Monday, 06 May 2019 11:58

ቃለ ምልልስ “ዶ/ር ነጋሶ፣ ልጄን ዳግም ወልደው የሰጡኝ ደግ ሰው ናቸው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 - ልጄ ከእኔ ጋር የመጣችው እሳቸውን ልታመሰግን ነበር
       - ስለ እርሳቸው ገድል ምስክርነት የመስጠት ሃሳብ አለኝ


        ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ በ“ሪፖርተር” እና “ኢትኦጵ” ጋዜጣ ላይ በጋዜጠኝነት ሰርቷል:: በተለያዩ ሌሎች ጋዜጦችም ላይ ይጽፍ ነበር - ጋዜጠኛ አርአያ ተስፋማሪያም፡፡ በተለይ በ“ኢትኦጵ” ጋዜጣ፣ “ከህወሃት መንደር” በሚል ርዕስ በልጁ ስም ይጽፍ በነበረበት ጊዜ የሚያገኛቸውን የፓርቲውን ምስጢሮች ይፋ በማውጣቱ፣ በ1996 ዓ.ም በአስከፊ ሁኔታ ተደብድቦ፣ ለ6 ወራት ያህል የአልጋ ቁራኛ ሆኖ እንደነበር ይገልፃል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ላለፉት 10 ዓመታት በአሜሪካ በስደት ለመኖር እንደተገደደ ተናግሯል፡፡
በድንገት ህልፈታቸው ከተሰማው ከቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ጋር የነበረው ግንኙነት ግን ከጋዜጠኝነቱ ጋር የተገናኘ አልነበረም፡፡ ትልቅ ውለታ እንደዋሉለት ይናገራል፡፡ “ዶ/ር ነጋሶ፣ ልጄን ዳግም ወልደው የሰጡኝ ደግ ሰው ናቸው” ብሏል - ጋዜጠኛ አርአያ ተስፋማርያም፡፡  ለ10 ዓመት በስደት ከኖረበት አሜሪካ ከልጁ ጋር ከወር በፊት ወደ አገሩ የመጣበት አንዱ ምክንያትም ለተደረገለት ውለታ በአካል ተገኝቶ ምስጋና ለማቅረብ እንደነበር ይናገራል:: በተለይም በመጪው ዓመት፣ በባዮኬሚካል ኢንጂነሪንግ በድግሪ የምትመረቀው ሴት ልጁ፣ ዶ/ር ነጋሶን በአካል ተዋውቃ፣ ለማመስገንና በምርቃቷ ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ ጭምር አቅዳ ነበር፡፡ ሆኖም ህልፈታቸውን በድንገት በመስማታቸው መደንገጣቸውንና ማዘናቸውን ይናገራል፡፡ “ሳላገኛቸው ልጄም ደስታዋን ሳትገልጽላቸው፣ ሞታቸውን መስማት መሪር ሀዘን ነው የሆነብን፡፡” ብሏል ጋዜጠኛው፡፡ ለመሆኑ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ለጋዜጠኛ አርአያ ተስፋማርያም የዋሉለት ውለታ ምን ነበር? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ጋዜጠኛውን አነጋግራዋለች፡፡ እነሆ፡-

           
          መቼ ነበር ከኢትዮጵያ የወጣኸው?
መጀመሪያ ከአገር የወጣሁት ልጄን ለማሳከም ነበር፡፡ ለህክምና ያመራሁትም ወደ ህንድ ነበር፡፡
ልጅህ ያጋጠማት እክል ምን ነበር?
ልጄ የገጠማት በተፈጥሮ “ስኮሎይስስ” የተባለ የጀርባ አጥንት ችግር ነበር፡፡ ያ ችግር በአገር ውስጥ ህክምና ሳይሆን በውጭ አገር በከፍተኛ ህክምና መቀረፍ እንዳለበት የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህክምና ቦርድ ፃፈላት፡፡ ህክምናው ደግሞ ብዙ ገንዘብ ያስፈልገው ነበር::
ምን ያህል ገንዘብ ነበር የሚያስፈልገው?
ከ10-20 ሺህ ዶላር ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህንን ገንዘብ ለማግኘት ከሁለት አመት በላይ ጣርኩኝ፤ ወጣሁ ወረድኩ፤ ነገር ግን ገንዘቡን ማግኘት አልቻልኩም፡፡ በመጨረሻ በጭንቀት ላይ ሳለሁ፣ በ1999 ዓ.ም ሀምሌ  ወር ላይ የዶክተር ነጋሶን ስልክ አገኘሁና ደወልኩላቸው፡፡
ከዚያስ?
