Saturday, 27 April 2019 11:15

ክርስቲያኖች የተፈናቀሉትን እያሰቡ በዓሉን እንዲያከብሩ ተጠየቀ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(3 votes)

 በመጽሐፍ ቅዱስ፤ አንድ እስራኤላዊ ከግብጽ ሳይወጣ የፋሲካ በዓል ማክበር አይችልም፤ ከግብጽ ወጥቶ ነው የፋሲካ በዓልን ማክበር የሚችለው ይላል:: አንድ ሰው የፋሲካን በዓል ማክበር ያለበት ለዶሮ እና ለበግ ሳይሆን የመውጣትን በዓል በማድረግ ነው ከቀደመው በጨለማ አለም እራሱን በማውጣት ነው፡፡
አንድ ክርስትያን የፋሲካን በዓል በዘረኝነት ውስጥ ሆኖ ማክበር አይችልም፣ በጥላቻ ውስጥ ሆኖም እንዲሁ አንድ ክርስቲያን በግብጽ ሆኖ የፋሲካን በዓል ማክበር እንደማይችለው ሁሉ፣ እግዚአብሔር የመውጣት በዓል እንዲሆንላቸው ነው ለእስራኤሎች የፋሲካን በዓል የሰጣቸው:: አንድ ክርስቲያን በዓሉን ማክበር ያለበት በዶሮ፣ በቅቤ፣ በበግ፣ በልብስ፣ በዘፈንና በመጠጥ ሳይሆን እግዚአብሔር ከማይፈልገው የህይወት አኗኗር በመውጣት  ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ከሆነ  ቃሉንም አይደግፍም እግዚአብሔርም አይከብርበትም:: እንደውም ሰው ለፋሲካ ሲሠበሰብ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል ተሰብሰቡ እና በጉን ብሉ” ይላል፡፡ ለእስራኤል ሰዎች የሰጣቸው አንድ ህግ ይሄ ነው፡፡ እያንዳንዱ ግብፃዊ ቤት በኩር ልጅ ሲሞት፣ እያንዳንዱ እስራኤል ቤት ደግሞ በግ ይሞታል፡፡ በጉ የክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ስለዚህ ተሰብስባችሁ በጉን ብሉት ይላል፡፡ ምን ማለት ነው? እስራኤላውያኖች የማህበራቸው ምክንያት በጉ ነው፡፡ የሚያሠባስባቸው አመለካከታቸው አይደለም የሚያሰባስባቸው የአንድ ነገድ ልጅ መሆናቸው አይደለም፡፡ በአንድነት የሚበሉት በግ  ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ክርስቶስን የህይወቱ ዋና ማዕከል እስካደረገ ድረስ በዘር የመሰባሰብ ክርስቲያኒያዊ ፍቃድ የለውም፡፡ በአመፃ ወይም በአመለካከት አይደለም የሚሰባሰበው፤ በክርስቶስ ህይወት ብቻ ነው የሚሰባሰበው፡፡ ፋሲካም የሚያመለክተው አንድም የሚመሠረት ማህበር የአመለካከት የስርአት፣ የባህል ሳይሆን የበጉ ወይም የክርስቶስ ዋና ማዕከላዊነት መሆኑን ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የመውጣት በዓል መሆኑ ነው፤ ከባርነት ከጨለማ፣ አስተሳሰብ፣ ከዘረኝነት፣ ከክፋት መውጣት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ይህንን የዘረኝነት የክፋት አመለካከትና ህይወትን በመጽሐፍ ቅዱስ የዮሐንስ ራዕይ ላይ ሲናገር፤ “ታርደሃልና በደምህም ከነገድ ከቋንቋ ዋጅተዋል” ነው የሚለው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር፤ ሰዎች ከዚህ እንዲወጡ ይፈልጋል፡፡ በዚህ ሰአት የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች፡- ኦርቶዶክስ፣ ፕሮቴስታንት፣ ካቶሊክ… በስመ ክርስትና የሚጠሩ ሁሉ አሁን ኢትዮጵያ ከገባችበት የዘረኝነት፣ የጥላቻ፣ የግላዊነት፣ ለራስ ብቻ የማሰብ ህይወት መውጣት ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ እንዲሁ የምግብ በዓል ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ እግዚአብሔርን የሚያስከብር በዓል አይሆንም፡፡ መንፈሳዊ ይዘትና ትርጓሜ አይኖረውም፡፡ እግዚአብሔርም እውቅና አይሰጠውም፡፡
በየቦታው በርካታ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡ ለእነሱ በዓል ጠብቆ መስጠት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ለአንድ ቀን ብቻ እራሳችንን ለመፈናቀላቸው ምክንያቶች ነን ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ተፈናቃዮች ስንል ክርስቲያኖች ብቻ አይደሉም፤ የሌላ ሃይማኖት ተከታዮችም አሉ፡፡ ሁሉም የራሱን ሀይማኖት ተከታዮች የሚያፈናቅለው እራሱ መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ እንደ ክርስቲያን እውነተኛ አምልኮ፤ የወደቁትን ማንሳት ነው፣ አቅምና ረዳት የሌላቸውን መደገፍ ነው፡፡ እውነተኛ አምልኮ መዝሙር ወይም መባህና አስራት መስጠት አይደለም፡፡ እውነተኛ አምልኮ ከተጠቃ ጋር፣ ከድሀ አደግ ጋር፣ ወላጅ ካጣ ህፃን ጋር አብሮ መቆም ነው፡፡ በዚህ የፋሲካ በዓል እነዚህ ከቀያቸው ተፈናቅለው ያሉትን በማሰብ አይዟችሁ፣ ከጐናችሁ ነን በማለት በዓሉ ቢከበር፣ ሙሉ መንፈሳዊ ትርጉም ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡
ክርስቲያን አንድ ጊዜ ተቀብሎ ሁልጊዜ እየሰጠ የሚኖር ነው እንጂ ሁልጊዜ እየተቀበለ አይኖርም:: የክርስቲያንን እምነት ልዩ የሚያደርገው ሁሌ የምንቀበልበት እምነት አይደለም፡፡ ሁሌ የሚሰጥበት ነው፡፡
ደግነትንም፣ ምህረትንም፣ ይቅርታንም አንዴ ነው የምንቀበለው፡፡ ሁሌ በህይወታችን ዘመን ይቅርታን ደግነትን እየሰጠን ነው የምንኖረው ስለዚህ ክርስቲያኑ ከአምላኩ ከክርስቶስ የተቀበለውን ፍቅር፣ ርህራሄ መልሶ የማካፈል ህይወት ሊኖረው እንደሚገባ ለማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡ የተቀበልነውን የማንሰጠው ከሆነ እንግዲያውስ መቀበላችን ስህተት ነው፡፡ መቀበላችን አይጠቅመንም፡፡ ለመላው የኢትዮጵያም ሆነ በአለም ያሉ ክርስቲያኖች መልካም የፋሲካ በዓል እንዲሆንላቸው እመኛለሁ፡፡ እግዚብሔር አገራችንን ይባርክ!!

_______________

 
                                    “የትንሳኤ ፍሬ ሠላም፣ ፍቅርና እርቅ ነው”
                                       አባ ተሾመ ፍቅሬ፤ (የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤ/ክ/ጠ/ፅ/ቤት/ም/ጠ/ ፀሐፊ)


