Monday, 06 May 2019 00:00

የኢትዮጵያ ፕሬስ - ከአፈና ወደ ፈተና

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

“ጋዜጠኞች ተፈተዋል፤ መረጃ ግን ታስሯል”

           የአለማችን አገራትን አጠቃላይ የፕሬስ ነጻነት ሁኔታ በመገምገም በየአመቱ የአገራትን ደረጃ ይፋ የሚያደርገው ሪፖርተርስ ዊዛውት ቦርደርስ የተባለው አለማቀፍ ተቋም እ.ኤ.አ በ2013 ነበር ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ በአመታዊ የፕሬስ ነጻነት ደረጃ ሪፖርቱ ውስጥ ያካተተው፡፡
ተቋሙ በአመቱ ይፋ ባደረገው አለማቀፍ የፕሬስ ነጻነት ደረጃ ውስጥ ከተካተቱ 180 የአለማችን አገራት መካከል የ137ኛ ደረጃን የያዘችው ኢትዮጵያ፤ በቀጣዩ የ2014 አመት ደግሞ የፕሬስ ነጻነት ሁኔታዋ ይበልጥ ከፍቶ ወደ 143ኛ ደረጃ ዝቅ አለች፡፡ በቀጣዮቹ ሁለት አመታት አንድ ደረጃን ብቻ በማሻሻል በ142ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ የዘለቀችው ኢትዮጵያ፤ እ.ኤ.አ በ2017 ግን የፕሬስ ነጻነቷ የባሰ አሽቆልቁሎ 150ኛ ደረጃ ላይ ተቀመጠች:: የኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ደረጃ በ2018 ምንም መሻሻል ሳያሳይ፣ በዚያው የ150ኛ ደረጃ ላይ መቀጠሉንም ተቋሙ በአመቱ ባወጣው አለማቀፍ ሪፖርት አስታውቆ ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ግን፣ የታሰሩ ጋዜጠኞችና ጦማርያን መፈታታቸውን ጨምሮ አገሪቱ በፕሬስ ነጻነት ረገድ ተጠቃሽ ለውጥ እንድታስመዘግብ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ እርምጃዎች ተወሰዱ፡፡ የሃሳብ ነጻነትንና የመገናኛ ብዙሃን እንቅስቃሴን በማፈን ለረጅም አመታት ስትወነጀል የኖረችው ኢትዮጵያ፤ በ2018 የፈረንጆች አመት ማብቂያ ላይ ግን፣ ከአስርት አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድም ጋዜጠኛ ወይም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ያልታሰረባት አገር መሆኗን  በርካታ ዓለማቀፍ  መገናኛ ብዙሃን በአድናቆት ዘገቡ፡፡
በሰኔ ወር ላይ የቀደመው መንግስት ለአመታት ዘግቷቸው የነበሩ 246 ያህል የተለያዩ የዜና ድረ-ገጾችንና የጦማርያን ገጾችን የከፈተው የዶ/ር ዐቢይ መንግስት፤ መቀመጫቸውን በውጭ አገራት ያደረጉና እንደ ጠላት የሚታዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ወደ አገር ውስጥ ገብተው በነጻነት እንዲሰሩ ፈቀደላቸው፡፡ በተደጋጋሚ ይታይ የነበረው የኢንተርኔት መዝጋት እርምጃ እንዲቀር በማድረግና ጋዜጠኞችን ለማሰር ያለአግባብ ጥቅም ላይ ይውል የነበረውን የጸረ ሽብርተኝነት ህግ በማሻሻል ረገድም አዲሱ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሰርቷል፡፡ የዶ/ር ዐቢይ መንግስት ከአንድ አመት አለፍ ባለው ቆይታው ያከናወናቸው መሰል ተግባራት አገሪቱ በፕሬስ ነጻነት ረገድ ከፍተኛ መሻሻል እንድታሳይና አምና ከነበረችበት የ150ኛ ደረጃ 40 ደረጃዎችን በማሻሻል፣ በዘንድሮው የፕሬስ ነጻነት ሪፖርት፣ በ110ኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡
በአገሪቱ ባለፈው አንድ አመት ውስጥ የታየውን ጉልህ የፕሬስ ነጻነት ሁኔታ መሻሻል ከግምት ውስጥ ያስገባው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኒስኮም፤ የአለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በኢትዮጵያ እንዲከበር የወሰነ ሲሆን ከሰሞኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ሰላምን ለማምጣት፣ ለማስጠበቅና ለማቆየት እንዲሁም የፕሬስ ነጻነትን ለማስፈን ላደረጉት የላቀ አስተዋጽኦ የ2019 የሰላም ተሸላሚ አድርጓቸዋል፡፡
