Monday, 06 May 2019 12:19

ሽግግር “የሙከራም የመከራም” ወቅት ነው!

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(2 votes)

ይህቺን ጦማር በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በኩል “ይድረስ” ያልኩበት ምክንያት የሀገራችንን ያለፈውን የአንድ ዓመት የአስተዳደር ሁኔታ ካየሁ በኋላ ሊታረሙ ይገባል ያልኳቸውን አሳሳቢ ጉዳዮች በማንሳት ትኩረት እንዲሰጣቸው ለማሳሰብ ነው፡፡ በሦስት ጉዳዮች ላይ ነው የማተኩረው፡፡ በቅድሚያ የመንግስትና የሀገር ምስጢሮች በየፌስቡኩ እየተዝረከረኩ መሆኑን እናያለን፡፡ ለጥቀን ስለ ባለስልጣናት ሹመትና ሽረት መብዛት እናነሳለን:: በመጨረሻም የመንግስት ባለስልጣናት በየመድረኩ ስለሚያሰሟቸው አወዛጋቢ ሃሳቦች በማንሳት ወደ ማጠቃለያው እናመራለን፡፡
በጥንት ዘመን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ዱቄት ይፈጭ የነበረው በሰው ኃይል፣ በድንጋይ ወፍጮ ነበር:: (ዛሬም አልፎ አልፎ በገጠር መንደሮች የድንጋይ ወፍጮ ሊኖር ይችላል) በድንጋይ ወፍጮ ጤፍ ሲፈጭ የወፍጮው ድምፅ አይሰማም፡፡ ባቄላ ሲፈጭ ግን መጁና ወፍጮው እየተፋጩ ባቄላውን ሲከኩና ሲያደቁ (ከባቄላው ትልቅነት የተነሳ) ድምጹ ከርቀት ይሰማል፡፡ ለዚህም ነው በምስጢር የተነገረ ጉዳይ በግልጽ በአደባባይ ሲነገር ስንሰማው “ኧረ ባክህ ሚስጢሬን የባቄላ ወፍጮ አታድርገው” የምንለው፡፡
የባቄላ ወፍጮን ጉዳይ አስቀድሜ ማንሳቴ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያለው ጉዳይ ለማንሳት ፈልጌ ነው፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት ካስተዋልናቸው ጉዳዮች አንዱ የመንግስትና የሀገር ምስጢሮች በተለያዩ መንገዶች እየሾለኩ መውጣታቸውና “በፌስቡክ ወፍጮ” እየተሰለቁ አደባባይ መዋላቸው ነው:: ችግሩ የምስጢሮቹ መሹለክ ብቻ አይደለም፡፡  የሾለኩት ምስጢሮች በግለሰቦችና በህብረተሰብ ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑ ነው፡፡
በየትም ሀገር ያሉ መንግስታት ውሳኔ ሊሰጡበት ያሰቡት ሹመትና ሽረት፣ ማሰርና መፍታት፣ መገንባትና ማፍረስ፣ ወዘተ. የመሳሰሉ ጉዳዮች በህብረተሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ወይም የተቃውሞና የድጋፍ መጠን ለመለካት፣ አንዳንድ ጊዜም ተጨማሪ መረጃዎችን ከህብረተሰቡ ለማግኘት በጸጥታ ሰራተኞች አማካይነት “ሚስጥር ነው” ተብሎ ወደ ህዝቡ እንዲደርስ ያደርጋሉ:: በእኛም ሀገር ይኸው ይፈጸም ነበር፡፡ አሁን አሁን በአክቲቪስቶች አማካይነት በየፌስቡኩ እየተለቀቁ ያሉት ምስጢሮች ግን ከዚህ የተለዩ ናቸው፡፡
መንግስታዊ ስልጣኑን የጨበጡት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በውስጣቸው በተለያዩ መድረኮች በሚያደርጓቸው ውይይቶች ላይ የፖለቲካ አመራር አባላቱ የሚያነሷቸው ሃሳቦች “እከሌ እንዲህ አለ፣ እንቶኒት እንዲህ ብላ መለሰቺለት፣ እንቶኔ ይሄም ያም ስልጣን ለእኔ ይሰጠኝ አለ፣…” ተብሎ በፌስቡክ አደባባይ በታዋቂ አክቲቪስቶች ሲለቀቅ አይተናል፣ አንብበናል፡፡
