Print this page
Monday, 13 May 2019 00:00

“የሸገር ገበታ” ግንቦት 11 ይካሄዳል

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግማሽ ቢሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል
              
            የአዲስ አበባ ወንዝ ዳርቻዎችን ለማልማት ለተነደፈው ፕሮጀክት ገቢ ማሰባሰቢያ የታሰበው “ሸገር ገበታ” የእራት መርሃ ግብር ግንቦት 11 ቀን 2011 የሚካሄድ ሲሆን፤ እስካሁን ከ2 መቶ በላይ ግለሰቦችና ተቋማት ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ ግማሽ ቢሊዮን ብር ለፕሮጀክቱ ለግሷል፡፡
ለዚህ ፕሮጀክት የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ድርጅት እና በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት 100 ሚሊዮን ዶላር፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ 6 መቶ ሺህ ዶላር እንዲሁም የጣሊያን መንግስት 5 ሚሊዮን ዩሮ ከወዲሁ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸው ተገልጿል፡፡
ከሀገር ውስጥ ተቋማትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀዳሚ ተነሳሽነቱን በመውሰድ 5 መቶ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለፕሮጀክቱ መመደቡን አስታውቋል፡፡
በተለይ ለአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ልዩ ትኩረት በመስጠት ላለፉት ዓመታት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት ሲሰራ መቆየቱን በላከው መግለጫ ላይ ያመለከተ ሲሆን በእንጦጦ፣ ገፈርሳና ሰበታ አካባቢዎች በየዓመቱ በርካታ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ለአረንጓዴ ልማት ስኬት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሆነ እና ለወደፊቱም በተጠናከረ ሁኔታ የሚቀጥል መሆኑን ገልጿል፡፡
“ሸገርን ማስዋብ” ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የአገሪቷንና የአፍሪካ መዲና እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችውን አዲስ አበባ ገጽታና እድገት ከመገንባት ባሻገር ለነዋሪዎቿ ምቹ አካባቢ ከመፍጠርና ቱሪዝምን ከማጐልበት አኳያ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ማኔጅመንቱና መላው ሠራተኛ ያምናል ብሏል - በመግለጫው፡፡
“ሸገርን ማስዋብ” ፕሮጀክት ዓላማ ባንኩ ተቋማዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ቀደም ሲል እየሰራባቸው ካሉ ዘርፎች ጋር የሚጣጣም በመሆኑ የዚህ ፕሮጀክት አጋር በመሆኑ ደስታችን የላቀ ነው ብሏል - ባንኩ:: ባንኩ ወደፊትም የከተማዋን ገጽታ በማስዋብና በማሻሻል ነዋሪዎቿን ተጠቃሚ በሚያደርጉ መሰል ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ አገራዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጿል፡፡  
የአዲስ አበባን ወንዞች ዳርቻ የማልማት ፕሮጀክት ከእንጦጣ ተራራ እስከ አቃቂ የሚደርስ 56 ኪ.ሜ የሚሸፍን ሲሆን በአጠቃላይ ለፕሮጀክቱ እውን መሆን 29 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ተብሏል::

Read 1743 times