በአዲስ አበባ የጀርመን ድምጽ ዘጋቢ የሆነው ጋዜጠኛ ዮሐንስ ገ/እግዚአብሔር፤ ጋዜጠኞች ቀደም ሲል አንድን ዘገባ ለማዘጋጀት ቀና ትብብር ከማጣት ጀምሮ ለእንግልት፣ ግፋ ሲልም ለእስር ይዳረጉ እንደነበር አስታውሶ፣ ባለፈው አንድ አመት ግን አንፃራዊ የሚዲያ ነፃነት መፈጠሩን ይገልፃል፡፡
“ለስራችን እንቅፋት የሆኑ ብዙ ተግዳሮቶች ነበሩ፤ ፖሊስ እንኳን ፎቶ ስታነሳ ሲያይ ያስር ነበር” ያለው ጋዜጠኛው፤ አሁን በነፃነት ተንቀሳቅሶ የመስራት አንፃራዊ እድል ተገኝቷል ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ ከመንግስት በኩል አስፈላጊ የዘገባ መረጃዎችን የማግኘት እድል በእጅጉ መቀነሱን ጋዜጠኛ ዮሐንስ ይናገራል፡፡ “አሁን እርግጥ ነው ጋዜጠኞች ተፈተዋል፤ መረጃ ግን ታስሯል” ይላል፤ ጋዜጠኛው፡፡
አንጋፋው የአሜሪካ ድምጽ ጋዜጠኛ መለስካቸው አመሃ በበኩሉ፤ ጋዜጠኞች ከእስር መለቀቃቸውና የተዘጉ ድረ ገፆች መከፈታቸው ቀደም ሲል በመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ላይ የነበረውን የፍርሃት ድባብ የሰበረ እርምጃ ነው፤ ይሄ ለሀገሪቱ ቀጣይ የሚዲያ ነፃነት ጉዞም መልካም እመርታ ነው ብሏል፡፡
ባለፈው አንድ ዓመት የሀገሪቱ የፕሬስ ነፃነት መሻሻል ማሳየቱን የገለፀው የአሶሼትድ ፕሬስ የአዲስ አበባ ዘጋቢው ጋዜጠኛ ኤልያስ መሠረት በሰጠው አስተያየት፤ አዳዲስ ሚዲያዎች መምጣታቸው የተፍታታ የመገናኛ ብዙሃን ድባብ ፈጥሯል ይላል:: ይሁን እንጂ  አሁንም በገበያ እጦትና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በተከፈቱ በጥቂት ቀናት ውስጥ የሚከስሙ ፕሬሶች እንዳሉ ይገልጻል፡፡  
የሚዲያ ጽንፈኝነት አንዱ የሀገሪቱ ችግር እየሆነ መምጣቱን የተናገረው ጋዜጠኛው፤ በዚያው ልክ ከመንግሥት መረጃ ማግኘት አሁንም አዳጋች ሆኖ መቀጠሉን ይጠቅሳል፡፡ “መረጃዎችን ለመንግስት መገናኛ ብዙኃን ብቻ ለይቶ መስጠት አሁንም ያልተቀረፈ ችግር ነው፤ ለሚዲያዎች ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኗል” ብሏል ጋዜጠኛ ኤልያስ፡፡
የአለም የፕሬስ ቀን በኢትዮጵያ
የአለም የፕሬስ ቀን በአለማቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ መከበሩን በበጐ የሚያነሱ ጋዜጠኞች፤ ለሀገሪቱ የገጽታ ግንባታ በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ በዓሉ በአዲስ አበባ መከበሩ ለሀገሪቱ ፕሬስ የመንፈስ መነቃቃትን ይፈጥራል የሚለው ጋዜጠኛ መለስካቸው አመሃ፤ ለሀገሪቱ የፕሬስ ነፃነት እውቅና መሠጠቱ የበለጠ ነፃነቱ እንዲጠናከር አጋዥ ነው ብሏል፡፡
የጋዜጠኛ መለስካቸውን ሃሳብ የሚጋራው ጋዜጠኛ ዮሐንስ በበኩሉ፣ በአዲስ አበባ መከበሩ ለሀገሪቱ የገጽታ ግንባታ ፋይዳው የጐላ ነው ይላል:: ይሁን እንጂ በዓሉን አስመልክቶ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ሲሰነዘሩ የነበሩ አስተያየቶች የሀገሪቱን የፕሬስ ይዞታ በትክክል የቃኘ እንዳልነበር መታዘቡን ጋዜጠኛው ይገልፃል፡፡
በቀጣይ የሀገሪቱ ሚዲያዎች በኃላፊነት ስሜት፣ በተለይ በሀገሪቱ በሚታዩ ግጭቶችና መፈናቀሎች ላይ አተኩረው ሊሠሩ እንደሚገባ ሁሉም ጋዜጠኞች በጋራ ይስማማሉ፡፡
“ሰዎች በቀስት፣ በገጀራና በጥይት በሚጋደሉበት ሀገር፣ በስፖርታዊና መዝናኛ ጉዳዮች ላይ አተኩረው የሚሠሩ ሚዲያዎች መበራከት፣ ኃላፊነት የጐደለው የሚዲያ እንቅስቃሴ መጐልበቱን አመላካች ነው” ሲሉ ይተቻሉ ጋዜጠኞቹ፡፡


Read 6281 times