ከዚያ ማንነቴን ስነግራቸው በአካል ባያውቁኝም በጋዜጣ ላይ በምሰራው ሥራ አወቁኝ፡፡ ማወቅ ብቻ ሳይሆን የደረሰብኝን ጉዳትና ድብደባ ጭምር አስታወሱ፡፡ ከዚያም ምን እንደምፈልግ ጠየቁኝ፡፡ በአካል አግኝቼ ላናግራቸው እንደምፈልግ ነገርኳቸው:: የሚገርምሽ እኔ በደወልኩበት ጊዜ የነበሩበትን ቤት ልቀቁ ተብለው በፍርድ ቤት ተከስሰው፣ እሱን ጉዳይ በመከታተል ላይ እንደሆኑ ነግረውኝ፣ ለምን እንደፈለግኳቸው በስልክ እንድነግራቸው ጠየቁኝ:: ያው በስልክ ከመናገር ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበረኝም:: በልጄ ላይ የደረሰውን ህመም፣ እሷን ለማሳከም የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት ያደረግኩት የረጅም ጊዜ ሙከራ አለመሳካቱንና ቶሎ ካልታከመች ወደፊት ምን ሊገጥማት እንደሚችል ጭምር አስረዳኋቸው፡፡ እጅግ በጣም ነው ያዘኑት፤ በጣም ነበር የተሰማቸው፡፡
ምን ምላሽ ሰጡህ?
በዚህ ሳምንት አልችልም፤ ነገር ግን የነገርከኝ ችግር ጊዜ የሚሰጥ ስላልሆነ፣ የልጅህን ዶክመንት አምስት ያህል ኮፒ አምጥተህ፣ አበበ ለተባለው የጥበቃ ሰራተኛዬ ስጠው አሉኝ፡፡ ወስጄ ሰጠሁት:: በጣም የሚገርምሽ የመልካምነታቸው ብዛት በአካል ሳያገኙኝ፣ ልጄንም ሳያዩዋት፣ ቀጥታ ወደ ስራ ነው የገቡት:: ለፈረንሳይ፣ ለጣሊያን፣ ለህንድ፣ ለጀርመንና ለአንድ ሌላ ኤምባሲ በአጠቃላይ ለአምስት ኤምባሲዎች የልጄን ዶክመንት እያስገቡ፣ እገዛ እንዲደረግልኝ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ የሚደንቅሽ ያን ጊዜ እሳቸውም ችግር ላይ ነበሩ፡፡ መኪናም አልነበራቸውም፡፡ የራሳቸውን ጉዳይ ወደ ጐን ትተው፣ በታክሲ እየተሳፈሩ ነው በየኤምባሲው ሲዞሩ የነበረው፡፡
ውጤቱ ምን ሆነ?
መጨረሻ ላይ በወቅቱ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር የነበረው ሚስተር ፓረል ሆልዝ የሚባል ሰው፤ “በአንተ የመጣን ጉዳይ እኔ ነኝ የምጨርሰው” አላቸው፡፡ ብቻ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዶ/ር ነጋሶ ደወሉልኝና የጀርመን ኤምባሲ፣ በጀርመን ሮታሪ ክለብ በኩል፣ 10ሺህ ዶላር ፈቅዶላታል ብለው የምስራች ነገሩኝ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፤ በዚህ ገንዘብ ወደ ጀርመን ሄዳ የምትታከምበትን መንገድ ከአምባሳደሩ ጋር እነጋገራለሁ አሉኝ:: አምባሳደሩን አነጋገሩ፡፡ በዚያ ገንዘብ ግን ጀርመን አገር ህክምናው አልተገኘም:: ከዚያ በላይ ገንዘብም ማግኘት አልተቻለም፡፡ ስለዚህ ወደ ህንድ ሄዳ እንድትታከም፣ የህንድን አምባሳደር አነጋገሩልኝ፡፡ ህንድ ህክምናው በ13ሺህ ብር ተገኘ፡፡ ሆኖም በአምባሳደሩ ምክንያት ኒውደልሂ ውስጥ በ10ሺህ ዶላር ህክምና እንድታገኝ አድርገው፣ ህንድ ሄደን የተሳካ የቀዶ ህክምና አደረገች፡፡ በ2000 ዓ.ም ሀምሌ ወር ላይ ነበር፡፡ የሚገርመው ነገር፣ ህንድ ህክምና ላይ እያለች ሁሉ፣ ዶ/ር ነጋሶ እየደወሉ “እንዴት ሆነች? ህክምናው ምን ይመስል ነበር?” እያሉ ይጠይቁኝ ነበር፡፡ ይሄ መቼም ለእኔ ከደግነት በላይ ነው፡፡ እሳቸውን የምገልጽበት ቃል ቢኖር  ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ከምነግርሽና ከምገልፃቸው በላይ ደግና ትሁት ሰው ነበሩ፡፡ እጅግ የማከብራቸውና ልጄን ዳግም ወልደው የሰጡኝ፣ መልካም ልብ ያላቸው ሰው ናቸው:: እናም ህንድ ህክምናዋን ካጠናቀቀች በኋላ በዚያው ወደ አሜሪካ ሄድን፡፡
እንዴትና ለምን ወደ አሜሪካ ሄዳችሁ?
ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ በጋዜጠኝነቴ የደረሰብኝ ድብደባና በርካታ ችግሮች ስለነበሩ፣ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ለእኔ አደጋ ነበረው:: እዚህ መጥቼ መስራትም ስለማልችል፣ ልጄን ይዤ በUNHCR በኩል የአሜሪካ ኤምባሲ ወዲያው ፈቃድ ሰጠን:: በደንብ ያውቁኝም ስለነበር ወዲያው ነው ቪዛ የሰጡኝ፡፡ ከዚያ አሜሪካ ሄድኩኝ፡፡ እዚያ እንደገባን አንድ ሌላ ተጨማሪ ቀዶ ህክምና ያስፈልጋት ነበር፤ እሱን በተሳካ ሁኔታ አጠናቀቀች፡፡ ልጄ ጐበዝ ተማሪ ነች፤ ሁሉንም የትምህርት አይነቶች “ስትሬይት ኤ” ነው የምታመጣው፡፡ በሚቀጥለው አመት በባዮኬሚካል ኢንጂነሪንግ ዲግሪዋን ትይዛለች፡፡
ኢትኦጵ ጋዜጣን ጨምሮ በተለያዩ ጋዜጦች ላይ በስሟ ጽሑፍ የምታቀርብባት ኢየሩሳሌም ነች አይደል ልጅህ?
ትክክል ነሽ፡፡ ኢየሩሳሌም አርአያ ትባላለች፡፡
ያኔ ወደ ህንድ ለህክምና ስትሄዱ፣ ኢየሩሳሌም ስንት አመቷ ነበር? አሁን ዕድሜዋ ስንት ነው?
ያኔ ስምንት ወይም ዘጠኝ አመት ቢሆናት ነው:: አሁን 21 ዓመት አካባቢ ናት፡፡ አብራኝ መጥታለች:: መኪና ውስጥ ናት (ሄዶ ይዟት መጣ፤ ጠይም ቆንጆ፣ ፈገግታዋ የሚያምር ወጣት ቃለ ምልልሱን ያደረግንበት ካዛንቺስ፣ ባህርዳር ሆቴል መጥታ ተቀላቀለችን)፡፡ አሁን ፍፁም ጤነኛና ደስተኛ ናት:: ያኔ ዶ/ር ነጋሶ ባይደርሱላት ኖሮ፣ ዛሬ ይሄንን የተስተካከለ ቁመና፣ ፈገግታና ስኬት ማየት አንችልም ነበር፡፡
መቼ ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣችሁት? አመጣጣችሁስ ለምን ነበር?
ለሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ነበር የመጣነው:: አንደኛ፤ የእናቴንና የወንድሜን ሞት መርዶ አሜሪካ ሆኜ በአንድ ቀን ነው የሰማሁት፤ ነገር ግን በዚያን ወቅት ወደዚህ መምጣት ስለማልችል እርሜን አላወጣሁም ነበርና አንዱ ምክንያቴ የእናቴና የወንድሜ ጉዳይ ነው፡፡ ሁለተኛው፤ እኒህን ታላቅ ባለውለታዬን ሰው ጉልበት ስሜ ለማመስገንና ከልጄ ጋር አስተዋውቄ፣ እሷም በአካል ምስጋናዋን እንድታቀርብ ነበር፡፡ ከአንድ ወር በፊት ነው ኢትዮጵያ የገባነው፡፡ እርግጥ ወደ ህንድ ስሄድም ጉልበታቸውን ስሜ ነው የተሰናበትኳቸው፡፡
እንዴት ሳትገናኙ ቀራችሁ? በቅርቡ ነው ለህክምና ወደ ጀርመን የሄዱት ተብሏል---
ትክክል ነው፡፡ በመጣሁ በነጋታው ደውዬ እንድንገናኝ ቀጠሮ እንዲሰጡኝ ጠይቄአቸው ነበር:: የዶ/ር ዐቢይ ዝግጅቶችና ሌሎችም ፕሮግራሞች ላይ ነበሩና አልተመቻቸውም:: ማክሰኞ ደውልልኝ አሉኝ፤ ማክሰኞ ስደውልላቸውም “አይመቸኝም ፕሮግራም አለኝ” አሉኝ፤ “እባክዎ በተጣበበ ጊዜም ቢሆን ላግኝዎት” አልኳቸው፡፡ አልቻሉም፡፡ መልሼ ሀሙስ ዕለት ስደውል፣ “ቅዳሜ ወደ አማቶቼ አገር ጀርመን ለቼክአፕ ልሄድ ነው” አሉኝ:: ይህን ሲያወሩኝ እየሳቁ ነበር፤ ሲመለሱ ልንገናኝ ቀጠሮ ነበረን፡፡ በዚህ መሀል ያልታሰበ ነገር ተከሰተ፡፡ ሳላገኛቸው ልጄም ደስታዋን ሳትገልጽላቸው፣ ሞታቸውን መስማት መሪር ሀዘን ነው የሆነብን::
አሜሪካ እያለህ ትደዋወሉ ነበር?
