Monday, 06 May 2019 12:13

ቂምህን ሣትጥል የፍቅር መዝሙር አትዘምር!-

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

 እናንተ ኮከቦች፣
              ቁልቁል ተወርወሩ፣
          ቁጭ ያለን ከቆመው የፍጥፍጥ አጋጩት፣
          ጥሬውን ከብስል፣ የተኛን ከነቃው፣
               ደባልቃችሁ ፍጩት፡፡
                    

       አንዳንዴ ጥበብ የጣማት ነፍስ ግጥም አድርጋ ሥትጠጣው አሊያም እየተጐነጨች ሥታጠጥመው ፋሲካዋ የትየለሌ ነው፡፡ በተለይ “በደቡባዊቷ ኢራን  ማሺራዢ ከተማ ተወልዷል” ብሎ ገጣሚ በረከት በላይነህ ያስተዋወቀን ሀፊዝ፤ ደመና ላይ እንደ ውቂያኖስ የሚያሥዋኙ፣ ጽጌረዳ ያለ እሾህ የሚያሸትቱ፣ በፍልቅልቅ ደስታ የሚያሠክሩ ግጥሞች አሉት፡፡ የተራበን ልብ የሚያጠግቡ፣ የተጠማን ነፍስ በጅረት የሚያስጋልቡ ብዙ ስንኞች ይዟል:: ግጥም ደግሞ ፈንጠዝያው ውስጥ የሚሸሽጋቸው ጮሌ ሃሳቦች አማላይ ናቸው፡፡ በአደባባይ ላይ እየተነበቡ ለብቻ በጆሮ ሹክ የሚሉት ምስጢር አላቸው፡፡ ግጥም ሰባኪ፣ ግጥም አስተማሪ መሆን የለበትም የሚባለው ሃሳብ፣ የጥቂት ሰዎች አተያይ አይደለም፤ የጠቢባኑ ጉባኤ ያጨበጨበለት እውነታ ነው፡፡ ሃፊዝ የሚወደደው አንድም በዚህ ነው፡፡ ሳይንሱን አይደሰኩርም፤ ፖለቲካውን ፕሮፓጋንዳ አያደርግም፤ እርሱን ካድሬ ይስበክህ! ብሎ ለካድሬ ይተዋል፡፡ እርሱ አንድዋን ቀንበጥ ይሰጥህና ዳር ቆሞ ሳቅና ለቅሶህን መልሶ በስንኞቹ ከንፈር ላይ ያንጠለጥልልሀል፡፡ ከገባህ ገባህ፣ ካልገባህ አፍንጫህን ላስ፤ እርሱ ምን አገባው!! የራስህ ጉዳይ! “የለውጥ ጫፍ” የሚለው ግጥሙ ከኮረኮሩኝ ግጥሞቹ መካከል አንዱ ነው፡፡ ልቃቂቱን ብተረትረው ምን ይመስል ይሆን ብዬ ሙዳዩ ውስጥ ገብቻለሁ፤  የራሴ ጉዳይ፤ ሃፊዝ ምን አገባው!
አበቦች!
እርገፉ፣ ተቀነጣጠሱ፣ እንክትክት በሉ፤
መልካችሁ ይረገጥ፣ ከቀለም ተጣሉ፡፡
ፍራፍሬ ሁላ!
