Sunday, 05 May 2019 00:00

ከልጅነት እስከ እውቀት የታገሉ ጎምቱ ፖለቲከኛ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 - ብሔራዊ የሐዘን ቀን ታውጆላቸዋል
                 - ሥርዓተ ቀብራቸው ነገ ይከናወናል


           ድንገተኛ ህልፈታቸው ባለፈው ቅዳሜ ሚያዚያ 19 ቀን 2011 ዓ.ም የተሰማው የቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አስከሬን በዛሬው ዕለት ወደ ሀገር ቤት እንደሚገባ የተነገረ ሲሆን የቀብር ሥነ ስርአታቸውም ነገ በአዲስ አበባ ዊንጌት ት/ቤት አካባቢ በሚገኘው ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን እንደሚፈፀም ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሀቀኛነትና የህሊና ታማኝነት ምሣሌ ተደርገው በብዙዎች የሚጠቀሱት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ ላለፉት 50 አመታት ከተማሪነት ጊዜያቸው ጀምሮ ያልተሳተፉበት የፖለቲካ ትግል የለም ማለት ይቻላል፡፡ ከተማሪነት ጀምሮ ወዳጃቸው የነበሩት ፖለቲከኛው አቶ አስራት ጣሴ፤ “የመሬት ላራሹ መፈክር ይዞ ከሌሎች ተራማጅ ሃይሎች ጋር ታግሏል፤ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ህብረት እንዲመሠረትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል” ይላሉ፡፡
“ዶ/ር ነጋሶ ያመነበትን ሃሳብ ለማራመድ ችግር የለበትም፤ ከዚህ ወገን ተቃውሞ ይመጣብኛል ይሄን አስከፋለሁ ብሎ አያስብም፤ ያመነበትን ሃሳብ በመርህ ላይ ተመስርቶ ይከራከራል” የሚሉት አቶ አስራት፤ “ዶ/ር ነጋሶ ጠንካራ የመርህ ሰው ነበር” ሲሉ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡
በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት ሌላው የዶ/ር ነጋሶ ወዳጅና የትግል አጋር አቶ ተመስገን ዘውዴ በበኩላቸው፤ “ዶ/ር ነጋሶ ሃቀኛ፣ ለሀገር አሳቢና የጠንካራ ዲስፒሊን ባለቤት ናቸው” ሲሉ በዚህ ባህሪያቸው ሁሌም እንደሚደነቁባቸው ይናገራሉ፡፡ “የዶ/ር ነጋሶ ህልፈትም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በሀቀኝነትና በመርህ ህወሓት ላይ ክፍተት ይፈጥራል” ብለዋል አቶ ተመስገን ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፡፡
ዶ/ር ነጋሶ ለዲሞክራሲ እውን መሆን የታገሉ፣ ሀገርን የሚገነቡ ጠንካራ ስራዎችን የሠሩ ሰው ናቸው ያሉት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሌ ሀሰን ናቸው:: የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ም/ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሣ በበኩላቸው ዶ/ር ነጋሶ የመብት ታጋይና ተሟጋች ነበሩ ይሏቸዋል::
እኔ በግሌ እሳቸው ከድርጅት ከወጡ በኋላ ነው ወደ ድርጅቱ የመጣሁት ነገር ግን ትልቅ አክብሮት ነው ያለኝ፡፡ ካወኳቸው ጊዜ ጀምሮ በማበረታታት አቅጣጫዎችን በማሳየት ሲደክሙ ቆይተዋል በኃላፊነት ከመምጣቴ በፊት በምሠራው ስራዎች ውስጥ እየደወሉ በግሌ ሲያበረታቱኝ ሲመክሩኝ ሲያገኙኝም በመምከር በማበረታታት ነበር የሚታወቁት አቅጣጫን በማሳየት ነው የሚያውቁት እና በጣም የካበተ ልምም ያላቸው ጠንካራ ስብዕና ያላቸው አገራቸውን እና ህዝባቸውን ከማንም በላይ የሚወዱ ማንኛውንም አይነት መስዋዕት ለመክፈል የተዘጋጁ ነበሩ - ይላሉ አቶ ሽመልስ፡፡
የደርግ ውድቀትን ተከትሎ ከኢህአዴግ በቀረበላቸው ጥሪ መሠረት፣ ከሚኖሩበት ጀርመን ወደ ሀገራቸው ተመልሰው፣ የኦህዴድ አባል በመሆን፣ ከማስታወቂያ ሚኒስትርነት እስከ ኢፌዲሪ ፕሬዚዳንትነት የዘለቀ የ10 ዓመት መንግስታዊ አገልግሎት አበርክተዋል -  ዶ/ር ነጋሶ፡፡
የመንግስት አካሄድ ከፖለቲካ እምነታቸውና መርሃቸው ጋር ያልተጣጣመላቸው ዶ/ር ነጋሶ፤ የፕሬዚዳንትነቱ ስልጣን ይቅርብኝ ብለው ከመንግስት አመራር ለመልቀቅ ጨርሶ አላመነቱም:: ይህን በማድረጋቸውም ለጤና መታወክ፣ ለጉስቁልናና ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡ በተደጋጋሚ  መድኃኒት መግዣ አጥተው ተቸግረው እንደነበር በህይወት ሳሉ ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡ ጣራው በተነደለ የሚያፈስ ቤት ለመኖር የተገደዱት ዶ/ር ነጋሶ፤ ቤቱ ይታደስልኝ ብለው ባመለከቱበት ወቅት “ጭራሽ ቤቱን ለመንግስት አስረክበህ ልቀቅ” ነው የተባሉት፡፡
ከፕሬዚዳንትነት በለቀቁ ማግስት በግላቸው ለፓርላማ አባልነት ተወዳድረው ማሸነፋቸውን ተከትሎ፣ መንግስት በፖለቲካዊው ውሳኔ የሚገባቸውን ጥቅማ ጥቅሞች በመንፈግ፣ የጉስቁልና ህይወት እንዲገፉ እንዳደረጋቸው ራሳቸው በአንደበታቸው ተናግረውታል - ለአዲስ አድማስ፡፡
ይህንን በቅርበት የሚያውቁት አቶ አስራት፤ “ዶ/ር ነጋሶ በአጠቃላይ በተወሰደበት የቂም እርምጃ ብዙ ተጐድቷል” ይላሉ፡፡ በአንድ ወቅት ከባለቤቱ ደመወዝ በቀር ምንም አይነት ገቢ የሌለው በመሆኑ፣ የልብ ቀዶ ጥገና አድርጐ፣ ወደ አሜሪካን ሀገር ተመልሶ ሄዶ፣ በቀጠሮው መሠረት የጤንነት ማረጋገጫ ማድረግ አልቻለም ነበር፣ ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ፡፡
ህክምና በማጣት ብዙ አስቸጋሪ ወቅቶችን ማሳለፋቸውን የሚያስታውሰው የ “ዳንዲ የነጋሶ መንገድ” መጽሐፍ አዘጋጅ ዳንኤል ተፈራ በበኩሉ፤ የመድሃኒት መግዣ አጥተው ብዙ ጉስቁልና ደርሶባቸው ነበር” ይላል፡፡ ቢያንስ ካለፈው አንድ አመት ወዲህ በእነ ዶ/ር ዐቢይ ድጋፍ የተሻለ ህክምና እያገኙ ባለበት ወቅት ህይወታቸው ማለፉ የሚያስቆጭ መሆኑን ዳንኤል ይናገራል፡፡
 “ዶ/ር ነጋሶ የቁስ ጥቅም የሚያታልላቸው አሊያም ለገንዘብና ለቁስ ፍቅር የነበራቸው ሰው አልነበሩም” ሲሉ የሚመሰክሩላቸው የቅርብ ወዳጆቻቸው፤ “በተደጋጋሚ ቤቴ ይታደስልኝ፣ እንደ ቀድሞ ፕሬዚዳንትነቴ ጥቅሜ ይከበርልኝ” ሲሉ አቤቱታ የሚያቀርቡት በዋናነት ጥቅሙን ፈልገውት ሳይሆን በህግ የተሰጠ መብትን በፖለቲካ መሻርን ለመቃወም ነበር ይላሉ፡፡ እሳቸውም በተደጋጋሚ ለመንግስት አካላት በሚጽፏቸው የአቤቱታ ደብዳቤዎች “ተማጽኖ” ሳይሆን ህጉን ጠቅሰው መብታቸውን ይጠይቁ እንደነበር ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ይገልፃሉ፡፡ “ህግ የሰጠኝን መብት በፖለቲካ ውሳኔ መሻር አትችሉም” የሚል ክርክር ነበር ሲያቀርቡ የቆዩት፡፡
ነገር ግን የሰማቸው አልነበረም፡፡ ትግላቸው ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል፡፡ በአዋጅ የተደነገገላቸውን የፕሬዚዳንትነት ጥቅማ ጥቅም ሳያገኙ እስከ ወዲያኛው አሸለቡ፡፡
እንደ መጽናኛ የሚቆጠር ነገር አለ ከተባለ፣ በ11ኛው ሰዓት ላይ የአቶ ለማ መገርሣ የኦሮሚያ ክልል አመራር ከአንድ አመት በፊት ደመወዝ የሚያገኙበትን የአማካሪነት ስራን ጨምሮ የመኪናና የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መወሰኑ ነው፡፡ ህልፈታቸው እስከተሰማበት እለት ድረስም የህክምና ወጪያቸው ይሸፈን የነበረው እነ ዶ/ር ዐቢይና አቶ ለማ በፈቀደላቸው  የድጋፍ ፕሮግራም መሠረት መሆኑም ታውቋል፡፡
