Saturday, 27 April 2019 10:43

መልካም እረኛ አጣን!

Written by  ደ.በ.
Rate this item
(1 Vote)

   ለመቶ አመታት ምናልባትም ከዚያ በላይ ኢትዮጵያ በደም የታጠበች፣ በእንባ የጠቆረች ሀገር ነች፡፡ ከንጉሥ ንጉሥ ሲቀባበሏት፣ አንዱ ሌላውን ከስልጣን ለማውረድ አሊያም ግዛት ለማስፋት ጦር ሲማዘዝ፣ ጦሩ የሚበላው ከኢትዮጵያዊት እናት ማህጸን የወጣውን ልጅዋን ነበር፡፡ የወንድ ልጅ እናት በዚህ ጦስ በእንባዋ እየታጠበች፣ ግጥምዋን እየደረደረች፣ በሰቆቃ ለመኖር ተገዳለች፡፡ በየዘመኑም መልካም እረኛ ፍለጋ ወደ ሰማይ አንጋጣ ፀልያለች፡፡
ግና ብዙ ህልሞች፣ ብዙ ምኞቶች እጅ ላይ ገቡ ሲባል፣ ገና ምድር እልልታውን ሳታስተጋባ፣ ጨንግፈዋል፡፡ በተለይ ደግሞ መሬት ላራሹን የመሰለ የዘመናት የህዝብ ጥያቄን መልስ ይዞ የመጣው የደርጉ መንግስት ሥልጣን በያዘ ወቅት በልቡ ጮማ ያልገመጠ አልነበረም፡፡ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጅ፣ የፕሬስ ነፃነትና የመሳሰሉትን ለወረት ይዞ ብቅ ሲል፣ በየሀገሩ የተበታተነው፣ ዳያስፖራ ሳይቀር፣ ለውጡን በአበባ ለማጀብ፣ በዕውቀትና በጥበብ ለማገዝ፣ ቤት ንብረቱን ሳይቀር ጥሎ፣ ትምህርቱን አቋርጦ አገር ገብቶ ነበር፡፡ ሁኔታው ግን እንደታሰበው አልነበረም፣ ደርግም የተናገረውን ቃል አልፈፀመም:: ህዝባዊ መንግስት ከማቋቋም ይልቅ የስልጣን ጥማቱን ለማርካትና የራሱን ወንበረ ለማደላደል፣ የሌሎችን ደም ማፍሰስን ነው የመረጠው፡፡ በወቅቱ የተነሱ የነፃነት ጥያቄዎችን በውይይትና በንግግር ከመፍታት ይልቅ ጦርን መረጠ፡፡ ተቃራኒ ሀሳብ ያላቸውን በሙሉ በጥይት እየቆላ፣ ሀገሪቱን የሽለላና የፉከራ ምድር  አደረጋት፡፡
እመራበታለሁ ባለው የሶሻሊዝም ርዕዮተ-ዓለም በመተገን፣ ተመሳሳይ ርዕዮት ያላቸውን ሳይቀር እያሳደደ በመጨፍጨፍ፣ ሀገሪቱን የዋይታና የለቅሶ ሜዳ አድርጓት ቁጭ አለ:: በተለይ ኢሕአፓና የኤርትራ ነፃ አውጭ ግንባር የመሳሰሉትን ከፊሉን በመድፍ፣ ሌላውን በዲሞትፎርና አልቤን እያቃጠለ፣ የሥልጣን ዘመኑን ለማዝለቅ መዳከር ጀመረ፡፡ ሌላው ቀርቶ በራሱ በደርግ ውስጥ የነበሩትንና የተለየ ሀሳብ የነበራቸውን ሁሉ ማስወገድ ቀጠለ፡፡ ይሁንና ያሰበውን ከግብ ለማድረስ አልቻም፡፡ ብብቱ ስር የበቀለው ጎጠኛው የወያኔ ቡድን ሌላ ሰይፍ ይዞ ብቅ ሲል፣ እርሱን ለማስወገድ ተብሎም ትናንት ኢህአፓ ተብለው ልጆቻቸውን ያጡ ወላጆች፣ የቀሩትን ለብሔራዊ ውትድርና እንዲገብሩ ተገደው፣ ሌላኛው የጭዳ ምዕራፍ ተከፈተ፡፡
ደርግ ሥልጣን ሲይዝ መልካም እረኛ፣ ድንበር አስከባሪ፣ ለጭቁን ሕዝብ ተሟጋች ወዘተ-- በሚል ብዙዎች ልባቸውን የጣሉበት መንግስት ነበር፡፡ ወደ ብርሃን ሊመራን የሶሻሊዝምን ችቦ ጨብጧል፣ የጭቁኖች ህመም ይገባዋል፣ ከጭቁኑ ወገን የተገኘ ነው ተብሎም ነበር፡፡ ግና ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ ሀገሪቱን ቁልቁል ይዟት ተምዘገዘገ፡፡ እርሱም ሀገሪቱም አብረው ዘጭ አሉ፡፡