ና ተላጥ፣ ተጨመቅ፣ ይቺን ዋንጫ ሙላ፡፡
ርዕሱ እንደጠቆመን ለውጥ እንዲህ ነው፡፡ አበባ ይረግፋል፣ ይቀነጣጠሳል፣ እንክትክት ይላል፡፡ ቀለሙ የለም፤ ውበቱ ይጠወልጋል፤ ይጠፋል፡፡ ፅጌረዳ እንዳማረባት አትዘልቅም፡፡ ምክንያቱም ለውጥ ነው፤ ኮረዳ ደሟ ሲፍለቀለቅ ዐይኖችዋ በብርሃን እሳት ሲንከባለሉ፣ በብርሃን ጸዳል ስትከበብ ያኔ አበባ ነች:: ውበት ለራሷና ለተመልካቿ ልብ ፈንቃይ፣ ልብ አባባይ ነው፡፡ ያያትን ሁሉ ትሰርቃለች፤ የተከተላትን ሁሉ ታጠምዳለች፡፡ ግን አትዘልቅም፤ ፍሬ ልታፈራ ትጠወልጋለች፡፡… ስትወልድ መጠጥ ትላለች፤ ግን ብዙ ትሆናለች፤ እምቡጦችን ትተካለች፡፡ ብዙ ተስፋ እንደ ክብሪት ጭራ ዐለምን ታደምቃለች፤ ጥርሶችዋ በሌላ ጥርሶች ተደብቀው ይመጣሉ፡፡ ዐይንዋን ጨፍና የሚንተገተጉ ዐይኖች ትልካለች፡፡ ሕይወት ይቺው ናት! ተታልላ ታታልላለች! ሜዳዋ ላይ ስቃ፣ ሜዳዋ ላይ ስትወድቅ ብዙ ሰው አያያትም፤ ለማየት መንጠቆ አይኖች ያስፈልጋሉ፡፡ የሃፊዝ ዐይኖች፡፡
አበባም እንደዚያ ናት! ሮዝ ሆነች ቢጫ፣ ቀይ ሆነች ወይን ጠጅ፣ ለዘላለም አትቆይም፤ ቀለሟ ጠፍቶ ትረግፍና ሌሎች ባለቀለሞች አምጣ የምትወልድበት ፍሬ ይዛ ታልፋለች፡፡… ከዚያ በኋላ በለውጥ ቀለበት ተንከባልላ፣ ነገን ለሌሎች ትሰጣለች፤ ሌሎችም እያበቡ ይረግፋሉ፡፡
ፍራፍሬ ከአበባ ተወልዶ፣ ፍሬ ከሆነ በኋላ ውስጡ ያለው መብልና ሥጋ ውበት አፈርጥሞ ብቻ አያበቃም፤ ተቀጥፎ ይጨመቃል፡፡ ከዚያም ወደ ጽዋ ይመጣና ይጠጣል፡፡ የተጠጣው ለጠጪው ቀለም ፈጥሮ፣ ጣዕም ሰጥቶ፣ በሰው ሕይወት ውስጥ ሃይልና ጉልበት ይሆናል፤…. የለውጡ መንገድ እንዲህ ነው፡፡
    ሃፊዝ፤ ለውጥን በአበቦችና በፍራፍሬዎች ዓለም ብቻ አላየውም፤ ኮከቦችን እንዲህ ብሏቸዋል፡-
እናንተ ኮከቦች፣
ቁልቁል ተወርወሩ፣
ቁጭ ያለን ከቆመው የፍጥፍጥ አጋጩት፣
ጥሬውን ከብስል፣ የተኛን ከነቃው፣
                 ደባልቃችሁ ፍጩት፡፡
እነዚህ ሰማይ የተንጠለጠሉ የብርሃን ማህፀኖች፣ ቁልቁል ለሚወረወሩት ለምንድነው! ሰማዩ ላይ ሆነው ብርሃን ቢሰጡ አይሻልም? ሃፊዝ አይስማማም፡፡
ይልቅስ ‹‹ፈዛዛውን ከንቁው፣ ቋሚውን ከተቀማጩ አጋጩት›› ይላል ‹‹ጥሬና ብስሉን ቀይጡት፤ ይፈጭ›› ይላል፡፡ ከዚያ በኋላ አዲስ ቅርጽ፣ አዲስ መልክ፣ ሌላ አስተሳሰብና የህይወት መልክ ይዞ ብቅ ይላል፡፡
ሁልጊዜ ሣይሆን አንዳንዴ የሕይወት መዶሻ ቅርጽህን ሊቀይር ሲሻ፣ በዚህ መንገድ ብቅ ይላል እያለን ነው፡፡ መፈጨት… መድቀቅ… እንደገና በሌላ ቅርጽ መሠራት!