          መንፈሳዊ በዓላት ማህበራዊ አጀንዳም አላቸው:: ቤተሰብም በጋራ ሆኖ አንድ መአድ የሚቆርስበት፣ የሚጠያየቅበት፣ የሚደጋገፍበት በዓል ስለሆነ የትንሳኤን ፀጋ በእርቅ እንድናሳልፈው ይፈልጋል:: ክርስቶስ በመስቀል ላይ እኛንና እግዚአብሔርን አስታርቋል፣ ሰማይንና ምድርን አስታርቋል፤ ሰላምን አውርዷል፤ የትንሳኤ ፍሬ፣ ሠላም፣ እርቅ ነው:: በተለይ በቤተሰብ መካከል ለእርቅ የሚያስቸግሩ ጉዳዮች ካሉ፣ የጥል ጉዳዮች ካሉ እውነተኛን ትንሳኤን ማክበር የምንችለው በዚያ ቤተሰብ መካከል እውነተኛ ፍቅርና እርቅ ሲወርድ ብቻ ነው፡፡ በግለሰቦች፣ በቡድኖች፣ በቤተሰብ መሀከል ትንሳኤ ዋጋ የሚኖረው ክርስቶስ ያመጣውን ሠላም፣ ክርስቶስ ያመጣውን ዕርቅ ወደ እያንዳንዳችን ህይወት አስገብተን በእርቅ መንፈስ መመላለስ ስንችል ነው፡፡ ስለዚህ ትንሳኤን በመንፈሳዊ በዓልነቱ ከማክበራችን በፊት በእርቅ ማዕድ ውስጥ አልፈን፣ በእርቅ ህይወት ውስጥ አልፈን ያንን የትንሳኤ ፀጋ መካፈል እንችላለን፡፡ ወደ ማህበራዊ ጉዳይ ስንመጣ፣ በዓሉ በጋራ የምናከብረው ነው፤ ቤተሰብ የሚጠያየቅበት ነው፡፡
እኛ ክርስቲያኖች ይህንን በዓል በደስታ ስናሳልፍ ምናልባት መስቀል የተሸከሙ፣ የተጐዱ፣ ዛሬም የተገለሉ፣ ዛሬም የተቸገሩ፣ በበሽታ አልጋ ላይ የወደቁ ዛሬም ጧሪ የሌላቸው፣ ከክርስቶስ መስቀል ጋር መስቀላቸውን አገናኝተው የኖሩ ሰዎች በዙሪያችን  አሉ፡፡ የምናውቃቸውም የማናውቃቸውም፡፡ ስለዚህ መንፈሳችን እንድናገለግል ያነሳሳናል፡፡ ትንሳኤ ማለት አገልግሎት ነው፤ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ እኛን አገልግሏል፡፡ የአገልግሎት በዓል ነውና የተጐዱ ወገኖቻችንን ዝቅ ብለን የምናይበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ መንፈስ ትንሳኤን ብናከብር በተለይ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን፣ ትንሳኤን በቤታቸው ማክበር ላልቻሉ ህዝቦቻችን ስንደርስላቸው፤ ትንሳኤያችንን በመንፈሳዊም ሆነ በማህበራዊ ይዘቱ ሙሉ እናደርገዋለን፡፡
ሌላው አገራችንን ለመበጥበጥ ተዋናይ የሆኑ ጥቂት ግለሰቦች አሉ፡፡ በአገራችን ሰንካላ ነገሮች ሲገጥም ወጣቶች የቅድሚያ እርምጃ ይወስዳሉ::  ችግሮች ሲፈጠሩ ቀድመው ወጥተው ግጭቶቹን የሚያባብሱ ሊሆኑም ይችላሉ፡፡ ግን ከጀርባቸው እነዚህን ወጣቶች ወደዚያ እንዲሄዱ የሚገፋቸው ሁኔታም አለ፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን መሪ ፖፕ ፍራንሲስ፤ “ለሰይጣን ብለን መሬት አንሁንለት” ይላሉ፡፡ ክፋት የሰይጣን ነው፡፡ አመጽ የሰይጣን ነው፡፡ ክርስቲያኖች በበቀል አይደለም የምናሸንፈው:: የመስቀሉ ትርጉም ሲገባን፤ መስቀል አሸናፊነቱን… ክርስቶስ ሞቶበት ዝቅ ብሎበት ነው ያሸነፈው፡፡ ክርስቶስ የሰዎችን ቁስል፣ የሰዎችን በደልና ኃጢአት ተሸክሞ ነው ያሸነፈው፡፡ ማሸነፍ የሚቻለው እንደ ክርስቲያን ወድቆ ተበልጦ ነው፣ ዝቅ ተደርጐ ነው:: በአደባባይ ላይ ወጥተን በምናደርገው ሩጫ ያሸናፊነት ስሜት ልናገኝ አንችልም፡፡ ስለዚህ መረዳዳት የክርስቲያኖች መገለጫ ሊሆን ይገባል:: አጢኖ አዙሮ ማየት የክርስቲያን ወጣቶች ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ ትህትና ከክርስቶስ የምንማረው ነገር ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች መሆን የለብንም፤ ተስፋ አለን፡፡ ከመስቀል ቀጥሎ ትንሳኤ እንዳለ ሁሉ ከስቃይና ከመከራ ከኢ-ፍትሃዊና ኢ-ዲሞክራሲያዊነት ቀጥሎ ይቺ ሀገር ተስፋ አላት፡፡ ለተስፋዋ ነው መስራት ያለብን፤ ስቃይዋን መከራዋን፤ ልዩነቷን፣ ግጭቷን ለማብዛት መትጋት የለብንም፡፡
በአገራችን የምናያቸው ጨለማ፣ የብሔር ግጭት፣ መለያየት፣ መፈናቀል…ታሪኳ እዚህ ላይ አያበቃም፤ ወደ ትንሳኤው ይሻገራል፤ ስለዚህ ትንሳኤ እንዳለ እያመንን በፀሎት መንፈስ ብንሻገረው ተስፋ አለን:: ተስፋ የቆረጠ ብቻ ነው ወደ አመጽ፣ ወደ ጥል፣ ወደ ጭቅጭቅ፣ ወደ መፈናቀል፣ ወደ መገዳደል… የሚሄደው፡፡
በመግደል፣ በማጥፋት ማሸነፍ አይቻልም፤ ይልቁኑ ክርስቶስ በአምሳሉ የፈጠረውን ወንድሜን ማፈናቀል የለብኝም የሚል አመለካከት ሊኖረን ይገባል፡፡
ለሰው ልጅ የማይመጥን አካሄድ ከመከተል መቆጠብ አለብን፡፡ ብዙ ሰዎች በእምነት ጥላ ስር ያሉባት አገር ነች፡፡ ነገር ግን ሦስት ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ በሚያሳዝን ሁኔታ ተፈናቅሎ ሜዳ ወድቋል ሲባል ያሳዝናል፡፡ አፈናቃዩም አማኝ ነው፤ ተፈናቃዩም አማኝ ነው፡፡ የትኛውም ሀይማኖት ወገን ነው፡፡ ስለዚህ አይምሯችንን መልሰን እራሳችንን ለእግዚአብሔር እናስገዛ፡፡
የትንሳኤ በዓል የሠላም፣ የፍቅር፣ የደስታ በአል ነው፤ በመውደቅ፣ በመሞት የተገኘ፡፡ በሀይለኝነት በጦረኝነት ሳይሆን በታዛዥነት የተገኘ በዓል ነው:: እግዚአብሔር አገራችን ከክፉ ነገር ይጠብቅልን፤ ከሞት የተነሳው ክርስቶስ ሰላሙን ይስጠን!!

______________________



                               “ክርስቶስ የሞተው ነፍሳችን ትርፋማ እንድትሆን ነው”
                                       መጋቢ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ (በኢ/ኦ/ተ/ቤ የሃይማኖት መምህር)

         መንፈሳዊ በዓላት ከአለማዊያን በዓላት የሚለዩበት ገጽታ አለ፡፡  ውስጣዊና ውጫዊ ወይም መንፈሳዊና ስጋዊ ወይም ማህበራዊና ሃይማኖታዊ ብለን ልንለየው እንችላለን፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኑ በሁለቱም በኩል ማክበር ይችላል፤ እንደየቅደም ተከተላቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የሃይማኖት በዓል ነው፤ የክርስቲያን በዓል ነው፡፡ ከውጪ ይልቅ ወደ ውስጥ ያደላል፤ ከስጋዊ ይልቅ ወደ መንፈሳዊነት ያደላል፡፡ ከማህበራዊነት ህይወት ይልቅ ወደ መንፈሳዊ ህይወት ያደላል፡፡ ስለዚህ ህሊና አዕምሮ ነፍስ የምንላቸው፣ እንደ መላዕክት ረቂቃን ነን ወይም በረቂቅነታችን የሚስማሙን የነብስ ምግብ የምንላቸው ይቅርታ፣ ሠላም፣ ፍቅር…  ናቸው፡፡
