Sunday, 05 May 2019 00:00

“ጉባኤው የዘመናት የህዝበ ሙስሊሙን ጥያቄ የመለሰ ነው”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

የኢትዮጵያ እስላማዊ ም/ቤት (መጅሊስ) ሁሉንም ያማከለ፣ ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆኖ በሃይማኖቱ ልሂቃንና ታማኞች እንዲዋቀር መወሰኑ፣ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን የዘመናት ጥያቄ የመለሰ መሆኑን የቀድሞ የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡
ባለፈው ረቡዕ በሸራተን አዲስ ጠ/ሚኒስትሩን ጨምሮ ከ300 ላይ ሰዎች በተገኙበት በተከናወነው ጉባኤ ላይ ቅሬታ ሲቀርብበት የነበረው ነባሩ መጅሊስ በገዛ ፍቃዱ ከስልጣን ለመልቀቅ መወሰኑ ታሪካዊ ተግባር ነው፤ ብዙዎች መስዋዕትነት የከፈሉበትን ጥያቄም የመለሰ ነው ተብሏል፡፡
የጉባኤውን ውጤት አስመልክቶ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ ጥናት ኮሚቴ አባል ኡስታዝ ኑሩ ያሲን፤ “በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ ውስጥ እስካሁን ድረስ ያልታየ ታሪካዊ ተግባር ነው” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ዋነኛ ጥያቄ ሆኖ የዘለቀው ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ነፃ የሆነና ሁሉን ያማከለ መጅሊስ እንዲቋቋም እንዲሁም ህዝበ ሙስሊሙን ባላግባባ መንገድ ወደ ስልጣን የመጣውና በስልጣን ላይ የቆየው የመጅሊስ አመራር እንዲወርድ የሚል ነበር ያሉት ኡስታዝ ኑሩ፤ በሸራተኑ ስብሰባ ነባሩ መጅሊስ ከስልጣን ወርዶ ሁሉን አቀፍ መጅሊስ በአዲስ አወቃቀር እንዲደራጅ መወሰኑ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል፡፡ የህዝበ ሙስሊሙ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ ያገኘበት ጉባኤም መሆኑን አክለው ገልፀዋል፡፡
“በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ መግባባት ስልጣን ላይ የነበረ መጅሊስ ስልጣን ለህዝብ ጥያቄ ያስረከቡበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው” ያሉት ኡስታስ ኑሩ፤ ሁነቱ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን አንድነት ያረጋገጠም ነው ብለዋል፡፡
በእለቱም በፈቃዱ ከስልጣን በወረደው መጀሊስ ምትክ የባለ አደራ መጅሊስ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ 26 አባላት ያሉት ጊዜያዊ የባለአደራ የኡለሞች ም/ቤትና ሰባት አባላት ያሉት ጊዜያዊ የመጅሊስ ቦርድ መቋቋሙንም ኡስታዝ ኑሩ አስታውቀዋል፡፡
እነዚህ ሁለት አካላት በኢትዮጵያ ሙስሊሞች መዋቅራዊ ለውጥ ኮሚቴ ተጠንቶ በቀረበው የመዋቅር ማሻሻያና የመጅሊስ ምርጫ አከናወን መሰረት ቀጣዩ የጋራ መጅሊስ በህዝብ የሚመረጥበትን መንገድ ያመቻቻሉ ተብሏል፡፡ ምርጫውንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ያከናውናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኡስታዝ ኑሩ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ምሁራንና የሃይማኖቱ ልሂቃን አስተዋፅኦ ታሪካዊ እንደሆነም ተነግሯል፡፡   

Read 6768 times