Saturday, 27 April 2019 11:15

የመጅሊሱን እጣ ፈንታ የሚወስን ጉባኤ ረቡዕ ይካሄዳል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 የአደራ ቦርድና የጋራ የኡላማዎች ም/ ቤት ይቋቋማል
                                           
              አሁን በስራ ላይ ባለው የኢትዮጵያ እስልምና ምክር ቤት (መጅሊስ) የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ የሚወስን እስላማዊ ጉባኤ መጪው ረቡዕ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ከ300 በላይ ጉባኤተኞች በሚገኙበት በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡
ከ10 ወራት በፊት በኢትዮጵያ እስልምና ም/ቤት ላይ ያሉ ችግሮችን ለይቶና አጥንቶ እንዲያቀርብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አነሳሽነት  የተቋቋመው ዘጠኝ አባላት ያሉት የጋራ ኮሚቴ፤ የመጨረሻውን የጥናት ውጤቱን ከትናንት በስቲያ ለጋዜጠኞች ይፋ አድርጓል፡፡
የጋራ ኮሚቴው በመጅሊሱ ላይ የሚታዩ ችግሮችን እንዲሁም ለወደፊት እንዴት ይዋቀር በሚለው ላይ በሶስት ሰነዶች ያዘጋጀውን ጥናት በሸራተን አዲስ የፊታችን ረቡዕ በሚካሄደው ጉባኤ ይፋ ይሆናል ተብሏል፡፡  የጋራ ኮሚቴው ካቀረባቸው ምክረ ሃሳቦች መካከል ከሱፊያና ከሠለፊያ ሴክቶች የተውጣጣ የጋራ የሆነ የኡላማዎች ምክር ቤት የማቋቋም፣ በተጨማሪም ቀጣዩ የመጅሊስ ምርጫ እስከሚካሄድ አንድ የአደራ ቦርድ ማቋቋም የሚል  እንደሚገኙበት የኮሚቴው የህዝብ ግንኙነት ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
እነዚህ ሁለት አካላት በጉባኤው ከተቋቋሙ በኋላ ቀጣዩን የመጅሊስ ምርጫ በጋራ የማመቻቸት ሃላፊነት ይወስዳሉ ተብሏል፡፡
ከ300 በላይ የሃይማኖት አባቶች፣ ሽማግሌዎች ወጣቶችና ምሁራን የሚሳተፉበት ጉባኤው፤ አሁን በስራ ላይ የሚገኘው መጅሊስ የሚያበቃበትና የጋራ የኡላማዎች ም/ቤትና የአደራ ቦርድ የሚቋቋምበት ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኡስታዝ ካሚል  ጠቁመዋል፡፡  

Read 8334 times