ለአዕምሯችን ሠላም በመመገብ፣ ለነብሳችን ይቅርታ በመመገብ፣ ለልቦናችን ፍቅርን በመመገብ ልናከብረው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ይሄ በዓል ዋናውና ትልቁ የሰዎችን ስጋዊ ጥያቄ ለመመለስ አይደለም:: ክርስቶስ የተሰቀለውና የሞተው ፖለቲካን ለማረጋጋት ወይም ንግዱ ትርፋማ እንዲሆን ወይም መሬቱ ምርታማ እንዲሆን አይደለም፡፡ ክርስቶስ የተሰቀለው ነፍሳችን ትርፋማ እንድትሆን፣ አዕምሯችን ምርታማ እንዲሆን ነው፡፡
የበዓሉ መሠረታዊ ምክንያት እንዳይዘነጋ ጥንቃቄ ይገባል፡፡ የበዓሉ አስኳል መሠረት የነብስ ጉዳይ ነው፤ የሀይማኖት ጉዳይ ነው፡፡ ከሞት በኋላ ህይወት አለ፤ ከመቃብር በኋላ ትንሳኤ አለ፡፡ አዲስ ዓለምና አዲስ ህይወት አለ፡፡ የመጀመሪያው ይሄ ነው - ዝግጅት የሚደርግበት፡፡
ሁለተኛው ደግሞ በዓላት ሲመጡ የአነጋገር፣ የአመጋገብና የአለባበስ ለውጥ ያመጣሉ፡፡ በአላቱ ሲመጡ ሰዎች አመለካከታቸው ይቀየራል፤ አለባበሳቸው ይቀየራል፡፡ ንግግራቸው ሁሉ ይቀየራል፡፡ በዚህ በኩል ለውጥ ማምጣት አስፈላጊ ነው፡፡ እኔ በአላት ሲከበሩ ሦስት አይነት እርቅ መምጣት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ሰዎች ከራሳቸው ጋር መታረቅ አለባቸው፡፡ ከቤተሰቦቻቸው ወይም ከጓደኛቸው ጋር፣ ከፈጣሪያቸው ጋር መታረቅ አለባቸው፤ ከተፈጥሮም ጋር መታረቅ አለባቸው፡፡ ከተፈጥሮ ጋር መጣላት ማለት ዛፍን መቁረጥ ዛፍን መግደል ማለት ነው ወይም ለእንስሳት አለመራራት ማለት ነው፡፡ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ሲጣሉ፣ እግዚአብሔርን ገድለዋል፤ ከሰዎች ጋር ሲጣሉ ሰው ገድለዋል፡፡ ከራሳቸው ጋር ሲጣሉ እራሳቸውን ይገድላሉ፡፡ ስለዚህ በውስጥም በውጪም ከራሳቸው ጋር እንዲታረቁ መታረቅ አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ እኛ በሶስቱም በኩል የተሳካልን አይመስለኝም፡፡
ከራሳችን ጋር ተጣልተናል፡፡ ከማህበረሰቡ ጋር ተጣልተናል፡፡ ከተፈጥሮም ከፈጣሪም ጋር ተጣልተናል፡፡ ስለዚህ በአራቱም መንገድ ብንታረቅ ደስ ይለኛል፡፡ ማህበረሰቡ ይሄንን በዓል ሲያከብር እነዚህን በስራ ላይ አውሎ እንዲሆን እመክራለሁ፡፡
አባቶቻችን ሊቃውንት ቤ/ክ ሲተረጉሙ ሠባቱ መስተፃርራን ይላሉ ይሄም ማለት ነፍስ እና ስጋ፣ ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላዕክት፣ ህዝብና አህዛብ የታረቀበት ነው፡፡ የልዩነት መጋረጃ የተቀደደበት፣ ለዘመናት የተገነባው የሀጢአት ግንብ የተናደበት ወቅት፣ እግዚአብሔር ወደ ሰው የመጣበት፣ ረቂቅ ገዝፎ ሰማያዊ ምድራዊ ሆኖ፣ ዘላለማዊ ጊዜያዊ ሆኖ ሟች ሆኖ በእኛ መካከል ተገኝቶ፣ እኛ መቀበል ይገባን የነበሩትን መከራዎች ሁሉ የተቀበለበት ነው፡፡
