Monday, 06 May 2019 12:47

በህንድ 22 ተማሪዎች ፈተና በመውደቃቸው ራሳቸውን አጥፍተዋል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ባለፈው ሳምንት ብቻ በህንድ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ፈተና ወስደው ማለፍ ያቃታቸው 22 ተማሪዎች ራሳቸውን ማጥፋታቸውን ሂንዱስታን ታይምስ ዘግቧል፡፡
በባዮሎጂ ፈተና ጥሩ ውጤት ማምጣት ባለመቻሏ ባለፈው ቅዳሜ ራሷን በእሳት አቃጥላ የገደለችዋን አንዲት ህንዳዊት ጨምሮ በድምሩ 22 ተማሪዎች ራሳቸውን በመስቀልና በሌሎች መንገዶች ለሞት መዳረጋቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡የአገሪቱ የትምህርት ቦርድ ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ ባለፉት የካቲትና መጋቢት ወራት በአገሪቱ አንድ ሚሊዮን ያህል ተማሪዎች ፈተናዎችን የወሰዱ ሲሆን 350 ሺህ ያህሉ ፈተናቸውን ለማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
በርካታ ቁጥር ያላቸው ህንዳውያን ተማሪዎች በፈተና መውደቃቸው በወላጆችና በአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ቁጣና ተቃውሞን መቀስቀሱን የጠቆመው ዘገባው፤ መንግስት ፈተናዎችን የሚያርምበት ቴክኖሎጂ ለተማሪዎች መውደቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ሲሉ መቃወማቸውን አመልክቷል፡፡ ራስን ማጥፋት በአገረ ህንድ ተማሪዎች ዘንድ እየተባባሰ የመጣ ክስተት መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ በሁለት የአገሪቱ ግዛቶች ውስጥ ብቻ ባለፈው አመት ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ከ50 በላይ ተማሪዎች ራሳቸውን ማጥፋታቸውንም አስታውሷል፡፡

Read 3389 times