ከዚያ በኋላ ሀገሪቱ የወደቀችው በጎጥ ፖለቲካ በናወዙ ዘረኞች እጅ ላይ ነበር፡፡ ገና ሲመሰረቱ ኢሕአፓን የአማራ ፓርቲ አድርገው በመቁጠር “ከክልላችን ውጡ!” ያሉ እጅግ ኋላ ቀር አስተሳሰብ ያነገቡ ሰነፎች  ሥልጣን ያዙ፡፡ እንደኔ እንደኔ ሀገር ገነጣጥሎ ህዝብን በታትኖ፣ እንደ ጭራሮ ለየብቻ አስሮ፣ ችቦ እያሉ ከማቃጠል የባሰ ኋላቀርነት የለም:: ታዲያ የነርሱም አመጣጥ ቀላል አልነበረም:: ሲገቡ ነጠላቸውን አልገቡም፡፡ የተለያዩ ሀገራዊና ብሔር ተኮር ፓርቲዎችን ከያሉበት ለቃቅመው ይዘው መጡ፡፡ ሆኖም ልባቸው ውስጥ ያለው ምኞት ለዚህ ዓይነቱ የሰለጠነ ፖለቲካ የተዘጋጀ አልነበረም፡፡ በዚህም የተነሳ ለሴራቸው አደገኛ እንደሆኑ የገመቷቸውን ሁሉ በጊዜ አሰናበቷቸው:: አንዳንዶቹንም አሳድደው ቀጠቀጧቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ ኦነግ ነበር:: ጠመንጃውን እንኳ ሳይተኩስበት በአንዳች ሴራ ከጨዋታ ውጭ አድርገው አባረሩት፡፡ አባላቱንም በአሸባሪነት እየፈረጁ ወህኒ አጎሯቸው፡፡ የእነሱም መጨረሻ ግን አላማረም።
ጥቂት ተጋዳላይ ነን ባዮች ስልጣኑን በሙሉ ጠቅልለው፣ ሀብቱን ሲጨምሩበት፣ ሌላው በገዛ ሀገሩ ባይተዋር እየሆነ ሲያጉተመትም፣ ይህንን ማስታመም ያቃተው የኢህአዴግ መንግስት፤ ከፊሉን ወደ እስር ቤት ከትቶ ሲያሰቃይ፣ ሌላውን ደግሞ ከሀገር አባሮ ለስደት ዳረገ፡፡ ሀገር አሁንም እንደ ጥንቱ ማንባት ጀመረች፡፡ ደርግን አምባገነን ብሎ ዘወትር ሲኮንን የነበረው ኢህአዴግ ራሱ፣ ከታገለው መንግስት ብሶ ቁጭ አለ፡፡ አሁንም ህዝቡ “እግዚዮ” እያለ ወደ ሰማይ ማንጋጠጥ ጀመረ፡፡ ተስፋ ያደረጋቸው ህልሞች ሁሉ ረግፈው፣ የተስፋው አጥንት ገጥጦ ሲቀር፣ በደም በጨቀየና በእንባ በረጠበ ምድር እዬዬ ማለት ጀመረ፡፡
ከእነዚህ ትዕይንቶችና የስቃይ ቀለሞች ከተገላገልን ገና ዓመታችን ነው፡፡ አሁንም ሀገራችን በለውጥ ሀዲድ ላይ ነች፡፡ ያሁኑ ለውጥ በቁጣ የሚፎክር ሳይሆን በፍቅር የሚዘምር ነው፡፡ የለውጡ ፊታውራሪዎች “ኢትዮጵያ” የሚለው ስም ከአፋቸው የማይጠፋ፣ ህዝብን በፍቅር ድምፀት የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ህልማቸው አንድነትና ብልፅግና እንደሆነም ደጋግመው ሲነግሩን፣ እኛም አጨብጭናል። የፕሬስ ነፃነቱ ያለ አንዳች እንከን አንድ ዐመቱን ደፍኗል፡፡ ሰዎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳቢያ ታስረው መሰቃየታቸው ለጊዜው ያበቃ ይመስላል:: የመንግስት ወታደሮች ሰው እያሳደዱ መግደል፣ ያለ ፍርድ ማሰር ረገብ ብሏል፡፡