እንግዲህ ክርስቶስ በአጠቃላይ የተቀበለው መከራ ዋጋ ለማግኘት ዝና ለማግኘት ወይም ጊነስ ቡክ ላይ ለመመዝገብ አይደለም፡፡ ለእኛ ሲል የተደረገ ነው፡፡ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ብሏል፡፡ እኛ የይቅርታ ሰዎች ነን ወይ? የፍቅር ሰዎች ነን ወይ? ሀኪም ክኒኑን መርፌውን ሲሠጠን፣ ክኒኑንም ውጠን መርፌውን ተወግተን ሽሮፑን ጠጥተን እንድንፈወስበት ነው፡፡ ክኒኑን በኪሳችን ይዘን ብንዞር፣ መድሃኒቱ ከጀርመን ይምጣ ከህንድ፣ ከአውሮፓ ይምጣ ከካናዳ ጥያቄው እሱ አይደለም፣ መዋጥ ካለብን መዋጥ መወጋት ካለብን መወጋት አለብን፡፡
ሃይማኖትም መድሃኒት ነው፡፡ ክርስትና መድሃኒት ነው፡፡ ልንጠጣው ልንውጠው ይገባል:: ወደ ተግባር ልናወርደው ይገባል፡፡ ክርስቶስ ሐሙስ ማታ እግር አጠበ፤ አርብ ተሰቀለ፤ ይሄ ሁሉ ለእኛ ትምህርት ነው፡፡ እግዚአብሔር የጠላቶቹን እግር አጠበ፡፡ የከሃዲውን ሊያሰቅል የሸጠውን የይሁዳን እግር አጥቧል፡፡ ስለዚህ ይሄ ማህበረሰብ ያፈናቀላቸው ወገኖቹ፣ የይሁዳ ያህል በድለውታል ወይ?
ክርስቶስ የሰቀሉትን የቸነከሩበትን ይቅር ብሏል እውነት እነዚህ ተፈናቃይ ወገኖቻችን ቸንክረውብናል፣ ሰቅለውናል? ሀሞት ኮምጣጤ ግተውናል ወይ?
ይልቁኑ ከእኛ ጋ ቡና ሲጠጡ የነበሩ ናቸው:: ብንታመም የሚጠይቁን፣ ብንድር ሠርጋችንን የሚያደምቁልን፣ ሀዘን ብንቀመጥ የሚያስተዛዝኑን ናቸው፡፡ እንደ አማኝ ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው አስበን፣ ሰው በመሆናችን ብቻ ሲታሰብ የሚደረግ አይደለም:: የሃይማኖት ተከታይ መሆን አያስፈልግም - ይሄንን ላለማድረግ፡፡ የኦሮሞ መኖር ለአማራ እርግማን አይደለም፡፡ የአማራው መኖር ለትግሬው እርግማን አይደለም፡፡ የትግሬው መኖር ለጉራጌው እርግማን አይደለም፤ በረከቱ እንጂ፡፡ ሰው ከሌለ ምንም የለም፡፡ የሬሳ ሳጥን የሚሸጠው እንኳን ሥራ ጠፋ ይላል፤ ሰው አልሞተም ማለት ነው፡፡
ዛሬ በእኛ ጭካኔ ከቀያቸው የተፈናቀሉት እኮ ጠምቀው ጠጡልን ብለው የሚያጠጡ፣ ጋግረው ብሉልን ብለው የሚያበሉ ነበሩ፤ ከመቀበል ይልቅ ለመስጠት የቀረቡ ነበሩ፤ አብሉኝ ከማለት ይልቅ ኑ ብሉልኝ በማለት የሚታወቁ ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ ተቀባይ፣ የሚያበላቸው የሚያጠጣቸው የሚፈልጉ ሆነዋል፡፡ ይሄ ቅደም ተከተል ሆኗል፡፡ ነገ ማን ሊፈናቀል እንደሚችል መታሰብ አለበት፡፡ እነዚህ ከቤታቸው ነው የተፈናቀሉት፡፡ ከአይምሯቸው የተፈናቀሉ አሉ፤ እነዚህን ተፈናቃዮች ማድረግ የምንችለውን ነገር ብናደርግላቸው እንደ ሃይማኖታችን መጽደቂያ ነው፤ እንደ ስጋችን የዜግነት ግዴታችን ነው፡፡
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለትንሳኤ በዓል አደረሳችሁ እያልኩ፤ ለሙስሊም ወንድሞቻችን ደግሞ በአመት አንድ ጊዜ ለሚመጣው ሚያዝያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም እንኳን በሠላም አደረሳችሁ እላለሁ!!   


Read 8878 times