Monday, 06 May 2019 13:13

በቤኒሻንጉል በደረሰ ጥቃት በርካቶች ተገደሉ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(6 votes)

   - የ10 ብር የትራንስፖርት መልስ የብዙዎችንን ህይወት ቀጥፋለች
           - ከ3ሺ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል
                      

         በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዳንጉር ወረዳ በተነሳ ግጭት የ21 ሰዎች አሰቃቂ ግድያን ተከትሎ፣ በአዊ ዞን አስተዳደር በሚገኘው ዳውሮና ጃዊ ወረዳ በጉሙዝ ተወላጆች ላይ በተከፈተ የአፀፋ ጥቃት በርካቶች በጅምላ መገደላቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ም/ፕሬዚዳንት አቶ አዲጐ አምሳያ - ለአዲስ አድማስ አስታወቁ፡፡
ሴቶችና ህፃናትን ጨምሮ በርካታ የጉሙዝ ተወላጆች ባልገመቱት መንገድ በዱላ፣ በገጀራና በጦር መሳሪያ ጥቃት እንደደረሰባቸው ም/ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል፡፡ በአንድ መንደር ውስጥ የጅምላ ጭፍጨፋ በሚያስብል ሁኔታ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የተናገሩት አቶ አደጐ፤ ጥቂት የተረፉ ሰዎች በሆስፒታል ተኝተው ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሌሎቹ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመተባበር በግልገል በለስ መጠለያ እንደተጠለሉ የገለፁት አቶ አድጐ፤ አብዛኛዎቹ ከጥቃቱ የተረፉት ህፃናቶች እንደሆኑና ቤተሰቦቻቸውን ግን በጥቃቱ መገደላቸውን ተናግረዋል፡፡
ጥቃቱን ፈጽመዋል የተባሉ ተጠርጣሪ ግለሰቦችን ለመያዝ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን የገለፁት ም/ፕሬዚዳንቱ፤ ከአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመነጋገር ሁኔታው እንዲረጋጋ በማድረግ በአሁኑ ሰአት ሰላም መስፈኑን ጠቁመው፤ ሆኖም በፌስቡክ በሚሠራጩ ሀሰተኛ ወሬዎች ማህበረሰቡን ሙሉ በሙሉ አረጋግቶ፣ ወደ ቀድሞ ህይወቱ ለመመለስ ክልሉ መቸገሩን አመልክተዋል፡፡
በዳንጉር ወረዳ በአማራ ክልል ተወላጆች ላይ በደረሰው ጥቃት 21 ሰዎች መገደላቸውንና ከ30 በላይ ጥቃቱን አድርሰዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች፣ አንድ የፖሊስ አባልን ጨምሮ መያዛቸውን ም/ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡ በተፈጠረው ችግር ከቀያቸው የተፈናቀሉ ከ3ሺህ በላይ የአማራ ክልል ተወላጆችን የምግብና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ ለማዳረስ ክልሉ እየሠራ መሆኑን የፀጥታ ስጋት እንዳይኖርም የክልሉ ፀጥታ አስከባሪዎች ጥበቃ እያደረጉ መሆኑን አክለው ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም ከመቶ በላይ ቀስት እና መወርወሪያ መያዛቸውንም ገልፀዋል፡፡  
የዚህ ሁሉ ግጭትና እልቂት መነሻ የ10 ብር መልስ ነው ይላሉ - ምንጮች፡፡ ከዳንጉር ወረዳ ወደ ቆሳ ቀበሌ በትራንስፖርት ለመጓዝ የአንድ ጊዜ ጉዞ ክፍያ 40 ብር ነው፡፡ ይሄ የተለመደ ክፍያ ሲሆን፤ “ባለፈው ሳምንት  ግን 50 ብር አስከፍለኸኛል ከዚህ በፊት 40 ብር ነው ዋጋው፤ 10 ብሬን መልስልኝ” በማለት አንድ የጉሙዝ ተወላጅ ተሳፋሪ ከሹፌሩ ጋር ክርክር ይጀምራል፡፡ ሹፌሩ አልመልስም ይላል፡፡
ሹፌሩ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ሁኔታ ሦስት ጊዜ ችግር መፍጠሩን የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ ሹፌሩ እንዲህ አይነት ችግር ከመፍጠር እንዲገታ መክረነው ነበር ይላሉ፡፡
ጭቅጭቅ ከተነሳበት ቦታ ወደ 7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ካምፕ ፖሊሶች ለመጥራት ተሳፋሪዎችን በሙሉ በማውረድ፣ መኪናውን ይዞ እንደሄደና ፖሊስ ይዞ እንደመጣ ነዋሪዎች ይገልፃሉ፡፡ “ሹፌሩ ፌደራል ፖሊስ ለመጥራት ሲሄድ የጉሙዝ ተወላጆች ከጫካ ሆነው ከመኪናው የወረዱትን ተሳፋሪዎች በቀስት እየመቱ ነበር” የሚለው ግዛቸው ገዛኸኝ የተባለ፤ የዓይን እማኝ ድርጊቱን በአይኑ ማየቱን ይናገራል፡፡ “የመጣው የፌደራል ፖሊስ አባል ብቻውን በመሆኑ ወደ ላይ ተኩሶ ለማረጋጋት ሞክሮ ነበር፤ ነገር ግን እሱም ተመታ” ይላል የአይን እማኙ፡፡  
“አብዛኛዎቹ በሦስት ቀስት ነበር የተመቱት፤ ህፃናት ሳይቀር ሞተዋል፡፡ አንዲት ሴትን በቀስት ገለዋት እየደፈሯት ነበር ልዩ ሃይል የደረሰው” ይላል - ግዛቸው፡፡
በእሱ እጅ ዘጠኝ አስከሬን ማንሳቱን የሚናገረው ግዛቸው  ገዛኸኝ፤  እናት ከልጇ ጋር የተገደለችበት ሁኔታም እንደነበር ይገልፃል፡፡
በወቅቱ ጥቃት አድርሰዋል ያልናቸውን ሁለት የጉምዝ ወጣቶችን ይዘን ነበር፤ “አትግደሉን ተከፍሎን ነው፤ ማን እንደከፈለን እናሳያችኋለን” ብለውን ሁለቱንም ለልዩ ሃይል አስረክበናቸዋል ያለው ግዛቸው፤ ጉዳዩን የያዘው ልዩ ሃይል ግን ውጤቱን አልነገረንም ብሏል፡፡
በዚህ ግጭት ሦስት ሺህ ሃያ አምስት ነዋሪዎች ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸው ታውቋል፡፡

Read 9391 times