እንዲህ ያሉት የውስጥ የፖለቲካ ሽኩቻ ምስጢሮች በመንግስት የጸጥታ ሰራተኞች ከሚለቀቁ የህዝብ ስሜት መለኪያ መረጃዎች በጣም ይለያሉ:: በመንግስት ሆን ተብለው የሚለቀቁት መረጃዎች የተመጠኑና ውጤታቸውም ተገማች ነው፡፡ የፓርቲዎችን የስልጣን ሽሚያና የፖለቲከኞችን ሽኩቻ የሚያመላክቱ ምስጢሮች ግን ውጤታቸው ተገማች ካለመሆኑም በላይ፤ አንዱን ወገን ከፍ ሌላውን ዝቅ የሚያደርግ፣ አንዱን የሚያሞግስ ሌላኛውን የሚያኮስስ፣ ያልታሰበ ብጥብጥና ሁከት የሚቀሰቅስ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲህ ያለው መረን የለሽ የመረጃ ፍሰት በፖለቲከኞቹ መካከል መተማመን እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ በደጋፊዎቻቸውም መካከል ብጥብጥ የሚፈጥር ይሆናል፡፡
በርግጥ እዚህ ላይ የሚነሳው መሰረታዊ ጥያቄ “ምስጢር ማለት ምን ማለት ነው? ምስጢር የሆነውንና ያልሆነውን የሚለየው ማን ነው? በምን መስፈርት?...” የሚል ሊሆን እንደሚችል አስባለሁ:: ይሁን እንጂ፣ እነዚህን ጥያቄዎች ለህሊና ፍርድ ካልሰጠን የአንድ ጉዳይ ምስጢር መሆን አለመሆን አወዛጋቢ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡
አንድ የመንግስት ሰራተኛ ሲቀጠር በፊርማው አረጋግጦ የሚፈጽማት ቃለ መሀላ አለች:: ያቺ ቃለ መሀላ በውስጧ “በስራዬ አጋጣሚ የማገኛቸውን ምስጢሮች ልጠብቅ…” የሚል ሃሳብን ይዛለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች ተሿሚዎችም እንዲሁ መሀላ ይፈጽማሉ:: እነዚህ በፈጣሪ ስም ምለን የምናረጋግጣቸው ቃል ኪዳኖች መጠበቅ አለባቸው::
በስራው አጋጣሚ ያገኘውን የመንግስትና የሀገር ሚስጥር ያልጠበቀ የመንግስት ሰራተኛ፣ ከሥራ ከመባረር ጀምሮ በወንጀል እስከመጠየቅ የሚደርስ ቅጣት እንደሚጠብቀው በመንግስት ሰራተኞች ማስተዳደሪያ አዋጅ ተደንግጓል:: የመንግስት ባለስልጣናትን በተመለከተም በወንጀለኛ መቅጫ ህግ እና በፀረ-ሙስና አዋጅ ጭምር የሰፈሩ ቅጣቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስባለሁ፡፡
በመሆኑም እንደ ማህበረሰብ ኢትዮጵያውያን የጋራ አመለካከት ባልፈጠርንበት ሁኔታ ሀገርን ሊያፈርስ የሚችል መረጃን በገሀድ ማሰራጨትም ሆነ በሥራ አጋጣሚ የተገኘን ሀገራዊና መንግስታዊ ምስጢርን የሚያባክኑ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ የፓርቲ አባላትና አክቲቪስቶች ጭምር አግባብ ባለው ህግ መሰረት ሊጠየቁ ይገባል፡፡
ወደ ሁለተኛው ጉዳይ እናምራ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት እለት ጀምሮ ባለፈው አንድ ዓመት በርካታ ሰዎች ሲሾሙና ሲሻሩ አይተናል፣ ሰምተናል:: አንድ የሀገር መሪ ስልጣን ሲይዝ የራሱን ካቢኔ ማቋቋሙ የተለመደ ነው፡፡ ይህ ግን በተረጋጋና ህግን መሰረት ባደረገ አግባብ ሊፈጸም ይገባዋል፡፡ ይሁን እንጂ በእኛ ሀገር ይህ ሁኔታ እንዴት እንደሚፈጸም በግልጽ አይታወቅም:: በዚህም ምክንያት ህዝብ አገልጋይ የሆነ፣ ጠንካራ የአሰራር ስርዓት ሊፈጠር አልቻለም፡፡ መንግስታዊ ቢሮክራሲው (ሲቪል ሰርቪሱ) የተረጋጋ መሆን አልቻለም፡፡ (በመሀል በመሀሉ የተሾሙትንና የተሻሩትን ትተን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሁለት ጊዜ ሙሉ የካቢኔ ብወዛ አካሂደዋል፡፡ ይህም በመሆኑ አንዳንድ ሚንስቴር መ/ቤቶች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እስከ ሦስት ሚኒስትሮች ተፈራርቀውባቸዋል::)
በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የጠየቅኳቸው አንድ የሥራ አመራር (ማኔጅመንት) ምሁር፤ “እንዲህ ያለው ተደጋጋሚ ሹም ሽር የሚያሳየው ባለፈው አንድ ዓመት የተረጋጋ የመንግስት መዋቅር እንዳልነበር ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ሁለት፣ ሦስት ጠቅላይ ሚኒስትር አለመፈራረቁ መታደል ነው ወይም በበጎነት የሚታይ መልካም አጋጣሚ ነው:: ሁለት፣ ሦስት ጠቅላይ ሚኒስትር ቢፈራረቅ ኖሮ ሀገሪቱ ሀገር አትሆንም ነበር…” ነው ያሉኝ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግስታዊ መዋቅሩን መቀያየራቸውም ሆነ ባለ ስልጣኖቻቸውን መሾምና መሻራቸው በራሱ ችግር አይደለም፡፡ ይህ ሂደት ግን በስሜት ሳይሆን በጥናት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የሚሾሙት ሰዎች ስነ ምግባር፣ አካላዊና አእምሯዊ ብቃት፣ የትምህርት ዝግጅትም ሆነ የሥራ ልምድ በአግባቡ ሊፈተሽ ይገባዋል፡፡ ይህ ባለመደረጉ (ለምሳሌ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ተሹመው የነበሩ ጄኔራል በጥቂት ወራት ውስጥ ከስልጣን ተነሱ መባልን ሰማን፡፡ ለምን? ስንል በአንድ በኩል “የጡረታ ጊዜያቸው ስለደረሰ” የሚል ምክንያት ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ “በጤና ምክንያት ነው” የሚል ሰበብ ይቀርባል፡፡ እነዚህ ሁለት ምክንያቶች ግን ሰውየው ከመሾማቸው በፊት ሊጣሩ የሚችሉ ነበሩ፡፡
ሌላው ባለፈው አንድ ዓመት ያስተዋልነው ሊታረም የሚገባው ጉዳይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ባለስልጣናት የሚናገሯቸው አወዛጋቢ ቃላትና የሚጋጩ ሃሳቦች ናቸው፡፡ አበው “መታፈር በከንፈር” ይላሉ፡፡ ይህም ማለት ከአፋችን የሚወጡ ቃላት ወይ ያስከብሩናል ወይ ያስደፍሩናል ማለት ነው፡፡ ከመሪዎች የብቃት መለኪያዎች አንዱ ለማን ምን መናገር እንዳለበት አስቦና ተዘጋጅቶ መናገር ነው፡፡ ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት ኢህአዴግ ከሚታወቅባቸው ጉዳዮች አንዱ ከአናቱ ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅሮቹ ድረስ ያሉ ኃላፊዎች በአንድ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም ማራመዳቸው ብቻ ሳይሆን አንድ ዓይነት ቃላት ጭምር መናገራቸው ነበር፡፡ እንዲያውም በዚህ ጉዳይ “ኢህአዴጎች እንደ በቀቀን አንድ ዓይነት ቃል ይናገራሉ” እየተባለ ብዙ ጊዜ ይተቹ ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ ደግሞ የኢህአዴጎች መንደር መናበብ የሌለበት የጨረባ ተስካር ሆኗል፡፡ በዚህም ምክንያት “አፍ እላፊ” ንግግር ተበራክቷል:: በእላፊ ንግግር ሰበብ “ይቅርታ ጠይቅ” የሚባለው ሰው የዚያኑ ያህል በዝቷል፡፡ “ባለፈው እንዲህ ያልኩት እንዲያ ለማለት ነው” የሚለው ማስተካከያና ማስተባበያም ጥቂት የሚሰኝ አይደለም፡፡
ባደጉትና በሰለጠኑት ሀገሮች መሪዎች ለንግግር ወደ መድረክ ከመውጣታቸው በፊት ልምምድ (ሪሄርሳል) ያደርጋሉ፡፡ በእኛ ሀገር ግን ከእንቅልፉ ተነስቶ፣ ማይክራፎን ጨብጦ መግለጫ የሚሰጥ ባለስልጣን ጥቂት የሚሰኝ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት በተለይም ከቁጥር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ሲፋለሱ ይስተዋላል፡፡