የሰው ልጅም እንዲህ ነው፤ ሺህ ጊዜ ይፈጫል፣ ሺህ ጊዜ ይጋገራል፤ ሺህ ጊዜ ይነድዳል፡፡ እልፍ ጊዜ ይፍማል፡፡ አንድ ጊዜ ይከሥማል! ታሪክ ግን ሥዕሉን ያስቀምጣል፤ ምትሃቱን ያወራል፡፡… ሕይወት እንዲህ ናት፡፡
ከላይ የተንጠለጠሉ የተማሩና ያወቁ፣ ያነበቡና የተጣበቡ ከላይ ወርደው ህዝቡን ያጋጩታል:: ሕዝቡን ያፋጩታል፡፡ ጥሬና ብሥሉን ባንድ ይወቅጡታል፡፡ ከሙቀጫው ሲወጣ፣ ከወፍጮው  ሲወርድ ሌላ ቅርጽ ያመጣል፡፡ እነዚህ የሕይወት መዶሻዎች፤ ከሰው ጭንቅላት አይወርዱም፡፡ ከኮከቦች አንዱ ኮከብ፣ ከአንዱ በክብር ይበልጣል፤ ጠቢቡ እንዳለው፡፡
የሃፊዝ ሌላዋ ግጥም “ጠላት መለየት” ትችላለች፤ ለቀደመችዋ ግጥም መልስ የምትሰጥ ይመሥላል፤ እንዲህ ብላ ትጀምራለች፡-
አትርሳ!
የማለዳው አየር መታደስ ያዘለው፣
ሳይደክም የሚከንፈው ወደ አበቦችህ ነው፡፡
የንቀት ግዳግዳ
የጥላቻ ጥላ.. ገፍቶ ካልከለለው
እያንዳንዱ ውበት የራሱ አሽከር አለው፡፡
ይኮተኩተዋል ያጥረዋል ሊያፈካው፣
ይሟገትለታል ቀጣፊ ሲነካው፣
ዐለም ላይ ከእንቅልፍ መልስ፣ ከመኝታ ማግስት በየማለዳው የተስፋ አየር ይነፍሳል፣ የሚያድስ ዐለም ይፈጥራል፡፡ አበቦችን ለመዳሠሥ፣ አበቦችን አቅፎ እሽሩሩ ለማለት ይመጣል፡፡ ይህ ንፋስ ተቀናቃኝ ጠላት አለው፡፡ የንቀት ግድግዳና የጥላቻ ጥላ ሊመልሰው ይችላል፡፡ ገፍትሮ ሊመልሰው ይገተራል፣ ብርሃኑን ሊጐርሥ አፉን ይከፍታል፡፡ ይሁንና ውበትም ጠባቂ አሽከር አለው፡፡ ውበትም አጃቢ አለው፡፡ ዝም ብሎ እጁን ለሰደደ ሁሉ በር አይከፍትም፤ ጥርሱን ላፋጨ ሁሉ አበባውን አያጐርስም፡፡ መቀሱን ለሣለ ሁሉ መቀንጠስ አይፈቀድለትም፡፡ ሃፊዝ እንዲህ ይላል፡-
ይኮተከተዋል ያጥረዋል ሊያፈካው፣
ይሟገትለታል ቀጣፊ ሲነካው፡፡
የውበት አሽከር የነፃነት ሎሌ አለው፡፡ እሾህ ሆኖ ጥርስ አውጥቶ፣ አበባዋን የሚከለክል አሽከር! ይህ አሽከር ቀና ነው፡፡ ለውበት የሚሳሳ፣ ለህይወት የሚያዝን፣ መቀጠፍ የሚያምመው! ሌላ አሽከርም አለ፡፡ ሃፊዝ እንዲህ የሚለው፡-
እንዳንተ ያለ አሽከር ግን!
ከፀሐይቱ ጋር እልህ የተጋባ፣
ከየንፋሱ ዐይነት፣
ከውሃው ከአፈሩ እልህ የተጋባ፣
ከውበት መደቡ መጠውለግ አረባ፡፡
ሥራውን ዘንግቶ ልቡ በእሾህ የተሞላው ጠባቂ፤ እልከኛው ጉበኛ፣ ውበት መጠበቅ ትቶ የውበት ምንጮችን ይጣላል፤ መቆሚያ መሥመሩን የውበቱን ሕልውና ጠላት አድርጐ ይቆማል፡፡ ውሃን… አፈርን… አየርን -- ጠላት አድርጐ በቆፈረው መደብ ላይ ፍፃሚው መጠውለግ ይሆናል፡፡
እንዳንተ ያለው አሽከር ግን!
