Saturday, 04 May 2019 15:07

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳና አዲስ አድማስ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

   የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ድንገተኛ ህልፈት፣ ለኛም አስደንጋጭ ነበር፡፡ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ገደማ፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ቤተሰብና ተባባሪ ነበሩ፡፡
በማንኛውም ጊዜ ለቃለ ምልልስ ስንጠይቃቸው፣ ሁሌም በደስታና በፈቃደኝነት ነው የሚቀበሉት፡፡  በአንዳንድ ታሪካዊና ህገ መንግስታዊ  ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ስንፈልግ፣
ስልካቸው ላይ መምታት ብቻ ነው፡፡ በዕውቀትና በመረጃ የደረጀ ምላሽ ይሰጡናል፡፡ እኛ ስንፈልጋቸው ብቻ ሳይሆን እሳቸውም ሲፈልጉን፣ ደውለው ወይም ቢሮ ድረስ መጥተው
ያገኙናል፡፡ ጉዳያቸውን ይነግሩናል፡፡ ለጋዜጣ የሚሆን መረጃ ያቀብሉናል፡፡
ሁልጊዜም ቃለ ምልልስ ከተደረጉ በኋላ በዚያ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ተጨማሪ የጥናት ጽሁፎችና ሰነዶች ይልኩልናል፡፡ ለአንባቢያን የምናቀርበውን ዕውቀትና መረጃ ለማበልጸግ
አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ነው፡፡ "የአዲስ አድማስ ጋዜጣ  የፖለቲካና የታሪክ ተንታኝ" ነበሩ ለማለት ያስደፍራል፡፡ ያውም ያለ ክፍያ፡፡ ዶ/ር ነጋሶ፤ የጋዜጣችን የረዥም ዓመታት
አንባቢም ነበሩ፡፡ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የተከማቹት፣ የአዲስ አድማስ ዕትሞች ይህን ይመሰክራሉ፡፡  
የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አስከሬን ዛሬ አዲስ አበባ ገብቷል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልና ማኔጅመንት፣ በእኚህ ጎምቱ ምሁርና ፖለቲከኛ፣ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማውን
ጥልቅ ሃዘን እየገለጸ፤ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጆቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ይመኛል፡፡ ፈጣሪ ነፍሳቸውን በገነት አጽድ ያኑርላቸው!!  


Read 8166 times