በርግጥ “ፖለቲካ ማለት የመሆን ጥበብ ነው”:: እናም አንድ የፖለቲካ ሰው ዛሬ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ተነስቶ የተናገረውን ሃሳብ ከቀናት ወይም ከሳምንታት አሊያም ከወራት በኋላ በተመሳሳይ ቃላት መድገም አይጠበቅበትም፡፡ ማሻሻል፣ መለወጥ ወይም ያንን ትቶ አዲስ ሃሳብ ማቅረብ ይችላል:: ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ የፖለቲካ መተጣጠፍ በእኛ ማህበረሰብ ያልተለመደና ለመቀበልም አስቸጋሪ በመሆኑ መሪዎች ህብረተሰቡን የሚመጥን ንግግር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ለማጠቃለል አንዳንድ ነጥቦችን ላንሳ:: ኢህአዴግ የስለት ልጅ ይመስላል፡፡ ከ27 ዓመታት እድሜው 26ቱን ያሳለፈው በርካታ የፖለቲካ ሰዎችን (የራሱን አባላት ጭም) ጭዳና ፊዳ በማድረግ ነበር የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ላለፈው አንድ ዓመት “ጭዳና ፊዳ” ባለማድረጉ ነው መሰል እሱም ጤና የለው፣ ሀገሪቱም ጤና አጣች፣ ህዝቡም ሰላም አጣ፡፡ አሁን ህመሙ የጠናበት ይመስላል፡፡ ወይ ለይቶለት አልዳነ፣ ወይ ለይቶለት አላንቀላፋም:: በገመምተኛነት ያንጎላጃል፡፡ ውስጣዊ ሰላም የለውም፡፡ ከአናቱ እስከ እግር ጥፍሩ ያሉ አካላቱ አይናበቡም፣ አይደማመጡም፡፡
በዚህም ምክንያት ወለጋ ላይ ባንክ ሲዘረፍ፣ መቀሌ መኪና አግቶ አደ ከቢሬ ይጨፍራል:: ጅግጂጋ ቤተ ክርስቲያን አቃጥሎ እሳት ሲሞቅ፣ በጎንደር መስጊድ ይነዳል፣ ቁርኣን ይቀደዳል፡፡ ደሴ እንደ ዶሮ በፈላ ውሃ ሲጎንፍ፣ የሲዳማ ኤጀቶ የምክር ቤት አባላትን እንደ ቡና ይወቅጣል፡፡ በጌዲዮ ህፃናት ሲጮሁ፣ በመተከል እናት በቀስት ትወጋለች:: በባልደራስ ለስብሰባ የተጠሩ መንገደኞች ባላደራ ምክር ቤት ሲያቋቁሙ፣ በለገጣፎ “መጤ” ከንቲባዎች “የህገ ወጦችን” ቤት ያፈርሳሉ… እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ጤነኛነትን አያመለክቱም፡፡
ፕሬዝዳንት ኦባማ ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ “አፍሪካን የሚያስፈልጋት ጠንካራ መሪ ሳይሆን ጠንካራ ተቋማት ናቸው” ብለው ነበር፡፡ መሪዎች በመጡና በሄዱ ቁጥር የማያረገርጉ፣ የማይፈርሱና የማይናጉ ጠንካራ የፀጥታ ተቋማት ባለመፈጠራቸው ነው ዛሬ የህግ የበላይነት ሊረጋገጥ ያልቻለውና የሀገሪቱና የህዝቧ ሰላምና ፀጥታ አደጋ ላይ የወደቀው፡፡ እናም የመንግስት ትኩረት የተቋማት ግንባታ ላይ መሆን አለበት፡፡
አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት በየትም ሀገር የሚደረግ የሽግግር ወቅት “የሙከራም የመከራም ወቅት ነው”፡፡ በዚህም ምክንያት በሽግግር ሂደት በርካታ ስህተቶች ሊፈጸሙ ይችላሉ፡፡ ቁም ነገሩ ስህተቶች ለምን ተፈጸሙ ሳይሆን ስህተቶች መረን በለቀቀ ሁኔታ እንዳይሰሩ ጥረት መደረግ አለመደረጉ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግስት ይህንን ጥረቱን በተጨባጭ ሊያሳየንና ሊያረጋግጥልን ይገባል፡፡
ጸሐፊውን ኢሜይል አድራሻዋ፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1712 times