ከፀሐይ ተኳርፎ ፣ከአየሩ ተጣልቶ፣
ከሃይቁ ሸሽቶ፣ ከወንዙ ሸፍቶ፣
ጫካውን ባህሩን በጥላቻ ባየ፤
ስንቱ ዕምቡጥ መሰለህ ከውበት የተለየ፡፡
ከሁሉ የተለየ የውበት ጠባቂ፣ ከሁሉ የተጋጨ የውበት ተሟጋች፣ ከሁሉ የተጣላ የመብት ተቆርቋሪ፣ ስንቱን ዕንቡጥ አሥቀጭቷል? ፀሃይን እንኳ ያላከበረ፣ አፈሩን የናቀ….
ሃፊዝ የሚለው ይህንን ነው፡፡ ከሁሉም ተጣልተህ ከሁሉም ተካስሰህ፣ ከሁሉ ተናክሰህ እንዴት ይሆናል!! አበባውን ያለፍሬ አሥታቅረው:: ወዳጆቹን አትንሣው! ይህ አንተ ከምንጩ ልትገነጥለው፣ ከተስፋው ልትለየው ያሰብከው ውበት በፍቅር ብታቆየው፣ ለተፈጥሮ፣ ለሰው ልጅ፣ ለአዳም ዘር ሁሉ መድህን ነው፡፡ ጠባቂ ሆይ ልብ ግዛ!.. ጠባቂ ሆይ አሥተውል! ውበት ያለ ፀሐይ፣ ውበት ያለ ውሃ፣ ውበት ያለ አፈር አይወለድምና ውበትን እጅህ ላይ አንጠልጥለህ አትግደለው!! ከወገኖቹ ጋር በኅብረት ይኑር!!
ኢራናዊው ሃፊዝ እንዲህ ይልሃል (ዕድሜ ለበረከት በላይነህ)
በል! አንተ ብኩን አሽከር!
ዜማውን አትሰባብር ከቅኝት ግባ፣
በፀሐይ ቂም ይዘህ አትትከል አበባ፡፡
ቀስ ብሎ በጆሯችን ሹክ የሚለን፣…ለሕይወት ቅኝት፣ ለሙዚቃ ጣዕም፣ መሠንቆና ክራር፣ ጊታርና ሣክስፎን፣ ትራምፔትና ሌላው እንደሚያሥፈልግ ሁሉ፣ ልዩ ልዩ ድምጽና ልዩ ልዩ ቀለም ስለሚያስፈልግ ተነጥለህ አታለቃቅስ፣ ኅብረ ድምፁን አታበላሽ:: ቂምህን ሣትጥል የፍቅር መዝሙር አትዘምር!- ያንተ ከቅኝት መውጣት አየሩን ረብሾታል፤ ሰላሙን አደፍርሶታል፡፡ ወደ ሕብረት ናና፣ አብረን የጣፈጠ መዝሙር፣ ያማረ ቅኔ እንቀኝ እያለ ነው፡፡
ያው የምታጭደው የዘራኸውን ነውና በፍቅር ሜዳ ጥላቻን አትዝራ! ሆምጣጤ ተክለህ የወይን ፍሬ አትጠብቅ! ነው ነገሩ፡፡
ሌላ ግጥሙ ላይ ለዚህ ሃሳብ የሚሥማሙ ስንኞች አሉት፡-
ወዳጄ!
በውድድር ሜዳ ማሸነፍ ስትቀምር፣
የትግልህን ጫፍ
ከውጤቱ ሣይሆን ከግብዐቱ ጀምር፡፡
የወፍጮ ቋት ውስጥ የስንዴ ፍሬ ከትተህ፣ የጤፍ ዱቄት ለማፈስ አታጎንብስ!!
ሃፊዝ የሀሣብ ጥልቀቱ የሕይወትን ዘንጐች የሚነቀንቅበት ጉልበትና ሃይል ልዩ ነው፡፡ ግጥም ዕምቅነት ባህርይው ነው፤ ምናባዊነትም፡፡ ሌላ ቀን ከሀሳቡና ከጭብጡ በዘለለ የግጥም ጌጦችን፣ የሳቅ ዘለላዎቹን ታቅፈን መሳቅ እንችላለን፡፡ እንደ ሽንኩርት የሚላጡ ግጥሞቹን የሰጠን ደጉ ገጣሚና ደራሲው በረከት በላይነህ ነው፡፡ መልካሙ ሰው፤ ከዚህ በላይ ይብዛልህ!

Read 1203 times