የአሁኑ መንግስት ችግር መልካም እረኛ መሆን ያለመቻል ይመስለኛል፡፡ ሀገሪቱ ብዙ ያልታሰሩ ተኩላዎች ከውስጥና ከውጭ ተለቅቀው የሚፏንኑበት ሜዳ ሆናለች፡፡ መንግስት ደግሞ ጠመንጃ መተኮስ፣ መፍትሄ አያመጣምና እንነጋገር እያለ ነው፡፡ ክፋቱ ግን የሚሰማው ብቻ ሳይሆን ሀሳቡን የሚረዳው እንኳ ያገኘ አይመስለኝም፡፡ ኢትዮጵያዊ ልጁን ሲያሳድግ በቁንጥጫ ነው፡፡ ባለጌን ሲሳደብም “ያልተቆነጠጠ!” ይላል፡፡ እኛ ሃገር መቆንጠጥ የጨዋ ልጅነት ምልክት ነው፡፡ የሀገሬ ሰው የሚበላው በሚጥሚጣ ነው፤ አልጫ ነገር አይወድድም፡፡ ትንሽ ካላቃጠለ ያቅለሸልሸዋል:: “ፍቅር ያዘኝ!” ቢል እንኳ “ኮስተር በል” ነው የሚባለው፡፡ ብዙ ነገሩ መራራ ነው፡፡ ዛሬ ለሆዱ ህመም  ድልቡል ክኒን ቢውጥም፣ መራራ ኮሶ በጥብጦ የሚውጥና “ዶሮ ማታ” እያለ ራሱን የሚደልል ነው፡፡
የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የ”ፍቅርና ይቅርታ” የአመራር ዘይቤ፣ ለአንዳንድ ክፉ አሳቢ ወገኖች፣ የክፍፍልና የግጭት አጀንዳ የተመቸ ይመስላል:: ልቡ በዘረኝነትና በጠባብት የተሞላ ሁሉ፣ አጋጣሚውን ተጠቅሞ፣ ከህዝቡ ላይ ፍቅሩንና ይቅርታውን፣ ሰላሙንና አንድነቱን ለመቀማት ምቹ ጊዜ እንደመጣለት ያስባል:: ዛሬ የምናያቸው መፈናቀሎችና መገዳደሎች የሚመነጩትና የሚተገበሩት እንዲህ ያለ ክፉ ሃሳብ በተጠናወታቸው የሃገር ጠርና ጠላቶች ነው፡፡    
እዚህ ሀገር ላይ የራሱ የመንግስት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሳይቀሩ፣ የጊዜውን ሁኔታ ተጠቅመው፣ ያሻቸውን በመናገር፣ ያሻቸውን እየጠመዘዙ ግራ አጋብተውናል፡፡ ወጣቱም የቻይናውን የባህል አብዮት ቀውስ የመሰለ ስካር ውስጥ ገብቶ፣ በማን አለብኝነት የፈለገውን ሲያፈርስ፣ የፈለገውን ሲጥስ እየታዘብን ነው:: የሚያሳዝነው ግን ቻይናውያን እንደሆኑት ሁሉ ነገሮች ካለፉ በኋላ በፀፀት የሚመጣ ነገር እንደሌለ ከታሪክ ተምሮ የሚያስተምር ጀግና አልተገኘም:: በዚህ ዘመን  ጀግና ማለት ሰዎችን ሰብስቦ የዘር ትርክት፣ የቁጭት እንባ - ንጦ፣ እሳት እየፈጠረ፣ እሳት እያጠፋ፣ የሀገሪቱን መፃኢ ዕድል ወሳኝ መሆኑን ለማሳየት መከራውን የሚበላ  ጀብደኛ ማለት ሆኗል፡፡ አሳዛኝ  ነው!
ሕዝቡ ግን ዛሬም ረሀብተኛ ነው። ሀገሪቱ ዛሬም ስንዴ እየለመነች ነው፡፡ ትውልዱ ትምህርትና ሥራ ይፈልጋል፡፡ የራሱ ኑሮ፣ የራሱ ሀብት ይሻል፡፡ ችግሩ ግን ዛሬም መልካም እረኛ የለውም፡፡ መንግስት መንጋው የተበታተነ ዕድለ ቢስ እረኛ ይመስል ከፈፋ ወደ ፈፋ፣ ከአንዱ አምባ ወደ ሌላው አምባ ይጮሃል:: የሚሰማው ግን የለም፡፡ እንደ መካከለኛው ምስራቅ እረኛ፣ ከፊት ሆኖ በፍቅር ማስከተል ይፈልጋል:: ሕዝቡ ደግሞ ከኋላው ሆኖ፣ ጅራፉን እያጮኸ የሚነዳው እረኛ ይፈልጋል:: አልተግባብቶም ማለት ይሄ ነው፡፡ መንግስት ከሚያሳድዱን ተኩላዎች አላዳነንም፤ ነገንም ተስፋ እንድናደርግ ጉልበት የሚሆነን ነገር አልሰጠንም፡፡ እንደተከበቡ በጎች ከስተናል፣ የነፃነትና የደህንነት ረሀብ እያኘከን ነው፡፡
እግዚአብሔር ሆይ መልካም እረኛ ስጠን! የሚዘምርልን ብቻ ሳይሆን ከተኩላ የሚታደገን!!

Read 1892 times