግልትና ስቃይ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በዋናነት የመንን እንደ መሸጋገሪያ ተጠቅመው፣ ወደ ሳኡዲ አረቢያ ለመግባት የሞከሩ መሆናቸውም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ አለማቀፉ የስደተኞች ተቋም፤ የኢትዮጵያውያኑን ደህንነት ለመከታተል ጥረት እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል:: በሌላ በኩል፤ የሳኡዲ አረቢያ መንግስት፤ ታላቁን የረመዳን ፆምን ምክንያት በማድረግ፣ በህገ ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጦ ወደ ሳኡዲ መግባትን ጨምሮ፣ በተለያዩ ወንጀሎች ጠርጥሮ ካሰራቸው ከነበሩ ኢትዮጵያውያን መካከል 1400 ያህሉን መልቀቁ ታውቋል፡፡

Read 8567 times