Monday, 06 May 2019 12:35

የሁዋዌ የሞባይል ሽያጭና የገበያ ድርሻ አድጓል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የአፕልና የሳምሰንግ ሽያጭ ቀንሷል

     በ2019 የፈረንጆች አመት የመጀመሪያው ሩብ አመት አለማቀፍ የሞባይል ሽያጭ፣ የቻይናው ሁዋዌ የ50.3 በመቶ ጭማሪ ሲያስመዘግብ፣ አፕልና ሳምሰንግ ሽያጫቸው መቀነሱን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
ቻይናው ሁዋዌ ባለፉት ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ 59.1 ሚሊዮን የሞባይል ምርቶቹን ለአለማቀፍ ገበያ ማቅረቡንና የገበያ ድርሻውን ማሳደጉን የጠቆመው ዘገባው፤ የሁለቱም ተፎካካሪዎቹ አፕልና ሳምሰንግ የሞባይል ሽያጭ መቀነሱን አመልክቷል፡፡ ሁዋዌ በአለማቀፉ የሞባይል ገበያ ያለውን ድርሻ 19 በመቶ ማድረሱንና ከፍተኛውን የገበያ ድርሻ ከያዘው የአለማችን ቁጥር አንድ የሞባይል አምራች ኩባንያ ሳምሰንግ ጋር የነበረውን የገበያ ድርሻ ልዩነት ለማጥበብ መቻሉንም ገልጧል፡፡
አይፎንን የሚያመርተው የአሜሪካው ኩባንያ አፕል በታሪኩ ከፍተኛውን የ30.2 በመቶ የሩብ አመት የሞባይል ሽያጭ መቀነስ ማስተናገዱን የገለጸው ዘገባው፤ ኩባንያው በሩብ አመቱ 36.4 ሚሊዮን ሞባይሎችን ብቻ መሸጡንና የገበያ ድርሻው ወደ 11.7 በመቶ ዝቅ ማለቱን አስረድቷል፡፡
የደቡብ ኮርያው ሳምሰንግ ኩባንያ የሩብ አመት ሽያጩ በ8.1 በመቶ መቀነስ ማሳየቱንና በ3 ወራት ውስጥ 71.9 ሚሊዮን ሞባይሎችን መሸጡን የጠቆመው ዘገባው፤ያም ሆኖ ግን በአለማቀፉ የሞባይል ገበያ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ መቀጠሉን ገልጧል፡፡
ዚያኦሚ፣ ኦፖ እና ቪቮ በአለማቀፉ ሞባይል ገበያ የሩብ አመት ሽያጭ እንደ ቅደም ተከተላቸው እስከ ስድስተኛ ያለውን ደረጃ የያዙት ታዋቂዎቹ የሞባይል አምራች ኩባንያዎች መሆናቸውንም ዘገባው አክሎ አመልክቷል፡፡
የአለማቀፉ የሞባይል ገበያ አጠቃላይ ሽያጭ ላለፉት ስድስት ተከታታይ ሩብ አመታት መቀነስ በማሳየት መቀጠሉን የገለጸው ዘገባው፤ በሩብ አመቱ በአለማቀፍ ደረጃ የተሸጡ ሞባይሎች ቁጥር በ6.6 በመቶ መቀነስ ማሳየቱንና በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በአለማችን የተሸጡ ሞባይሎች ቁጥር 310.8 ሚሊዮን መሆኑን አመልክቷል፡፡

Read 1155 times