አዎ እደውልላቸው ነበር፡፡ እንደውም መኪና አልተሸለሙም?
ኦህዴድ የሸለማቸውን ማለትህ ነው?
ዶ/ር ነጋሶ መኪናውን ሲሸለሙ ደውዬ “ኦህዴድ ሸለምዎት አይደል” ብያቸው ነበር፡፡ ያኔ ዶ/ር ዐቢይ የኦህዴድ ዋና ፀሐፊ ይመስሉኛል፡፡ ምንድነው ያሉኝ… “እኔ መኪናውንም ሆነ ህክምናውን እንዳገኝ ያደረገው ዶ/ር ዐቢይ ነው፤ በድርጅት ደረጃ አይደለም” ብለው ነግረውኝ ነበር፡፡ እንደዋወል ነበር:: ያው እንደነገርኩሽ መምጣት ስለማልችል በአካል አላገኘኋቸውም፡፡ እንደውም ያን ጊዜ “በዶ/ር ነጋሶ የለመለመች ህይወት” የሚል ጽሑፍ ጽፌ፣ የልጄን ፎቶ አያይዤ፣ በፌስቡክ ገፄ ላይ ለጥፌ፣ ብዙ ሰው ሼር እያደረገ ተቀባብሎት ስለነበር፣ ስንደዋወል “እኔ ፌስቡክ ባይኖረኝም ሰው አንብቦ ነገረኝ” ብለውኛል፡፡
እንግዲህ ፈጣሪ አልፈቀደም፡፡ አየሽ ልጄ በዋናነት ከእኔ ጋር የመጣችው ልታመሰግናቸው ብቻ አልነበረም፡፡ እንደነገርኩሽ በሚቀጥለው አመት ስለምትመረቅ የግብዣ ወረቀት ልካላቸው በምርቃቷ ላይ አሜሪካ እንዲገኙ ለመነጋገርም ነበር፡፡ ዋናው የመጣንበት ምክንያት ይሄው ነው፡፡ ከዛሬ ነገ ይመጣሉ ብለን ስንጠብቅ ህልፈታቸውን ሰማን:: ይሄ ከባድ ሀዘን ሆኖብናል፡፡ ልጄም በጣም በጣም ነው ያዘነችው፡፡ አጠገባቸው ቁጭ ብላ ልታወራቸው፣ ልታመሰግናቸውና ልታያቸው ትፈልግ ነበር፡፡ (አባትና ልጅ ተያይተው፣ አይናቸው በእንባ ተሞላ)
እንግዲህ የዶ/ር ነጋሶ ባለቤትና ልጆችም አሉ:: ከእነሱ ጋር የመቀራረብና ውለታ የመመለስ ሀሳብ አለህ?
ስለ እርሳቸው ገድል በሁሉም ሚዲያ ቀርቤ ምስክርነት የመስጠት ሀሳብ አለኝ፡፡ ያው አንድ ብዬ ከአዲስ አድማስ ጀምሬያለሁ፡፡ ከቀብር አስፈፃሚ ኮሚቴው ጋርም ቀርቤ ለመነጋገር እየሞከርኩ ነው:: የህይወት ታሪካቸው ሲነበብ ይሄ ነገር አብሮ እንዲካተት እፈልጋለሁ፡፡ እንደሰማሁት አርብ ወይም ቅዳሜ አስከሬናቸው ይገባል ተብሏል፡፡  
በመጨረሻ ምን ማለት ትፈልጋለህ?
በደጉና ሩህሩሁ ዶ/ር ነጋሶ ህልፈት እጅግ አዝኛለሁ፡፡ ውለታ ውለውልኛል፡፡ ያንን ውለታ ለመክፈል እድል አላገኘሁም፡፡ እንግዲህ ፈጣሪ ነፍሳቸውን በአፀደ ገነት ያኑርልን:: ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን እመኛለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡ 

Read 5290 times