ዶ/ር ነጋሶ ለእሳቸው ባይደላቸውምና ኪሳቸው ባይሞላም የደግነትና ልግስና ችግር አልነበረባቸውም:: “ዶ/ር ነጋሶ በኪሣቸው ያላቸውን በደስታ የሚያካፍሉ ሰው ነበሩ” የሚሉት ፖለቲከኛው አቶ አንዷለም አራጌ በኪሣቸው 150 ብር ይዘው ለታክሲ የምትሆናቸውን ብቻ አስቀርተው ሰውን ለመደገፍ ይታትሩ ነበር” ሲሉ ይመሰክራሉ፡፡
ዶ/ር ነጋሶ ከዚህም ያለፈ የደግነትና የበጐነት ምግባር የሚፈጽሙ ልበ - ርህሩህ ሰው እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ሠብአዊነት ቅርባቸው፣ ሩህሩህነት ምግባራቸው የሆኑ ሰው እንደነበሩ ሴት ልጁ በጠና በታመመች ወቅት ከብዙ መውጣትና መውረድ በኋላ ለሳቸው በስልክ ችግሩን ነግሯቸው፣ ራሳቸው ምንም ባልነበራቸው ጊዜ በየኤምባሲው ዞረው የ10ሺ ዶላር ድጋፍ  አግኝተው በህንድ እንዳሳከሙለት ጋዜጠኛ አርአያ ተስፋማርያም ይናገራል፡፡
ዶ/ር ነጋሶ ልጄ በህክምና ላይ በነበረች ሰአት እንኳ ህንድ ድረስ እየደወሉ እንዴት ሆነች? ህክምናው ምን ይመስል ነበር?” እያሉ ይጠይቁኝ ነበር ይላል ጋዜጠኛ አርአያ፡፡
ዶ/ር ነጋሶ በቤተመንግስት ቆይታቸው ወላጆቻቸው በሞት የተለዩ ሁለት ታዳጊዎችን በራሣቸው ገንዘብ ያሳድጉ እንደነበርና በአሁኑ ወቅት እነዚያ ልጆች አድገው ለቁም ነገር መብቃታቸውን  ምንጮች ነግረውናል፡፡
 
ዶ/ር ነጋሶ ማን ናቸው?
ነጋሶ ጊዳዳ ሶለን
ወለጋ - ደንቢ ዶሎ በ1935 ዓ.ም ተወለዱ
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ ልዑል በእደ ማርያም ት/ቤት ተማሩ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ት/ት የመጀመሪያ ድግሪያቸውን፣ በጀርመን ጐተ ዩኒቨርስቲ ሁለተኛ ድግሪያቸውንና ሶስተኛ ድግሪያቸውን በታሪክ አግኝተዋል፡፡
በ1960ዎቹ በአዲስ አበባ የተማሪዎች ንቅናቄ ንቁ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡
ወደ አውሮፓ ለትምህርት በሄዱበት ወቅትም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግን) በጀርመን ካደራጁት ዶ/ር ነጋሶ ቀዳሚው ነበሩ
በ1983 ዓ.ም የደርግ መውደቅን ተከትሎ ከኦነግ ጋር የሃሳብ ልዩነት በማድረግ ወደ ኦህዴድ የገቡት ዶ/ር ነጋሶ በሽግግሩ ወቅት በማስታወቂያ ሚኒስትርነት አገልግለዋል፡፡
ከ1985-1993 ዓ.ም የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል
ከኢህአዴግ በሃሳብና በአላማ ከተለያዩ በኋላ በ1997 በደምቢ ዶሎ በግል ተወዳድረው የፓርላማ አባል በመሆን ለ5 አመታት በፓርላማው ቆይተዋል
ፓርላማ በነበሩ ጊዜም ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ መጀመሪያ ላይ የ6 የፖለቲካ ድርጅቶች ስብስብ የነበረውን መድረክን አደራጅተዋል፣ እንዳውም የመድረክ ስብስብ መሀንዲስ እየተባሉ ይጠሩ ነበር፡፡
በብሔርተኛ ድርጅት ውስጥ ረጅሙን ጊዜ ያሳለፉት ዶ/ር ነጋሶ ኋላም የብሔር ፖለቲካን ወደ ጐን ብለው አንድነት ለፍትህ እና ለዲሞክራሲ ፓርቲን ተቀላቅለዋል:: ፓርቲውን በፕሬዚዳንትነትም ለሁለት አመታት በላይ መርተዋል፡፡
እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ድረስም በሀገሪቱ በሚፈጠሩ ማናቸውም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ምክር አዘል አስተያየት እና አቋም በማራመድም ይታወቃሉ፡፡ በቅርቡ የጠ/ሚሩን 1ኛ ዓመት ለመዘከር በተዘጋጁ መድረኮች ላይም ዶ/ር ነጋሶ ንቁ ተሳታፊ ነበሩ፡፡
በ75 አመታቸው ህልፈታቸው የተሰማው ዶ/ር ነጋሶ ከቀድሞዋ ኢትዮጵያዊት ባለቤታቸው ሁለት ልጆች እንዲሁም ከአሁኗ አዋላጅ ነርስ ጀርመናዊት ባለቤታቸው 1 ልጅ አባት ነበሩ፡፡

Read 6368 times